Get Mystery Box with random crypto!

ውርስ! ••• ቅርንጫፌ ውስጥ ካሉ ቆጣቢ ደንበኞች መካከል ትልቅ ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ደንበኛ ነው | ወግ ብቻ

ውርስ!
•••
ቅርንጫፌ ውስጥ ካሉ ቆጣቢ ደንበኞች መካከል ትልቅ ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ደንበኛ ነው። በየጊዜው የሚያስቀምጠው ገንዘብ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይቼ አላውቅም። ታታሪ ሰራተኛ፣ ባተሌ እንደሆነ ገንዘብ ሊያስገባ ለብሶት የሚመጣው የቆሸሸ የሥራ ቱታ ምስክር ነው። አንድ ትልቅ ጋራዥ እንዳለው አጫውቶኛል።
ለተወሰኑ ወራት ዐይቼው ስለማላውቅ አሳስቦኝ ስልኩ ላይ በተደጋጋሚ ስደውል ስልኩ አይሰራም።
                             *
አንድ ቀን ጠዋት አዳፋ፣ ለሐዘን ቀለም የተነከረ ነጠላ የለበሱ፣  እጅግ የተጎሳቆሉ እናትና ፊቷ በማድያት የጠቆረ ሴት ከእኔ ቀድመው ቢሮ ጠበቁኝ።
ወንበሬ ላይ ተደላድዬ እንደተቀመጥሁ የፍርድ ቤት የውርስ ውሳኔ እንዲሁም ከባንኩ ዋናው መሥሪያ ቤት የህግ መምሪያ የተሰጠ አስተያየትና የባንክ ደብተር አቀበሉኝ። የባንክ ደብተሩን ስገልጸው ከታታሪው ደንበኛዬ ፎቶ ጋር ተፋጠጥኩ።
"ምን ሆኖ ነው?!"
"ሥራ ቦታ አደጋ ደርሶበት አረፈ ልጄ!" አሉኝ - አሮጊቷ።
የሰማሁትን ለማመን አልቻልኩም። እጅግ ደነገጥሁ። የፍርድ ቤት ውሳኔውን አነበብኩት የውርስ ውሳኔው በቅርንጫፋችን ያለው ገንዘብ ለእናቱና ለእህቱ እንዲካፈል የሚያዝዝ ነው። እንዲህ የተጎሳቆሉት ሴት በእርግጥም የእዚያ የባተሌ፣ የእዚያ በየሳምንቱ በብዙ ሺህ ብሮች ሂሳቡ ላይ የሚያስገባ፣ የእዚያ ሚሊዮን ብሮች ሒሳቡ ላይ ያጠራቀመው ደንበኛዬ እናት መሆናቸው እጅግ ገረመኝ።
"እግዚአብሔር ያጽናዎ እናቴ! ነፍስ ይማር! እጅግ የማከብረው ደንበኛዬ ነበር። እጅግ ታታሪ ሰው ነበር። ስልኩ ላይ ደጋግሜ ስደውል የማይነሳው ለካ ለእዛ ነበር ለካ?! ወይኔ ወንድሜ!" አልኋቸው።
"ይኸው እንዲህ ጥሎ ለሚሞተው ገንዘብ 'ሥራ፣ ሥራ!' ሲል የት ወደቅሽ ሳይለኝ፣ ታምሜ ሳይጠይቀኝ፣ ቁራሽ ተቸግሬ ሳይረዳኝ፣ እህቱን ሳይረዳ፣ የዘመድ ለቅሶ በልቶ፣ ከዘመድ ተቆራርጦ ማንም ሳያስበው በድንገት ሞተ። ሲሞት ተደወለለኝ፣ መጥቼ ቀበርኩት። የማህጸን ማሟሻዬ፣ የበኩሬ ነበር፣ ሙት አይወቀስም ይሉኛል፣ እኔ ግን ስወቅሰው እኖራለሁ።" አሉኝ በእንባ ብዛት የሞጨሞጨ አይናቸውን በአዳፋ ነጠላቸው ጫፍ እየጠረጉ።
"አይዞዎት እናቴ! በርታ ይበሉ! እርሱስ ቢሆን ይሄ ይመጣል ብሎ አለች አሰበ?! ያው ህይወት ሩጫ ናት፣ ምናልባት አልሞላ ብሎት..."
አላስጨረሱኝም።
"እድሜዬ ካለቀ፣ መቃብሬ ከተማሰ ብር አውርሶኝ፣ የልጅነት ፍቅሩን ነፍጎኝ፣ መኖሬን እንድጠላ አድርጎኝ ሞተ። በህይወት መኖሩ ብቻ መጽናዬ ነበር። ልጄ እናት አለችህ?!"
"አዎን እማ!"
"ዛሬን ጠይቃት፣ 'እንዴት አደርሽ' በላት። ሞት መምጫው ስለማይታወቅ ለነገ ምንም አታሳድር ልጄ። ልጄ ሲለፋበት የኖረውን፣ እኔን ያስተወውን ብሩን ወረስኩ፣ ፍቅሩን ግን ሳያወርሰኝ ሞተ። እኔ እንደምወድደው አውቃለሁ እርሱም ያውቃል፣ ወጣትነቴን ሰውቼ ያለአባት አሳድጌዋለሁ። እንደሚወድደኝ ሳያሳየኝ፣ እንደሚወድደኝ ሳላውቅ ሞተ" አሉኝ።
                               ****
የውርስ ገንዘቡን አካፍያቸው እንደጨረስኩ ከጓደኞቼ ጋር ዱባይ ሄጄ ልዝናና ከቆጠብኩት ብር ወደ ላይ ግማሹን አውጥቼ ለእናቴ ከላኩላት በኋላ ስልክ ደውዬ "እማ በዓል አብሬሽ ነው የማከብረው፣ ለበዓል ጨምርልኝ ያልሽኝን ብርም አስገብቼልሻለሁ፣ አወድሻለሁ እማ!" አልኳት።
ባልተለመደ ባህሪዬ የተገረመችው እናቴ "ምን ነው ጥልዬ በቀን መጠጣት ጀመርክ እንዴ?!" ስትል ጠየቀችኝ።
እንደምወዳት የምነግራት ሞቅ ሲለኝ ብቻ ስለነበረ አልተቀየምኳትም።
                           •••••
ሐሳብ ወለድ ታሪክ!

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Tilahun Girma Ang