Get Mystery Box with random crypto!

​​የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፤ ' የሕገ-ወጥ ቤቶች ፈረሳ ሒደት መስጅድ ላይ ያተኮረ አይደለም ' | 🗣 ወቅታዊ_መረጃ 🇪🇹

​​የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፤ " የሕገ-ወጥ ቤቶች ፈረሳ ሒደት መስጅድ ላይ ያተኮረ አይደለም " አለ

ዛሬ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ኃላፊ  አቶ ሃይሉ አዱኛ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በዚህም ወቅት እየተካሄደ ስላለው የቤቶች ፈረሳ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው ፤  ምንም እንኳን እነማን እንደሆኑ በግልፅ ያልተናገሩት " አንዳንድ አካላት " ሲሉ የጠሯቸው በኦሮሚያ ክልል ህገ ወጥ ግንባታዎችን የማፍረሱን ሥራ በአንድ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ማስመሰላቸው ፈጽሞ ትክክል አይደለም ብለዋል።

" የሕገ-ወጥ ቤቶች ፈረሳ ሒደት መስጅድ ላይ ያተኮረ አይደለም " ያሉት ኃላፊው " በክልሉ 600 በሚሆኑ ከተሞች በህገ-ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን የማፍረስ ሒደት እንደሚከናወን ገልፀዋል።

ሕግ የማስከበር ስራው በዋናነት ህገ-ወጥነትን በዘላቂነት ለመከላከል ያለመ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ኃላፊው ይህ ስራ በሚሰራበት ወቅት የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ፤ አካላት የአንድ ብሔርና ሃይማኖት እንደተጠቃ አድርገው በመገናኛ ብዙሃን የሚያራግቡት ትክክል አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ህገወጥ ግንባታ ሲካሄድ መንግሥት ለምን ዝምታን መረጠ በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም ፤ " መንግስት ኃላፊዎቹን ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ለማረጋገጥ እንወዳለን " ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ኃይሉ አዱኛ ፤ " የሃይማኖት ተቋማት እና የእምነቱ ተከታዮች እምነትን ተገን አድርገው ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን በጋራ ሊከላከሉ ይገባል " ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በኦሮሚያ ክልል፣ ሸገር ከተማ በርካታ መስጅዶች እየፈረሱ መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በተደጋጋሚ ማሳወቁ እንዲሁም መፍትሄ እንዲፈለግ ለጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ደብዳቤ መፃፉ የሚዘነጋ አይደለም።

ምክር ቤቱ ከቀናት በፊት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ላይም በ " ሸገር ከተማ " ኢስላምንና ሙስሊሞችን በናቀ መልኩ በመስጂዶች ላይ እየተደረገ ያለው የጅምላ ፈረሳ ሂደት በአስቸኳይ እንዲቆም፥ እንዲሁም ለፈረሱት መስጊዶች የክልሉ መንግስት ምትክ ቦታ በመስጠት በአስቸኳይ ተመልሰው እንዲገነቡ በማድረግ ሕዝበ ሙስሊሙን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ እንዲክስ ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወሳል።

የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ፤ በሸገር ከተማ አስተዳደር እስካሁን ከ19 በላይ መስጂዶች ፈርሰዋል ሲል መግለጫ መስጠቱ የሚዘነጋ አይደለም።

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማየት የቴሌግራም ገፃችንን ይመልከቱ!
https://t.me/wektawi1mereja