Get Mystery Box with random crypto!

ከሚያነበው መጽሐፍ ገጽ ውስጥ የሰርግ ወሬ ሲነፍስበት ላፍታ ንባቡን ገታ አድርጎ፤ ሶፋ ላይ ተደላድ | ወግ ብቻ

ከሚያነበው መጽሐፍ ገጽ ውስጥ የሰርግ ወሬ ሲነፍስበት ላፍታ ንባቡን ገታ አድርጎ፤ ሶፋ ላይ ተደላድላ ስልክ ላይ ያፈጠጠችውን ልጁን አያት። የእድሜዋ መናር አሳሰበው። ደግሶ ድሮ የመመረቅ እና የመጎረር፣ የመደነቅ ስሜት በአምሮት ናጠው።

"ለምን ነው ፍቅረኛ ይዘሽ ወደ ትዳር ጎዳና ማትራመጂው? እስከመቼ እንዲሁ በዋል ፈሰስ ትባክኛለሽ?" አላት።

ዐይኗን ከስልኳ ሳትነቅል "መች አለና" የሚል መልስ አሽቀነጠረች።

"ምኑ?"

"ፍቅርም፣ ሁነኛ ፍቅረኛም"

መልሷ ከነከነው። ህልምን ፈርቶ እንዴት ከመተኛት ያፈገፍጋል ሰው? "ፍቅር ላንቺ ምንድን ነው?"

"ክርስቶስ"

መልሷ ግማሽ ልቡን ሀሴት አጠጣው፤ ግን ድፍን መልስ አይወድም። "አብራሪው!"

"በቃ ለሚወዱት ሰው እስከሞት ድረስ ታምኖ መጓዝ፤ ያውም ያለማፈግፈግ፣ አሁን ያለው ወንዱም ሴቱም ታምኖ ሚሄደው ተቃቅፎ የልቡን እስኪያደርስ፤ ስጋውን እስኪያስደስት፣ ኪሱን እስክታልብ ነው። ስሜት እና ብልጠት እንጂ ፍቅር የለም አባ" ምርር አለች።

"ምን ያህል የፍቅር ሰው ነኝ ትያለሽ? ፍቅርንስ በገለጽሽው መንገድ ለመኖር ምን ያህል ዝግጁ ነሽ?"

ጨነቃት!
መልስ ከውስጧ ተሰለበ።
ዝም አለች!
ዝምታዋን ታክካ ራሷን መመርመር ያዘች።

#ኤልዳን
by @eldan29

@wegoch
@wegoch
@paappii