Get Mystery Box with random crypto!

«ኡድሂያ ለማረድ ካቀዱ ከወዲሁ ጥፍርና ጸጉርዎን ከመቁረጥ ይቆጠቡ! ------------------- | ★ አለም አቀፍ የኢትዮጲያ ሙስሊሞች ድምፅ ★

«ኡድሂያ ለማረድ ካቀዱ ከወዲሁ ጥፍርና ጸጉርዎን ከመቁረጥ ይቆጠቡ!
-------------------
☞ እንድ ሙስሊም ሀጅ የማያደርግ ከሆነና በዒድ አል አድሀ እለት ኡድሂያን ለማረድ ካሰበ የዙልሂጃ ወር ከገባበት የምጀመሪያዉ ቀን ጀምሮ ጥፍሩንና ጸጉሩን አይቆርጥም፤ ቆዳውንም አይቀርፍም። ይህም ተከታዩን የኡሙሰለማ ሀዲስ መሰረት ያደረገ ነው።

ከኡሙ ሰለማ በተላለፈ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፤ «የዙልሂጃ ወርን ጨረቃ ካያችሁና ከናንተ መካከል አንዱ ኡድሂያ ለማረድን ካቀደ፤ ፀጉሩንና ጥፍሩን ከመቁረጥ ይቆጠብ» አል ኢማም አህመድ ዘግበውታል። በሌላም ዘገባም «ኡድሂያውን እስኪያርድ ድረስ ከፀጉሩና ከጥፍሩ ምንንም አይቁረጥ» ብለዋል። እንደዚሁ፤ «ከሰውነቱ ቆዳ ወይም ከፀጉሩ ምንንም አይቁረጥ» ብለዋል።

ይህ ማንኛውም ሙስሊም እራሱን በሀጅ ላይ ካሉ ሰዎች ጋር የሚያመሳስልበት እና የተወሰኑ የኢህራም ክልከላዎችን ከነሱ ጋር የሚጋራበት ዲናዊ ስርአትና ነብያዊ ትዕዛዝ ነው።

☞ ጸጉርንና ጥፍርን ከመቁረጥ የሚከለከለው ለራሱ ወይም ለሰው በራሱ ገንዘብ የሚያርድ ሰው ብቻ ነው። ህጉ የሚመለከተው የሚያርደዉን ሰው ብቻ ነው ሲባል፤ በወኪልነት ለሌላ ስው የሚያርድን ሰው አይጨምርም።

☞ እያወቀ ጥፍሩን ወይም ጸጉሩን የቆረጠ ወንጀል ፈጽሟልና ወደ አላህ በተውበት ሊመለስ ይገባዋል፤ ኡድሂያው ግን አይበላሽም ማካካሻ ከፋራም የለበትም። አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሳይሆን ወንጀሉን ቢፈፅምም ኡድሂያ ማረዱን መተው የለበትም።

☞ በስህተት ወይም በመርሳት ፀጉሩን ወይም ጥፍሩን የቆረጠ ሰው ምንም ወንጀል የለበትም። በተመሳሳይ መልኩ በጣም አስፈላጊ ሲሆን ቢቆርጥ ችግር የለውም። ለምሳሌ የተጎዳን የሰውነት ቆዳ ለማከም ወይም የተሰበረ ጥፍሩን ለማስተካከል መቁረጥ ይፈቀድለታል።

፠ ስለ ኡድሂያ ጥቂት ተጨማሪ ነጥቦች

1 - በዙልሂጃ አስር ቀናት ከተወደዱ ተግባሮች መካከል ኡድሂያን በማረድ ወደ አላህ መቃረብ አንዱ ነው።

2- ኡድሂያ በጣም ከጠነከሩ የነብዩ صلى الله عليه وسلم ሱናዎች መካከል ነው። ኡድሂያ የነብዩ ኢብራሂምን ሱና ህያው ከማድረግ በተጨማሪ ለድሆች እና ችግረኞች መድረስ ነው።

3- ኡድሂያን በተመለከተ አላህ ከኛ የሚፈልገው ለእርሱ ያለንን ፍራቻ ተቅዋና ታዛዥነት ግልጽ ማድረጋችንን ብቻ ነው። አላህ እንዲህ ብሏል፤

{ﻟَﻦ ﻳَﻨَﺎﻝَ اﻟﻠَّﻪَ ﻟُﺤُﻮﻣُﻬَﺎ ﻭَﻻَ ﺩِﻣَﺎﺅُﻫَﺎ ﻭَﻟَٰﻜِﻦ ﻳَﻨَﺎﻟُﻪُ اﻟﺘَّﻘْﻮَﻯٰ ﻣِﻨﻜُﻢْ ۚ ﻛَﺬَٰﻟِﻚَ ﺳَﺨَّﺮَﻫَﺎ ﻟَﻜُﻢْ ﻟِﺘُﻜَﺒِّﺮُﻭا اﻟﻠَّﻪَ ﻋَﻠَﻰٰ ﻣَﺎ ﻫَﺪَاﻛُﻢْ ۗ ﻭَﺑَﺸِّﺮِ اﻟْﻤُﺤْﺴِﻨِﻴﻦَ} الحج 37

አላህን ሥጋዎቿም ደሞቿም ፈጽሞ አይደርሰውም፡፡ ግን ከእናንተ የሆነው ፍራቻ ይደርሰዋል፡፡ እንደዚሁ አላህን በመራችሁ ላይ ልታከብሩት ለእናንተ ገራት፡፡ በጎ ሠሪዎችንም አብስር፡፡» አል ሐጅ 37

4- ኡድሂያ የሚታረደው ከዒድ ሰላት በኋላ ነው። የአላህ መልዕክተኛ صلى الله عليه وسلم ከኢድ ሰላት በፊት ያረደ ሰው እንዲደግም አዘዋል።

5- ሚዛን በሚደፋው የኡለማዎች አቋም መሰረት የዒድ ሰላት ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ የሶስተኛው ቀን ጸሀይ እስክትጠልቅ ድረስ ኡድሂያን ማረድ ይቻላል።

6- ወንድም ይሁን ሴት ግመል፣ የቀንድ ከብቶች፣ በግና ፍየል ለኡድሂያ ይታረዱሉ።

7- የአላህ መልዕክተኛ صلى الله عليه وسلم እንከን ያለባቸውን እንስሳት እንዳናርድ ከልክለዋል። አንድ አይኑ የታወረ፣ ስብራት ያለበት፣ የከሳና የደከመ ወይም የታመመ እንስሳ ለኡድሂያ አይሆንም።

8- ኡድሂያን ለብቻ ማረድ እንደሚቻለው ሁሉ ለሰባት ሆኖ አንድን ወይፈን ወይም በሬ መጋራትም ይቻላል።

9- አንድ ሰው ኡድሂያ ሲያርድ ለራሱ እና በህይወት ላሉም ይሁን በህይወት ለሌሉ ቤተሰቦቹ አስቦ ሊያርድ ይችላል።

10- የኡድሂያውን ስጋ፣ ለቤት፣ ለስጦታ እና ለሰደቃ አድርጎ ሶስት ቦታ መከፋፈሉ ሱና ነው። ይህ ማለት ግን እንደ አስፈላጊነቱ ለሶስቱም ያውለዋል ማለት እንጂ ሶስት እኩል ቦታዎች ይከፋፍለዋል ማለት አይደለም።»

: አቡ ጁነይድ ሳላሕ አሕመድ