2022-07-29 11:34:07
ነገ እኮ ሐምሌ 22 #ቅዱስ_ዑራኤል
በነጎድጓድና በመባርቅት ላይ ለተሾመ ለመልአኩ ለቅዱስ #ዑራኤል አመታዊ ክብረ በአል እንኳን አደረሰን
በመላእክት ከተማ በራማ ካሉት ሦስት ነገዶች ዉስጥ አንዱ ነገድ ሥልጣናት ይባላል፡፡ በሥልጣናት ላይ ከተሾሙ ሊቃነ መላእክት ዉስጥ አንዱ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሱርያል ይባላል፡፡ሱርያል የሚለዉ ስም በአንዳንድ ድርሳናት ካልሆነ በስተቀር እምብዛም አይታወቅም ትርጉሙም ‹‹‹ዐለቴ እግዚአብሔር ነዉ››› ማለት ነዉ፡፡ ሱርያል የቅዱስ ዑራኤል ሌላ ስሙ ነዉ፡፡ ዑራኤል ማለት ‹‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ነዉ›››ማለት ነዉ፡፡ በቤተ ክርስቲያንም በስፋት የሚተወቀዉ ስም ዑራኤል የሚለዉ ስም ነዉ፡፡/ድርሳነ ዑራኤል 1991 ገጽ 14/ በመጽሀፍ ቅዱስ ዉስጥ ስለ ቅዱስ ዑራኤል በስፋት የምናገኘዉ በመጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል ነዉ፡፡
ዕዝራን ይራዳዉ የነበረ ፤ለዕዝራም ጠፍተው የነበሩ የብሉይ ኪዳን መጻህፍትን እንደ ገና እንዲጽፋቸዉ ጽዋ ልቦና አጠጥቶ ምሥጢር የገለጠ ቅዱስ ዑራኤል ነዉ፡፡(ዕዝ ሱቱ2 )፡፡
‹‹‹በመብረቅና በነጎድጓድም ላይ የተሾመ ታላቅ መላክ ነዉ››››ሄኖክ 6፡2
ምሥጢረ ሰማይም ለሄኖክ ያሳየዉ ዕዉቀትን የገለጠለት እርሱ ቅዱስ ዑራኤል መሆኑን ጽፏል፡፡(ሄኖክ 28፡13-14)፡፡
እመቤታችንም በኪደተ እግርዋ ኢትዮጵያን በዞረች ጊዜ ቅዱስ ዑራኤል ያገለግላት እንደነበርና እንዳስጎበኛትም በድርሳነ ዑራኤል ተጽፏል ፡፡
ለአዳም የድህነትን ዜና የነገረዉ ቅዱስ ዑራኤል ነዉ ዮሴፍን ብርታት ሰጥቶ ከብእሲት ጲጥፋራ ያዳነዉ ቅዱስ ዑራኤል ነዉ ለእዝራ ምሥጢር የገለጠለት ቅዱስ ዑራኤል ነዉ የሚያረጋጋ ለኃጢያተኞች ምህረት የሚለምን መልአክ ነዉ፡፡(ስንክሳር ጥር)
ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በሐይቅ እስጢፋኖስ ለገዳሙ መነኮሳት እህል እየፈጨ ዉሃ እየቀዳ እመቤታችንን እየተማጸነ ሲኖር አንድ ቀን ከሥዕሏ ሥር እየሰገደ ሳለ መልአኩ ዑራኤል ተገልጦ ጽዋህ ልቦና አጠጣዉ፡፡ከዚያ ጀምሮ ምሥጢረ ሰማይ ወምድር ተገልጦለት ከ 40 በላይ መጻህፍትን ደርሷል፡፡ (መጽሐፈ አርጋኖን )
በእለተ ስቅለት የጌታ ደሙን በብርሃን ፅዋ ተቀብሎ በዓለም የረጨ ቅዱስ ዑራኤል ነው
ሐምሌ 21 እና 22 ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትእና እዝራ ሱቱኤልን የእውቀት ጽዋ ያጠጣበት ነው በአምላኩ አማላጅነቱን ኑና ተማጸኑት። በጸሎቱ ለተማጸነ ከአምላኩ በረከትን ምህረትን የሚያሰጥ አዛኝ እርሩህ መልአክ ነው። አሁንም ይህ ዓለም በአማላጅነቱ አምኖ ጸበሉን ቢጠጣ ከክፉ በሽታ እንደሚፈወሱ ቃለ ኪዳን ተሰጥቶታል፣በፍጹም መጠበቅን ጠብቆ ለዚህ ያደረሰን አምላካችን ክብርና ምስጋን አምልኮትና ውዳሴ ይድረሰውና ይህን ታላቅ መልዕክ በችሎታችን መጠን እንድናመሰግን ና እንድናገለግል እግዚአብሔር ይርዳን አምላክ ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ከመልዐኩ ከቅዱስ ዑራኤል በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡
ለእዝራ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ዕዉቀትን የገለጸ መልአክ ለኛም ይለመነን "አሜን"
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
849 viewsBiruk, 08:34