Get Mystery Box with random crypto!

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ በዚህች ቀን መጻሕፍትን የተረጐመ | ውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት



አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ በዚህች ቀን መጻሕፍትን የተረጐመ አባ ሰላማ አረፈ ። የቅድስት ሄዛዊም የመታሰቢያዋ በዓል ነው። በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር። ለዘለዓለሙ አሜን።



በዚህችም ቀን በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን የነበሩ ከኤፌሶን ሀገር ሰባቱ ደቂቅ አረፉ። እሊህም ሰባቱ ደቂቅ ከንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ውስጥ በመዛግብቱ ላይ የሾማቸው ነበሩ። አምልኮ ጣዖትን በማምለክ ሥራ አልተሳተፉም እሊህንም ቅዱሳን በንጉሥ ዘንድ ወነጀሏቸው ይዞም አሠራቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ለመሔድ በፈለገ ጊዜ እስከሚመለስ ድረስ ፈትቶ ለቀቃቸው ምናልባት ከምክራቸው ቢመለሱ ብሎ በልቡ አስቦ። ከዚህም በኋላ እሊህ ቅዱሳን ለረከሱ ጣዖታት እንዳይሰግዱ የጭፍራነት ሥራቸውን ትተው በተራራ ውስጥ ወደአለ ዋሻ ሄደው በዚያ ተሠወሩ የዋሻውን አፍ ዘጉ ከእሳቸውም ጋራ በንጉሥ ዳኬዎስ ስም የተቀረጸ ብር ነበር። ከእርሳቸውም አንዱም አንዱ በየተራቸው ወጥቶ ምግባቸውን ገዝቶ ወደእሳቸው ይመለስ ነበር። ዳኬዎስም ከሔደበት እንደተመለሰ በሰሙ ጊዜ የዋሻውን ደጃፍ ዘግተው ተኙ። የእሊህንም ቦታቸውን የሚያውቅ አማኒ የሆነ ከጭፍሮች ውስጥ አንድ ሰው ነበረ ወደ ከተማ ሲወጡ ያገኛቸው ዘንድ ጠበቃቸው ባልመጡምጊዜተነሥቶ ወደ ዋሻቸው ሄደ። ዋሻዋንም ከውስጥ እንደ ዘጓት ሁና እገኛት እርሱም በረሀብ የሞቱ መሰለው ታላቅም የደንጊያ ሠሌዳ አምጥቶ ከእሳቸው የሆነውን ገድላቸውን ጽፎ በቀዳዳ ወደ ዋሻው ውስጥ አስገባው። እሊህም ቅዱሳን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዘመናት አንቀላፉ ዳኬዎስም ሙቶ እስከ ቴዎዶስዮስ ብዙ ነገሥታት ነገሡ። በዚህም ምእመን ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዎች ተነሥተው ብዙዎች ተከተሏቸው። በዚያንምጊዜ እሊህን ቅዱሳን ሰባቱን ደቂቅ እግዚአብሔር አነቃቸው ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ግልጽ ያደርግ ዘንድ። ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው አንዱ ምግባቸውን ሊገዛ የከሀዲ ዳኬዎስንም ወሬ ይሰማ ዘንድ ብር ይዞ ወጣ ወደ ከተማም በገባ ጊዜ የከተማዋ ሁኔታ ተለወጠበት። በከተማውም በር መስቀሎችን አየ በየቅጽሮቿም የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ስሙን ያለ መፍራት ሲጠሩ ሰማ አንዱንም ሰው ይህች አገር ኤፌሶን አይደለችምን ብሎ ጠየቀ እርሱም አዎን ናት አለው። ያንንም ብር አውጥቶ ለባለሱቁ ሰጠው ምግባቸውን ይሸጥለት ዘንድ ባለሱቁም ያን ብር ተመለከተው የንጉሥ ዳኬዎስም ስም ተቀርጾበት አገኘውና ያንን ሰው ይዞ በአንተ ዘንድ የተሸሸገ መዝገብ አለ ይህ ምልክት ከአንተ ተገኝቷልና አለው። እንዲህም ሲጣሉ ወደእርሳቸው ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እንዲህም ብለው ጠየቁት አንተ ከወዴት ነህ ከዚህችአገር ነኝ አላቸው። ማንን ታውቃለህ አሉት እርሱም ዕገሌንና ዕገሌን አላቸው ከዘመን ብዛት የተነሣ የጠራቸውን ሰዎች የሚያውቃቸው የለም። ስለዚህም በእርሱ ላይ ተቆጥተው ወደ ዳኞችና ወደ ኤጲስቆጶስ አባ ቴዎድሮስ ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስም አቀረቡት። ንጉሡና ኤጲስቆጶሱም ከአንተ የሆነውን እውነቱን ንገረን ከወዴት አገር ነህ አሉት። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው እኛ ሰባታችን የከሀዲ ንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ነን እርሱም ወጥቶ ወደ ሌላ አገር በሄደ ጊዜ ከአንዷ ዋሻ ውስጥ ገብተን የዋሻዋን በር ዘግተን ተኛን። እነሆ ስንነቃ የምንመገበውን ምግብ እገዛ ዘንድ ላኩኝ። ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ በሰሙ ጊዜ ተነሥተው ወደዚያ ዋሻ ከእርሱ ጋራ ሔዱ ከእርሳቸውም ጋራ ብዙ ሕዝቦች አሉ ቅዱሳኑንም ተቀምጠው አገኙአቸው። የዘመኑም ቁጥር በውስጡ የተጻፈበትን በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመን የሆነውን ሠሌዳውን ወድቆ አገኙት ዘመኑም ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት እንደሆነ ታወቀ። ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉትም ይህን ድንቅ ሥራ አይተው ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አመኑ። እሊህ ሰባቱ ደቂቅንም በጠየቋቸው ጊዜ ከእርሳቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩአቸው። ከዚህም በኋላ ተመልሰው ተኙ። ነፍሳቸውንም ከእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ንጉሥም የወርቅ ሣጥን ሠራላቸው በሐር ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው። ከሥጋቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ። ስማቸውም
መክሲማኖስ፣ ታሙኪሮስ፣ መርዳዲሞስ፣ ዮሐንስ፣ ቈስጠንጢኖስ፣ አዝሚ እና ዲዮናስዮ ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የእሊህም ቅዱሳን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

አሜን።

"ጽዮንን የሚወዳት አይደክምም"
ቅዱስ ያሬድ