Get Mystery Box with random crypto!

የምወድደው አለቃዬን ዛሬ አገኘሁት፣ ከዓመታት በኋላ። ያለፈውን ጊዜ አንስተን እንደ አዲስ ተሳሳቅ | ወግ ብቻ

የምወድደው አለቃዬን ዛሬ አገኘሁት፣ ከዓመታት በኋላ። ያለፈውን ጊዜ አንስተን እንደ አዲስ ተሳሳቅን። በተለይ የሚከተለውን ገጠመኜን።
*
ባንክ ተቀጥሬ አመት ያህል እንደሆነኝ አንድ እሁድ እለት ከጓደኞቼ ጋር ኳስ ለማየት ከቤት ወጣን። ይሁንና ኳስ እያየን ድራፍት እየጠጣን የነበርን ጎረምሶች ባላሰብነው ሁኔታ በከተማው የሚገኙ አንድ ባለሀብት ባስወረዱልን ውስኪ እስከ እኩለ ሌሊት ስንራጭ አመሸን።

ጠዋት ላይ አንድ ጓደኞዬ ቤት ስነቃ ፣ እራሴን መሸከም አቅቶኛል። ቤቱ በመጠጥ ሽታ ተሞልቷል። በእርግጠኝነት በእዚህ መልኩ ሥራ መሄድ እንደማልችል ስለገባኝ ወደ አለቃዬ ስልክ ደውዬ...

"ዘመድ ስለሞተ ለመቅበር ወደ ገጠር እየሄድኩ ስለሆነ ፍቃድ ፈልጌ ነበር..." ስል ፈቃድ ጠየቅኩ።

ተፈቀደልኝ።

መሀል ላይ ሌላ መስሪያ ቤት የሚሰራ ጓደኛዬም ከእንቅልፉ ነቅቶ ወደ ቢሮው ደውሎ ለቅሶ ገጥሞኛል በማለት ሥራ ካስፈቀደ በኋላ የእኔን ጠየቀኝ።

"እንዲህ ሀንጎቨር ሳይለቅቀኝ ሥራ ገብቼማ የመጠጥ ሽታ ስጋብዛቸው አልውልም። እኔም አለቃዬ ጋ ደውዬ ዘመድ ሞቶብኛል ብዬ ዋሸሁ። ጌታ ይቅር ይበለኝ!" አልኩት።

"እኔማ አሁን ላይ ዘመዶቼን በሙሉ ጨርሼ በጎረቤት ሞት ምናምን ማስፈቀድ ጀምሬአለሁ" አለኝ። ተሳሳቅን።

ይሁንና እየተሳሳቅን ሰዐት ለማየት ስልኬን ሳነሳ ሳላውቅ ነክቼው ኖሮ አለቃዬ ጋ ደውሎ እየቆጠረ አገኘሁት። በእርግጠኝነት ንግግራችንን ሰምቷል። ቆሌዬ ተገፈፈ፣ መሬት ተከፍታ እንድትውጠኝ ተመኘሁ። ነግቶ አለቃዬን እንዴት ፊቱን እንደማየው ሲጨንቀኝ ዋለ፣ ማታም በሐሳብ ስገላበጥ፣ እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር ነጋ።

በማግስቱ ጭንቀት እየተጫጫነኝ፣ ልቤ እየደለቀ፣ አንገቴን ደፍቼ ወደ ምሰራበት ባንክ ሄድኩ። አለቃዬ እንደወትሮው በጠዋት ቢሮ ገብቷል። በጭንቀት እንደተዋጥኩ ፊቴን ከስክሼ ይቅርታ ለመጠይቅ ወደ እርሱ ሄድኩ።

ልክ እንዳየኝ ፊቱ ከንዴት ይልቅ በፈገግታ እንደተሞላ "ቀብር ደረስክ?!" ሲል ጠየቀኝ። ዝም አልኩ። ከፊቴ ላይ መሳቀቄን አንብቦ ነው መሰለ የእኔን ምላሽ ሳይጠብቅ...

"አይዞህ! አትጨነቅ። እኔም የሆነ ጊዜ ላይ እንዳንተው ጎረምሳ ነበርኩ። እረዳለሁ። ሌላ ጊዜ እንዳትዋሸኝ። አሁን ወደ ሥራህ ሂድ" አለኝ።
***

@wegoch
@wegoch
@paappii