Get Mystery Box with random crypto!

..... ለእኔም እኮ አይገባኝም፤ ቆይ በሕይወታችን የምንፈልገው ትልቁ ነገር ፍቅር ነው አይደል? | ወግ ብቻ

.....
ለእኔም እኮ አይገባኝም፤ ቆይ በሕይወታችን የምንፈልገው ትልቁ ነገር ፍቅር ነው አይደል? ያውም ጥልቅና ነጋሪ የማያስፈልገው እንዲው በአይን ብቻ የሚገባን? ይህንን የሁሉን መሻት እኮ ነው የኔ ሆኖ ያገኘሁት፤ ታዲያ ለምንድነው ማመሰገኑ የቸገረኝ? ለምን ይሆን ልቤን የጭነት ያህል የሚከብደው? ለምንድነው አሁንም ያልሞላ ክፍተት እንዳለ የሚሰማኝ?

ያኔ....
እሱ ወላጆቹን በሞት አጥቶ በሀዘን የተሰበረበት ጊዜ ነበር፤ በዛ ሁሉ ስቃይ ውስጥ ሆኖ የኔን አብሮነት ሲሻ የራስህ ጉዳይ የምልበት አቅም አልነበረኝም ግን ያውቀዋል አፍቅሬው አልነበረም።
በቆይታ እሱም ሀሳቡን የሚቀይር እኔም ልቤ የፈቀደውን የማደርግ መስሎኝ ነበር። ጊዜያት ባለፉ ቁጥር የሱ ፍቅር ሲጨምር እኔ ለሱ ያለኝ ክብርና የጓደኝነት መውደድ እንዳለ ከመዝለቁ ውጪ ልቤን ለፍቅር ማስረከብ አቃተኝ።

ራሴን እኮ እጠይቀዋለው "ያልወደድሽለትን አንድ ነገር ጥቀሺ" ብባል አፌ ይተሳሰራል እንጂ ይህ ነው የምለው አንዲት ሳንካ እንኳን የለበትም፤ ግን አላፈቀርኩትም።

ምንም ቢጠየቅ በሚገርም ብስለት ነገሮችን ያብራራል፤የእይታው አድማስ፣ የምልከታው ጥግ "ለካ ይህም አለ እንዴ?" እንዳስባለኝ ነው።

ቁጥብ ነው እናም ኮስታራ፣ ስክን ያለ፣ ልክ እንደ ውሀ የሚጋባ አይነት የእርጋታ መንፈስ ያለው፤ የልጅ አዋቂ።
በፊት በፊት ሰዎች የዚህ አይነት የስብዕና ጥልቀት የሚኖራቸው ከህይወት ብዙ ሲቀስሙ ይመስለኝ ነበር፤ እሱ ባለበት የእድሜ ልክ እንዴት ላስበው እችላለው?
በዚህ ለይ ደግሞ አፍቃሪነቱ፣ አይኑ ለይ የማየው መውደድ፣ አይን ያዝ ከሚያደርግ ግርማ ሞገሱ ጋር ልብን የመቆጣጠር ሀይል አለው፤ታዲያ እኔን
ማሸነፍ ለምን ተሳነው?

ብዙ ጊዜ ሁሉን እርግፍ አድርጎ ስለመተው እና ብቻዬን ስለመሆን አስባለው፤ እሱ ያንን እንዳደርግ አይፈቅድልኝም እንጂ።
"ራሴን አጠፋልሽና ትገላገያለሽ" ያለኝን ባሰብኩት ቁጥር ልቤ ይጨነቃል ለነገሩ እንደዛ ባይለኝም እንኳን ያንን ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል እርግጠኛ ነኝ፤ ለሱ የመኖሩ ምክንያት ነኛ!
አንዳንዴ "ቆይ መውደድ ያልቻልኩት ሁሌም ቅርቤ ስለሆነ በእጅ የያዙት ሆኖብኝ ነው? ሳጣው እንደ እሳት ሊያንገበግብኝ?" ብዬ አስባለው።
ነገር ግን ተጣልተን በቆየንባቸው ጊዜያት ከፋኝ እንጂ ያንን ፍቅር ግን አልታመምኩትም።

አከብረዋለው፣ ለሱ ያለኝ መውደድ ከልብ ነው፤ አንዲት እንቅፋት እንኳን በህይወቱ እንድታጋጥመው አልፈልግም፤ ሳቁ ነው የሚናፍቀኝ፤ የወደደውና የሚያስፈልገው እንዲሆንለት ነው ምኞቴ፤ ይህን ለመሰለ ስብዕናው መቼስ ቢያንስበት እንጂ አይበዛም።

ፍቅር ግን ተሰርቶ አይመጣም አይደል? "ይህንን ሰው መውደድ አለብኝ!" ማለት ነበረብኝ? ብልስ ይሆንልኛል?፤ ነው ወይስ ልክ እንደ ተሰማኝ ማስመሰል አለብኝ? ማንም ሰው እኮ ከራሱ አያመልጥም።
እንዳልወደድኩት ማሰቡ ለራሱ የጥፋተኝነት ስሜት ይፈጥርብኛል ግን እውነታው እሱ ነው ካልሆነ ከራስ ጋር ድብብቆሽ ይሆናል።
ፍቅር ደግሞ ይሰጠናል እንጂ በስራ አናመጣውም፤ በማንቆጣጠረው ልክ ውስጣችንን ሞልቶት እናገኘዋለው ያኔ ከዛ ሰው ጋር መሆን አማራጭ የሌለው ብቸኛው ውሳኔያችን ነው።

ግን ማናችን ነን የተሳሳትነው?
ያ ጥልቅ ስሜት ሳይሰማኝ ለሱ ስል ባላመንኩበት ህይወት ውስጥ እየዳከርኩ የራሴን ስሜት ለማዳፍን የምሞክረው፣ በገዛ ህይወቴ ለይ የመወሰን ስልጣኔን የተነጠኩት፣ ደስተኛ እንደማልሆን እያወኩኝ በተቀመረልኝ አብሮነት ውስጥ ማለፍ ግድ የሆነብኝ እኔ? ወይስ.....
ያለ ልክ የሚያፈቅራት ሴት እሷ ጋር ያ ስሜት እንደሌለ እያወቀ እንኳን መውደዱ ያልቀነሰበት፣ ከሷ ጋር ለመሆን የሷ መኖር እንጂ መልካምነቷ ግድ የማይሰጠው፣ የነገው ህይወቱ ከሷ መኖር ጋር የተሳሰረበት፤ እውነተኛው አፍቃሪው እሱ?
ማናችን ነን ልክ?.....የቱስ ጋር ነው የተሳሳትነው?
.
.
ለዚህ እኮ ነው... ለኔም አይገባኝም የምለው።

@wegoch
@wegoch
@paappii

By mahlet