Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል ትምህርቷን ስትጨርስ ሸጋ ውጤት አመጣች!! አዲስአበባ ዩንቨርስቲ ለትምህርት ተመደበች እና የ | ወግ ብቻ

ክፍል ትምህርቷን ስትጨርስ ሸጋ ውጤት አመጣች!! አዲስአበባ ዩንቨርስቲ ለትምህርት ተመደበች እና የ6 ዓመት ጨቅላ ልጃችንን ትታ መምጣት ግድ ሆነ!! ገና ከወራት ግን የልጇ ናፍቆት አቅቷት ተመልሳ መጣች። እሷ ከህልሟ አጓጉል ከምትሆን ምናባቱ ያገኘሁትን ሰርቼ እኖራለሁ ብዬ ልጄን ምሽቴን ይዤ አዲስአበባ ገባሁ!! ስራውንም ሳላማርጥ እየሰራሁ ባጀሁና ትንሽ ስደላደል እምዬንም አመጣኋት እኔጋ!! እንዳያልፍ የለም መቼም እንዴትም እንዴትም እሷ ተመረቀች። ይሄኔ እሷ ናት ይሄን ስራ በሰው አገኘሁልህ ብላ ደሳለኝጋ ያገናኘችኝ። እሷ ተመርቃ ከፍ ያለ ስራ ይዛ ከፍ ካሉ ሰዎች ጋር መዋል ስትጀምር ከእኔጋ መኖሩን እየተጠየፈችው መጣች። የምለብሰው አይጥማት ፣ አካሄዴ አይጥማት ፣ የማወራው አይጥማት …… ትምህርት ሚሽቴን ቀየራት ….. ትምህርት ሚሽቴን ነጠቀኝ!!» አለ ከደረቱ ቀና እንደማለት ብሎ በቁጭት ነገር የሆነ መፅሃፍ ትረካ ነገር በሬድዮ እየሰማሁ ያለሁ ነው እየመሰለኝ ያለው።


«ኋላማ ትዳራችን እንደማይሆን ሆነ። አቶ ደሳለኝ ጋር በጥበቃ ሰርቼ የማገኛት ገንዘብ ለሚስቴ ከራሷ ደመወዝ ጋር ተደምሮላትም የሚበቃትን ኑሮ አላኖር አለኝ። ኋላ ላይ አቶ ደሳለኝ በሷ ጥቆማ የግሉ ጠባቂ አደረገኝ። መድሃንያለም በሚያውቀው የዚህን ጊዜ ሁለቱ የሆነ ነገር ይኑራቸው የማውቀው የለኝም!! አይኔ ስር የሚሰሩትን ቆሻሻ ስራ አያለሁ!! ንፁህ ሰው አግተው ሲዝናኑ አያለሁ!! ቤቴን አቆም ብዬ አንገቴን ደፋሁ። ሰውየው <ልዩ ጠባቂዎቼ > የሚላቸው አሉት!! ስራው ጥበቃ አይደለም! ቆሻሻ ስራዎችን መስራት ነው!! የሚፈልገውን ሰው ከመሰለል እስከማገት ፣ መረጃ መስረቅ ፣ …… እነርሱን ተቀላቀል ሲለኝ አሻፈረኝ አልኩ። ሚሽቴ ብዙ ብር የሚያስገኝልኝን ስራ እንቢ ማለቴን ደሳለኝ እንደነገራት ነግራኝ ስትቆጣ የዚያኔ እምነቴ ሙሉ ስለነበር አልጠረጠርኳትም!! ብሩ ቢያስፈልጋት ነው ብዬ ስራውን ተቀበልኩ!! እሷን ካስደሰተልኝ እና በሷ ፊት ሞገስ ከሆነኝ ምናባቱ ብዬ ገባሁ!! ብዙ ወዳጅ አፈራሁ!! ስለከተማ ሰው ብዙ አወቅኩ!! እንዲያ ህሊናዬን አቆሽሼ ብዙ ብር ባመጣላትም ሚሽቴን አላቆየልኝም!! ፍታኝ አለችኝ!! በግድ ይዤ ላቆያት አልችል ለቀቅኳት።»

«ትወዳት ነበር!»

«ሚሽቴ አይደለች እንዴ? ቤቴ እኮ ናት የልጄ እናት! እንዴት አልወዳት?» አለኝ እንደመቆጣት ብሎ

«አይ እንዴት ሆነልህ ብዬ ነው! ባለፈው ሳያችሁ የሌላ ሴት ሚስት ሆና ምንም የመሰለህ አትመስልም ነበር።»

«ያልፋልኮ! ያልፋል! ቅናቱም ፣ ህመሙም ፣ እህህ ማለቱም ያልፋል!»

«እና ደሳለኝን ካገባችው በኋላ እሷን እያየህ ስራ እዛው እንዴት ቀጠልክ?»

«እኔና እሷ ከተፋታን ኋላ ትንሽ ቆይቶ እምይ በጠና ታመመችብኝና ለህክምና 10 ዓመት ብሰራ የማላገኘው ፍራንክ ተጠየቅሁ!! አቶ ደሳለኝ ብሩን ሊያበድረኝ እና በምትኩ ለ3 ዓመት የታዘዝኩትን ልሰራ ያቀረበልኝን ሀሳብ ለማለፍ ምርጫዬ የእምዬ ህይወት ነበርና ፈርሜ ገባሁበት!! እምዬን አዳንኩበት እኔ የማልወጣው ሀጥያት ውስጥ በየቀኑ ሰመጥኩ እንጅ!! ከዚያማ የልጄ እናት የአለቃዬ ሚስት ሆና መጣች። ትቼ አልሄድ ቃሌ ፣ ፊርማዬ ….. አልቀመጥ ሽንፈት ፣ ቅናት ፣ መከዳት ፣ መታለል ፣ መዋረድ አንገበገበኝ። ያልፋል አልኩሽ አይደል? አለፈ። እሷን ወይ አብራኝ እያለች አላውቃት ይሆን ወይ ከትምህርቱ በኋላ ተቀይራ : ጭራሽ የማላውቃት ሰይጣን ሴት መሆኗን አለቃዬ ስትሆን አወቅኩ። ለእኔ እንዲያ ብትሆንም ለልጄ ወደር የሌላት እናት ናት!! ልጄ በቋሚነት እኔጋ ብትሆንም ከአርብ እስከእሁድ እሷጋ ትሆናለች። አብረሽኝ ሁኝ ብትላት ልጄ እኔን መረጠች» አለ ኮራ ብሎ በፈገግታ ቀጥሎ

«አንቺጋ ስቀጠር ያገናኘን ሰውዬ ያንቺ ወዳጅ ቢሆንም በድብቅ የእነርሱ ወዳጅ ነው!! ያው ዘበኝነት ገብቼ የፈለጉትን መረጃ እንዳመጣ ነበር። ልጄ የታመመች ጊዜ » ብሎ ጊዜውን በማስታወስ ነገር ፍዝዝ አለ። «ልክ ያሁን ያህል አስታውሳለሁ። በረንዳው ላይ ተቀምጠሽ!

«ቤተሰብ ነኝ ብዬ ከቀበሌ የሆነ ወረቀት እናሰራ እና የእኔ ከሆናት የኔን ኩላሊት እሰጣታለሁ!» ስትይ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደስራዬ ሳይሆን እንደሰው ያየሁሽ!! የዚያኔ ነው ለምን እንደሆን እንጃ ስላንች ማወቅ ናፈቅኩ። እናቷ ያንች ኩላሊት መስማማቱን ስነግራት አይሆንም አለች። ፈጣሪ ደግ ነው ሌላ ሰው ተገኘና ልጄ ዳነችልኝ! በሰው በሰው ሳጠራ ማን እንደሆንሽ ደረስኩበት። ስራዬን ልልቀቅ ካልኩሽ በኋላ ለእነርሱም ሄጄ ሌላ ስራ እንዲቀይሩልኝ ጠየቅኳቸው። በእኔ ምትክ እንዲገባ አናግረሽው የነበረውን ሰውዬ እነርሱ ናቸው የላኩልሽ!! የሰው ተፈጥሮ ያልፈጠረበት የሰይጣን ቁራጭ አረመኔ ነው!! ምንም እንኳን የምጠላው ጎሳ ፣የወንድሜ ገዳዮች ልጅ ብትሆኝም ለልጄ ስትይ አካልሽን ልትሰጭኝ ስስት አልነበረብሽም እና ለዚያ አውሬ አሳልፌ ልሰጥሽ አልሆነልኝም!! መልሼ ሀሳቤን አንስቻለሁ እሰራለሁ በቃ ብዬ ተመለስሁ!!» ብሎ ነግሮኝ እንደጨረሰ ነገር ዝም አለ።

«ከዚያስ!»

«ከዚያማ ምን የማታውቂው ቀረ?»

«ይቀራል እንጂ! መች ነው የወደድከኝ? የተመታሁ ቀንኮ ግን ትተኸኝ ልትሄድ ነበር ለነሱ ትተኸኝ!»

«መች እንደወደድኩሽ ምኑን አውቄው? ስገቢ ስትወጭ ስትገለምጭ ስትሰድቢኝ!! አንዳንዴ ነገረ ስራሽ አፍሽ እንጅ የከፋ ልብሽ ደግ መሆኑን ሲነግረኝ አላውቅም!! እነርሱ የሚፈልጉትን መረጃ ሁላ አግኝቼ ለእነርሱ አሳልፌ ልሰጥሽ አቃተኝ!! ጥላሽን የማታምኝ ሴት እኔን ግን ከነጭርሱ አለመጠርጠርሽ አሳዘነኝ!! እንጃ ካስታወሽ የሆነ ቀን ለሊት ገብተሽ በር ስከፍትልሽ <አንተ ግን ደስተኛ ነህ?> አልሽኝ።»
ብሎ ፈገግ አለ። አስታወስኩት።

ትንሽም ቢሆን ደስታዬ የነበረው ከእሙጋ በማሳልፈው ጊዜ የነበረ ጊዜ እሷ የማያገባት ነገር የመቆስቆስ ሱሷ አላስቀምጥ ብሏት ለአምስተኛ ጊዜ የታሰረች ቀን ነው። (እኔ እስር ቤት ለ6 ዓመት እያለሁ እሷ ሁለቴ ገብታ ወጥታለች። ስትገባ አብረን ጊቢውን እናምሳለን። ከጋዜጠኝነቷ ባሻግር ታቱ መስራት በልምድ ተምራለች። እስር ቤት ውስጥ እንኳን ዘመናዊ ንቅሳት ልትነቀስ ፀጉሯን ከሁለት ጉንጉን የዘለለ የማትሰራ የገጠር ልጅ ሁላ ሳትቀር በጋዜጠኛ ምላሷ አዋክባ አሳምና ትነቅሳታለች። የጀርባዬን እና የቂጤን ንቅሳት ግማሹን መጀመሪያ የገባች ጊዜ የተቀረውን ቀለም ያልደረሰው ቦታ እየፈለገች  ሁለተኛ ስትመለስ  የነቀሰችኝ እሷ ናት።) የዛን ቀን መታሰሯን ሰምቼ የበረደው ልቤን ይዤ ስባዝን አምሽቼ ስገባ ጎንጥ ከእንቅልፉ ነቅቶ በር ከፈተልኝ። በረንዳው ጠርዝ ላይ ተቀምጬ እያየሁት በህይወቱ ምንም ግድ የሚሰጠው አይመስልም ነበር።

«አንተ ግን ደስተኛ ነህ?» አልኩት በመገረም እያየሁት! እንደገመትኩትም ቁልል ብሎ

«ፈጣሪ ይመስገን!!» አለኝ

«ምን ማለት ነው ፈጣሪ ይመስገን? መልስኮ አልሰጠኸኝም!! ነህ አይደለህም? ነው ጥያቄው ! ነኝ ወይም አይደለሁም! ነው መልሱ»

«ምን ለየው!! ፈጣሪ ይመስገን ማለቴ ደስተኛ በመሆኔም አይደል?» ብሎ አሁንም መልስ ያልሆነ መልስ ይመልስልኛል።

«አንተ ግን መቼ ነው ቀጥተኛ ወሬ የምታወራው? ምናለ አሁን ነኝ ወይ አይደለሁም ብትል!! ምንህ ይቀነሳል?»

«እሽ ካሻዎት! አዎን ደስተኛ ነኝ!! ምነው? እርሶ ደስተኛ አይደሉም እንዴ?» አለኝ መልሴ የጨነቀው አይመስልም። እኔ ግን ውስጤ መከፋቴ ሞልቶ ስለነበር መተንፈስ ለማልፈልገው ሰው ገነፈለብኝ።