Get Mystery Box with random crypto!

ጃሃ . . . ፀሀፊ እንኳ አልነበርኩም... ነገር ግን ይሁዳነቴን አምኖ የሀጢያት ባልደረባዬ የሆ | ወግ ብቻ

ጃሃ
.
.
.
ፀሀፊ እንኳ አልነበርኩም... ነገር ግን ይሁዳነቴን አምኖ የሀጢያት ባልደረባዬ የሆነኝ ሰው ያጋራኝን ታሪክ እውነት እና ውሸትን ባንድ መደርደሪያ ላይ አስቀምጦ በግማሽ ብርጭቆ አረቄ ከሚጠፋ እኔነቴ መሀል ተራ ሰጥቼው ልሰድረው አልፈለኩም። እርግጥ ፊያሜታን በዓሉ የገለፃትን ግማሽ የአዳም ተባረኪን እሩብ ልገልፅለት አልችልም እንደ ዴዝዴሞናም እያጎን ፈጥሬ ኦቴሎዋን አላሳጣለት ይሆናል። ቢሆንም የልጅነት ልቤ የግጥም ዛሩ ወጥቶለት የቄሳርን ለቄሳር ግጥምን ለነበእውቀቱ ብሎ እንደ ጲላጦስ እጁን ታጥቦ ብዕር ጥሎ ሲጋራ ካነሳ  ከዓመታት በኋላ እህ ማለት አሰኘኝ። ......"እኔ ምልህ"አለኝ ሲጋራ አጫጫሴን በትኩረት ካየ በኋላ ሲጋራ ምን ያህል እንደምወድ ቢያውቅም ምክንያቴን ግን ጠይቆኝ አያውቅም እኔም መልስ አልነበረኝ።

"እኔ ምልህ የውሀ አይነት ስሜት ታወቃለህ?"
ማለት የተረጋጋ ማለትህ ነው? አልኩት
"NO መልክ የሌለው ይሄ ነው ልትለው የማትችለው ዓይነት"
"እኔንጃ እእእ....." ምን እንደምመልስለት እያሰላሰልኩ ወገቧ ላይ የደረሰችውን ትንባሆ አቀበልኩት ጨዋታችን እንዲቋረጥ አልፈለኩም ሲያወራ ደስ ይላል። ታሪኩ ያለፍኩበትን ያስታውሰኛል። ሀሳቡ ዞሬ ላላየው የማልኩትን ትናንቴን እንድቃኘው ደጀን ሆኖኝ ያውቃል።

"ስለሷ ሳስብ ውሀነት ነው የሚሰማኝ" አለ ሁለቴ ስቦ ሲጋራውን ቂጡ ጋር ካደረሰ በኋላ......."በማይታይ ውበት..በሚረብሽ ፀባይ....ሴትነት ባልጎላበት ለዛ የተደበቀ ውብ እና አሳዛኝ ነብስ እንዳላት የተረዳው ቀን ክርስቶስ ሳይመጣ ይሁዳን ለመሆን ለምን ቸኮልሽ? ልላት አስብና "ዋ ይሄን ግራ የገባው ወሬህን እዛው" የሚል መልሷ እንደሚከተለኝ ስለማውቅ መልሼ እተወዋለሁ ።ሁሌም እንዲ ናት ጥያቄው ካልገባት ወይም መመለስ ካልፈለገች ቁጣ ይቀናታል።እና ስለሷ ባሰብኩ ቁጥር ስሜቴ ውሀ ይሆንብኛል።
አንዳንዴ ወድጃቸው ከነበሩት ሴቶች ዝርዝር ውስጥ እፈልጋት እና ከግርጌ አካባቢ እንኳ ሳጣት ግራ እጋባለው።

እንደምጠላትም ማመን አልችልም። መቼም ማፍቀሬን በግላጭ አግኝታ ከእግር ጥፍሬ እስከ ራስ ፀጉሬ ያለተቀናቃኝ መጣ ከጣለችው ይሁዲት ጋር ላወዳድራት አልችልም። ብቻ ጎኗ ቆሜ አለው ማለት በከበባት ጦር መሀል ገብቶ መፎከር ያምረኛል። እንድትስቅ እፈልጋለው...ጥሎባት ደሞ አትስቅም ፈገግ ካለችም ከስንት አንዴ ነው። የልጅ ነፍስ አላት ..ንፁህ መዓዛ ያለው..የሚጣራ አይነት.......
ሳያት ይቀለኛል.. ለብ ባለ ውሀ ሻወር የመወሰድ አይነት የመታደስ ስሜት ይሰጠኛል። ለስላሳ ሙዚቃ የመስማት ያህል እርጋታ ይከበኛል በናት ጉያ ስር እንደመወሸቅ ያለ ድፍረት ማንም የማይደርስብኝ ያህል ልበሙሉ ሆናለው ።
ስሰማት የአለም እውነት ሁሉ ውሸት ይሆንና ሀቅ ከሷ ወዲያ ላሳር ስል እውላለው። የፍቄ ትረካና የጂጂ ዘፈን ለጆሮዬ ያስጠላኛል ። ማርያምን አልወዳትም!!! ማታ ስገባ አላልማትም ሳያት ልቤ ምቱን አይቀይርም አትናፍቀኝም ላያት አልራብም። ሳያት ግን በሰራችው የሾክ አጥር ስር ሾልኬ ማራኪ ነፍሷን ሳይ እውላለሁ እገረማለሁ እራሴን እረሳለሁ ...እጠፋለሁ አ.ይ.ገ.ባ.ት.ም እላለው... ከዚ የተሻለ ይገባታል... ያለችበትን ቦታ የከረመችበትን ህይወት ቃኘውት አዲስ አልሆነብኝም የኔ አለም ውሰጥ ያለች ይመስለኛል ..አይገባትም ነበር በፍፁም!! ...."
በመጨረሻ ቃሉ ማብቂያ ራሴን አሰብኩ ዘመን ወደ ኋላ መለሰኝ እሷን የኔን አሰብኳት ወዲያው አዲስ ሲጋራ ለኮሰ ።ተቀበልኩት አይገባውም ነበር.....
ምንአልባት የሚገባው ......

@ wegoch