Get Mystery Box with random crypto!

ሰሞንኛ ..! በእውቀቱ ስዩም ትናንት ማታ በረንዳው ላይ ቁጭ ብለን ፥ ውስኪና የተልባ ጁስ እየ | ውብ ታሪኮች ®

ሰሞንኛ ..!
በእውቀቱ ስዩም

ትናንት ማታ በረንዳው ላይ ቁጭ ብለን ፥ ውስኪና የተልባ ጁስ እየጠጣን ስናወጋ ምኡዝ እንዲህ አለ፤ “ ከብዙ ሴቶች ጋራ መተኛት የብዙ ወንዶች ፍላጎት ነው ፤ ወንድ ልጅ ቢቻለው፥ ቢሰምርለት ቢቆምለት ከመላው ሄዋን ዘር ጋራ ቢዳመር አይጠላም፤ በሆርሞኑ በደሙ ያለ ነገር ነው፤ የባዮሎጂ ስሪቱ እንዲያ ነው ! ሼህ ቢሆን ቄስ ሳይንቲስት ሆነ ግምበኛ ለውጥ የለውም! ወንድ ልጅ ባንድ ሴት እሚወሰነው ሁለተኛ አማራጭ ሲያጣ ነው፤ በርግጥ ፍቅር የያያዘው ወንድ በፍቅረኛው ሊወሰን ይችላል! የፍቅርን ሀይል አልክድም”

ብዙ ሴቶችን መተኛት ለብዙዎቻችን የማይሰምር ህልም ነው፤ ስለዚህ የተሳካለትን ሰው እንቀናበታለን! እንጠምደዋለን! ባደባባይ ብናገኘው በግልምጫ እናፈርጠዋለን! በልባችንም እንዲህ እንብሰከሰካለን! እኔን የንጦጦ ብርድ ሲከካኝ እያደረ እሱ ምናባቱ ስለሆነ ነው እያማረጠ እሚበላው? ክርክሩ ላይ ድግምት አስሮ ካልሆነ በመልክ እንኳ እኔ እበልጠዋለሁ! እንዲያውም እኔ ሳልቦንሰው አልቀርም! ይሄ ሻኛ ፊት ! መፈጠሩን እንዲጠላ ካላደረሁት ወንድ አይደለሁም!

ሴቶች ፥ አተራማሽን ወንድ ሲገጥማቸው የወንዶችን ያክል አይጨክኑበትም፤ እንዲያውም በሴት አውል የሚሳቡና የሚጠመዱ ሴቶች አይጠፉም! ይሁን እንጂ ብዙ ሴት የሚያንባባ ወንድ ፥ ባብዛኛው ሴቶች ዘንድ እንደ ቁምነገር አይታይም! ልብን የሚያሳርፍ ባል ፤ መከታ የሚሆን አባት መሆን አይችልማ! ንብረቱን ትኩረቱን ጊዜውን የትም ስለሚበትን ለዘለቄታ ፤ ለህይወት አጋርነት | አይመርጡትም፤

ማህበረሰብ የቆመው የግለሰቡን እንደአሻው የመኖር ፍላጎት በመጨቆን መሆኑን አንርሳ! ከማህበረሰብ ተግባሮች አንዱ ፍትሀዊ የፍቅር ጉዋደኛ ክፍፍል ማድረግ ነው! አንድ ወንድ ብዙ ሴት ሰብስቦ ከያዘ፥ የሆነ ሰፈር ላይ ወንዶች በብህትውና መኖር ይገደዳሉ፤ ስለዚህ ብዙ ሴት የሚይዝ ወንድ የማህበረሰቡን ፍትሀዊ የሚስት ክፍፍል ያደናቅፋል ፤ ማህበረሰብ ሴት አውሉን በምድር በህግ ይቀጣዋል፤ በገሀነም እሳት ያስቦካዋል፤ ከዚያ በተረፈ በሀፍረት ያደባየዋል! በባህላችን ብዙ ሴት ጋ የሚሄድ ወንድ እንደ ሰው አይቆጠርም፤ ከአህያ ነው ምድቡ! “ አለሌ” የሚለውን ስም አስበኸዋል? አለሌ ማለት ከሴት አህያ አልፎ ሴት ፈረስ የሚሰርር አህያ ማለት ነው !

ስለዚህ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የተሳካላቸው መፍቅሬ -ሴት ወንዶች፥ ደስታቸውን ላለማጣት እና ደሞ በማህበረሰብ በትር ላለመቀጣት፥ በድብቅ በስውር በለሆሳስ ይራመዳሉ፤ በባህላችን ቅምጥ ፤ ውሽማ እና እቁባት አያያዝ ላይ የነበረው ምስጢራዊነት በሲአይኤ ውስጥ እንኳ አይገኝም፡፡ ንብረት ገላው የገጠመው መከራ ከዚህ አንጻር መታየት ያለበት ይመስለኛል! ማንም ስለንብረት ገላው ልጆችም ሆነ ስለ ልጆቹ እናት ደንታ ያለው አይመስለኝም! ስለራሱ ልጆች ደንታ ያለው አበሻ ምን ያህል ይሆናል? አጅሬ የተሸወደው ከብዙ ሴቶች ጋራ ይተኛ እንደነበር ባደባባይ ሲናዘዝ ነው ! እግዜር ይቅር ቢለው እኛ ይቅር አንለውም! ቦታ ብንቀይር ምን ይመስልሀል?”

“ ርእስም ብንቀይር ደስ ይለኛል”


@WubTarikoch