Get Mystery Box with random crypto!

ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ ማት እና ግሩምጋ ደወልኩ። 'እግዚአብሄር ይመስገን!' ካለኝ በኋላ ወዲያው | ወግ ብቻ

ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ ማት እና ግሩምጋ ደወልኩ።
"እግዚአብሄር ይመስገን!" ካለኝ በኋላ ወዲያው "መጣሁ!" አለኝ ማት ሳልነግረው ይገባው የለ? ግሩም ፈነጠዘ። ሆስፒታል ስደርስ ነቅታ ሰውነቷ ላይ ተሰካክተው የነበሩት ማሽኖች ተቀንሰው ቅልል ብሏታል።

"ልጄስ?" ነው ያለችኝ ገና ስታየኝ መልኬን ታውቀዋለች ማለት ነው? ወይስ ገምታ ነው ብዬ እያሰብኩ

"ትምህርት ቤት ነው!" አልኳት ባባ ትምህርት ከጀመረ ሁለት ሳምንቱ ነበር። ዶክተሩ 'ከዚህ በኃላ ልትነቃ የምትችልበት እድል እየጠበበ ነው።'ያለኝ ጊዜ ነው ትምህርት ቤት ግማሽ ሴሚስተር ላይ ያስመዘገብኩት። ዝም አለች። ከዛ ደጋግሜ "እንዴት ነሽ አሁን?" የምላት እኔ ሆንኩ። ማት እና ግሩም ሲገቡ ማናቸው በሚል ስታያቸው ማንነታቸውን ነገርኳት።

"ቤተክርስቲያን እየሄድኩ ነበር።" አለች ለግሩም በሚመስል አነጋገር።

"ይቅርታ በፍፁም አላየሁሽም ነበር!" አላት ቀጥሎ ከአፏ የሚወጣውን ለመስማት መጓጓቱ እያስታወቀበት።

"ከእጄ ላይ ሳንቲም ወድቆ እሱን ላነሳ ነበር!የመኪና መንገዱ መሃል መድረሴንም አላስተዋልኩትም ነበር።" አለች አሁንም ግሩምን እያየች .......ያቺ ያነሳኋት የአንድ ብር ሳንቲም ትዝ አለችኝ የዛን ቀን የቦርሳዬ ትንሽዬ ኪስ ውስጥ እንደከተትኩት ነው።

"የምሰራበት የነበረበት ሱቅ ባለቤት ስራ ልቀይር ነው ብሎ ሱቁን ዘግቶት ነበር። ስራ እየፈለግኩ እጄ ላይ የቀረው አንድ ብር ብቻ ነበር።" እንደነገሩ ቀለል አድርጋ እያወራችው ግን የሚጋባ መከፋት ነበረው ድምፅዋ

"በአንድ ብር ምን አደርግበታለሁ? ልጆች ሆነን ማሳደጊያ እማሆይ ወይኗ የምንላቸው እናት ነበሩ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያነቡልን ስለአንዲት ሴት ያነበቡልንን ሁሌ የማስታውሰው ነበር:: በሀገሩ የሚበላ ጠፍቶ ድርቅ በነበረበት ዘመን የቀራትን ትንሽዬ ዱቄት በውሃ ለውሳ ጋግራ ለነብዩ ስላበላች ሴት ..... ቃል በቃል አላስታውሰውም!ያላትን ለእግዚአብሔር አገልጋይ ሰጥታ እጇን አጣጥፋ ሞቷን ስለጠበቀች ሴት ........ ያለሽን የመጨረሻ እንጥፍጣፊ አልሰሰትሽምና ብሎ አምላክ ስለባረካት ሴት ....." ብላ ዝም አለች። የሁላችንንም ፊት ተራ በተራ ካየች በኃላ

"አላዋቂ ናት ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። የማደርገውን ሳጣ ያስታወስኩት ይሄን ታሪክ ነበር። በዛ ለሊት ተነስቼ ቤተክርስቲያን የምሄደው ያቺን የቀረችኝን አንድ ብር ለቤተክርስቲያን ሰጥቼ ልጄንም እኔንም እንደፈለግክ አድርገን ልለው ነበር። ከዛ ውጪ ምን ማድረግ እንደነበረብኝ አላውቅም ነበር። የማውቀው፣ ቸገረኝ የምለው ዘመድም ጓደኛም የለኝም ነበር።" ብላ አሁንም ዝም አለች። ማንም ምንም ለማለት አቅሙም ቃሉም አልነበረውም። ጉንጭሽ ላይ ካልተደፋሁ ብሎ መጣሁ መጣሁ የሚል እንባዬን መታገል ጀመርኩ። "አይዞሽ፣ እኔን!" ልላት እፈልጋለሁኮ ግን ቃል ከአፌ ከመውጣቱ በፊት እንባዬ እንደሚቀድም ስለገባኝ የባሰ ሆድ ላስብሳት አልፈለግኩም። ከሆነ ደቂቃ በኋላ

"አይዞሽ! ከአሁን በኋላ ቤተሰብ አለሽ! " አላት ማት እሷ ወደ እኔ አየች። ያን እንዳረጋግጥላት ይሁን አልገባኝም። የምለው ግራ ገባኝ እና እጇን ያዝኳት

"ከፈለግሽ ባባን በኋላ ከትምህርት ቤት ሲወጣ ላመጣው እችላለሁ!" ስላት ሳግ እያነቃት

"እሺ!" አለችኝ። ባባን እንደምትወስድብኝ ሳስብ የሆነ አንጀት የሚቆርጥ ህመም አለው ግን የመተው ዓይነት ህመም አይደለም...... ይከፋኛል ብዬ ያሰብኩትን ያህል አይደለም:: ልክ የሆነ ስሜት ሳይሆነው ልክ የሆነ ነገር ....... የሆነ በህመም ውስጥ ፈውስ ያለበት ነገር......

ይቀጥላል.......

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke