Get Mystery Box with random crypto!

አታምጣ ስለው አምጥቶ ቆለለው #8 «ስትነቃ ውሳኔሽን ባትቀበልስ” አለኝ ማት። የግሩምን ጉዳይ በ | ወግ ብቻ

አታምጣ ስለው አምጥቶ ቆለለው #8
«ስትነቃ ውሳኔሽን ባትቀበልስ” አለኝ ማት። የግሩምን ጉዳይ በሽምግልና እንዲያልቅ መወሰኔን ስነግረው።
"አስቤዋለሁ ማትዬ ... ይህቺ ሴት ሱቅ ውስጥ ተቀጥራ ነበር የምትሰራው። የቤት ኪራይ ከፍላ ...ልጇን አሳድጋ ... የትምህርት ቤት ከፍላ .... ምን ዓይነት ህይወት የነበራት ይመስልሃል? ይህቺ ሴት አንድ ቀን የምትጎርሰው ብታጣ ሄዳ የምትጠጋበት ዘመድ እንኳን የላትም። ታዲያ ለዝህች ሴት የገጫትን ሰው በእስር ከማስቀጣት እና ለልጇ የወደፊት ህይወት ዋስትና የሚሆናት ተቀማጭ ገንዘብ ከማግኘት የቱ ይበልጥባታል?"
"እሺ ካሳው ምን ያህል ብር እንዲሆን ነው ያሰብሽው?"
"ለዛ ነው እኮ የፈለግኩህ! ጉዳዩን በቁም ነገር እንዲይዙት እፈልጋለሁ። የሽምግልና ሂደቱ በትክክል ይደረጋል። ሰዎቹ ሀብታም ነገር ናቸው። ጥሩ ሰዎችም ይመስላሉ! እናትየው ልጇ አይታሰርባት እንጂ ምንም ያህል ብንላት አታመነታም! ብቻ ለባባ የወደፊት ዋስትና የሚሆን ገንዘብ መጠን መሆን አለበት። ሽምግልናውን የሚይዙልን ሰዎች አዘጋጅልኝ! "
"እንደገባኝ ከሆነ ያሰብሽው ገንዘብ ትንሽ አይደለም። ባይስማሙስ? "
"ምንም ቢሆን በልጄ ጉዳይ እንደማልቀልድ ማወቅ አለባቸው።" ባባን 'ልጄ!' ብዬ መጥራቴን ያስተዋልኩት ማት ያንን የስስት ፈገግታውን ፈገግ ሲል ነው።
"እሺ መች እንዲሆን ነው ያሰብሽው?"
"ነገሩን እያሰነዳዳን ትንሽ እንቆይ። ማትዬ ትንሽ ልጠብቃት። ምንም እንኳን አሸናፊ ሃላፊነቱን ቢሰጠኝም፣ እሷም ስሜን ስትፅፍ አምናብኝ ቢሆንም ህይወቱ የሷ ነው። የሷ የወደፊት ነው። ምንም የሚያስቸኩለን ነገር የለም! ልጠብቃት!"
"እሺ አያድርገውና ብትሞትስ?"
"ውሳኔዬን የፈራሁት እሱን ሳስብ ነው። ያሰብኩት ገንዘቡ ለባባዬ እንዲቀመጥለት ነው። ራሱን ሲችል የሆነ ነገር ለመጀመር ይረዳዋል። እናቱን አይመልስለት ይሆናል። ቢያንስ ግን ለሆነ ነገር ይጠቅመዋል። ግሩም ቢታሰርም እናቱን አይመልስለትም። ግን ትልቅ ሆኖ ከገንዘቡ ይልቅ እናቴን ያሳጣኝ ሰው ቢቀጣልኝ ነበር የምፈልገው ቢለኝስ? ይቅር ባይለኝስ? ቢጠላኝስ?"
"እህቴ ያንቺ ልጅ ሆኖ አድጎ እንደሱ ይላል ብዬ አላስብም! ካንቺ ጋር አይደለም አድጎ አንድ ቀን አድሮ ያንቺ ልብ የማይጋባበትኮ አይኖርም! ትልቅ ሲሆን እንዳንቺ ይቅር ባይ፣ እንዳንቺ ጠቢብ፣ እንዳንቺ መልካም ነው የሚሆነው።"
"ሁሉም ልጆችኮ በእናታቸው አይወጡም!"
"ሁሉም ልጆች ግን እንዳንቺ ፍቅሯ የዓለምን ክፋት ሁሉ የሚያስረሳ እናት የላቸውም።"
"ባክህ እናት ሁሉ ለልጇ እንደዛ ናት።"
"ለልጇ አዎ! በዙሪያዋ ላሉ በሙሉ ግን አይደለችም። ልጆችሽ ለእነርሱ የምታደርጊውንና የምትሆኚውን ብቻ እያዩኮ አይደለም የሚያድጉት። በእያንዳንዷ ቀንሽ ለሌሎች የምታደርጊውን እና የምትሰጪውን ፍቅር ያያሉ። እነርሱም ሲያድጉ በደም ለተጋመዳቸው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁሉ ቅንና ፍቅር ሰጪ መሆን ትክክለኛው መንገድ መሆኑን ያውቃሉ። በልጅሽ ውስጥ ራስሽን አታዪም? "
"እኔእንጃ ማት አንዳንዴ እኔ እንደምትሏት ዓይነት ቅን ሰው ከሆንኩ፣ ሁሌ እንደምትለኝ ገራሚ ልብ ካለኝ ለምንድነው አምላክ ደስተኛ ሆኜ እንድኖር ያልፈቀደው?" አልኩት
ማለት የፈለግኩት የነበረው ግን ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ የወደድኩት ሰው ትቶኝ ሲሄድ ጥፋቴ ምን ነበር? ሙሉ ልቤን ሰጥቼ ፍርክስክስ ያለ ልብ መቀበል ፍራቻ ወንድ መልመድ ሸሽቼ ልጄን ብቻዬን ሳሳድግ የየትኛው ጥፋቴ መከር ነበር?
"የምትፈልጊውን አምላክሽን ለምነሽው ታውቂያለሽ?"
"አምላክ እኮ ነው። የሚያስፈልገኝን ከእኔ በላይ የሚያውቅ፣"
"እራሱ አምላክ ነው 'ጠይቁ ይሰጣችኋል አንኳኩ ይከፈትላችኋል' ያለው። ሳንጠይቀው በፊት የምንጠይቀውን ስለማያውቅ አይደለም። አምላክ የነፃነት አምላክ ስለሆነ በፈቃዳችን ነው የሚያደርግልን። ፈቃዳችንን ይፈልጋል። ባይሆን ኖሮ ስንቱን ልበ ድንጋይ እያጋጨ አይመልሰውም ነበር? ምክንያቱም ልኩና የሚያስፈልገው መልካም መሆን ስለሆነ! ግን ለምርጫችን ይተወናል። አምባገነን አይደለማ!"
"እንዴ? የምንፈልገውና የምንጠይቀው ሁሉኮ ልክ አይደለም። አንዳንዴ የማይበጀንን እንጠይቃለን። እርሱ ግን የቱ እንደሚበጀን ያውቃል።"
"እኔ የማምነው ለምሳሌ 'አምላኬ ሆይ ደስተኛ አድርገኝ!' ብለሽ ስትለምኚ ምናልባት ያንቺ ልመና ገንዘብ ሊሆን ቢችል እርሱ ደስታሽ ልጅጋ ከሆነ ያለው ልጅ ይሰጥሻል። የለመንሽው ደስታን ነውና ደስታሽን ታገኛለሽ። እኔ እንደዛ ነው የማስበው!"
"እና ስላልጠየቅሽ ነው ያልተሰጠሽ ነው የምትለኝ?"
"ያንቺ ከዛም ያልፋል እህቴ!" ሳቅ እያለ "አምጥቶ አልጋሽ ላይ ቢያስተኛልሽም ራሱ 'የእግዜር እንግዳ' ነው ብለሽ አልጋሽን ለቀሽለት ትሄጃለሽ! ቢሰጥሽም ለመቀበል ዝግጁ አይደለሽም።"
"ባል ነው የምፈልገው ወጣኝ?" አልኩት ፈገግ ብዬ። ሁሌም ሳልናገር በፊት ያሰብኩት እንዴት እንደሚገባው ግርም ይለኛል።
"እኔስ እንግዳ ተቀባይ ነሽ አልኩ እንጂ ባል ትፈልጊያለሽ ወጣኝ? እኔ የምለው እማዬ ባባን እንዳላመጣሽው ነገረችኝ ለማን ትተሽው ነው ስራ የገባሽው?" አለኝ። ስራ ስገባ እነእማዬጋ እየተውኩት ነበር የምሄደው።
"የምታይልን ልጅ ቀጠርኩ" ስለው የሆነ የምስራች የነገርኩት ነበር የሚመስለው። ደስ አለው።
"ምነው? ምንድነው የሚያስፈነድቅህ?"
"እህቴ ሰራተኛ ኖራት!" ብሎ አሁንም ይፍነከነካል።
"ታዲያ ምኑ ነው የሚገርመው?"
"እስከዛሬ ሰው ሳያስፈልግሽ ቀርቶ ነበር ሰው ያልኖረሽ? 'እኔ የማንን ጎፈሬ ሳበጥር ነው ሰራተኛ የምቀጥረው?' ያልሽንን አምነንሽ ዝም ያልን ነው የሚመስልሽ? አዲስ ሰው ወደ ህይወትሽ በምንም መልኩ እንዲገባ ስለማትፈልጊ ነው። ይሄንንማ ለእማዬ እስክነግራት...."
"ኸረ አይደለም! ደግሞ እማዬም እንደዛ ነው የምታስበው?" የምርም በዚህ መንገድ አስቤው አላውቅም!!
"አንቺ ብቻ ነሽ እንደዛ የማታስቢው" አለኝ አሁንም ፈገግታው ፊቱ ላይ እየተርመሰመሰ። ቀጠል አድርጎ "ግሩም ምን አለ?"
"ስለምኑ?" ድንብር አልኩ።
"ስለሽምግልናው ነዋ!"
"ደስ ነው ያለው!! ቅጣቱን አይደል በገንዘብ የቀየርንለት? ለምን ካሳውን እንደመረጥኩ ስነግረው 'እንኳን በሞትና በህይወት መሃከል ለመሆኗ ምክንያት ሆኜ፣ እንዲሁም ልንረዳት የሚገባት ሴት ናት!' አለኝ"
"ቆይ ቆይ ከዚህ ሌላ ምን አወራችሁ?"
"ምንም!" አልኩኝ ፍርጥም ብዬ
"አላውቅሽም እና ነው? ሌላ ነገርማ አለ! ምን አለ ስልሽ እንደፌንጣ አትዘዪም ነበር።"
"እራት ልጋብዝሽ!" አለኝ።
"እና?"
" ለምን? ስለው ላመሰግንሽ አለኝ! እስከአሁን ያመሰገንከኝ በቂ ነው እራቱ አስፈላጊ አይደለም አልኩት ..." ተናግሬ ሳልጨርስ ማት በሳቅ ይንፈቀፈቅ ጀመር።
"እንዴት ያለሽው ገልቱ ነሽ?" እያለ በሳቅ ይፈርሳል ። የማይሆን ነገር ስናደርግ ገልቱ ብቸኛዋ የአባዬ ስድብ ናት። እራት ልጋብዝሽ ማለት 'ላውቅሽ እፈልጋለሁ!' ማለት እንደሆነ ጠፍቶኝ አልነበረም። አፌ ላይ የመጣልኝ ለምን? የሚል ጥያቄ ነበር። እሱም እንደማቲ 'ምኗ ገልቱ ናት?' ብሎ መሰለኝ ላመሰግንሽ! ያለኝ!! ማት መሳቁን አላቆመም!!
"ማቲዬ በእማዬ ሞት እረፍ!"
"እሺ ይቅርታ!" ለመኮሳተር ይሞክርና ደግሞ ይስቃል። "እህቴ ይቅርታ አለመሳቅ ከባድ ነው። ለምን? ምን የሚሉት ጥያቄ ነው?" ይደክማል። "ቆይ አንቺ ከአሼ በኃላ ጭራሽ ዴት አድርገሽ አታውቂም? እንዴ (እንደማስታወስ እያለ) ማነው ይሄ ቢጫ መኪና የሚነዳው ቢጫው ሰውዬ ..." ይስቃል