Get Mystery Box with random crypto!

ዜማና ሰውነት [ግዕዝ፤አሃዱ] ሰዎች'እንዴት ነው ሰብራህ የሄደችው ?' ብለው ሲጠይቁኝ ' ልቤ እስ | ወግ ብቻ

ዜማና ሰውነት
[ግዕዝ፤አሃዱ]
ሰዎች"እንዴት ነው ሰብራህ የሄደችው ?" ብለው ሲጠይቁኝ " ልቤ እስከሚያነክስ" ብዬ ከመለስኩላቸው ረጂም ጊዜ ቢያልፍም ድንገት ቀና ስል የጠራ የመስከረም ሰማይ አይቼ ናፈቀችኝ ።
ለእንቁጣጣሽ በፈካ ቢጫ አደይ ያቆጠቆጠ አረንጓዴ መስክ ላይ ይሄን ብራ ሰማያዊ ሰማይ ደርበን የተራከብን ነን። በሚያሳሳ የመስከረም ቀን መኻል
አፍላነት ያቀጣጠለው፤ ነፋስ ስሞ ያበረደው ገላችን ላይ ጣል ያደረግነው፤ የተጋፈፍነው ሰማይን ነው። ሽቅብ ያየሁበትን አይኔን ቶሎ ሰበርኩ እንጂ ባተኩር ከጭኗ የተላቀቀ የጠይምነቷን ባዘቶ ጉም ሰርቶ አየው ነበር። ሁሉ እንደዛሬ ስላይደለ ልብ ብዬ ባየው ህመሙ ነፍሴ ላይ ያረብባል እንጂ። በልጅነት ቀናቷ ድንግል ልቧን እና ነፍሷን የገረሰስኩ ተቀዳሚ ግዕዟ ነኝ። ማለት የመጀመሪያውን መሳም የትኛውም መሳም እንደማይሽረው፤ የመጀመሪያው ዜማ ድንቅነት በሌሎች እንደማይሸፈነው፤ በልቧ ቅኝት ላይ ተደላድዬ የተፃፍኩ ማንም የማይሰረዘኝ ዜማዋ ነኝ። ለመጣ ለሄደው ሳትሰለች የምትነግረኝ ገድሏ ከአንደበቷ የምወጣ ብቸኛ ተረኳ መሆን ትምክተኛ አድርጎኝ፤ ልታቅፈኝ የዘረጋቻቸው እጆቿ አየር ላይ
እንደተንከረፈፉ ትቻት ስነጉድ፤ በማንም ያልተሳሙ ለጋ ከንፈሮቿ ሊስሙኝ ሲተጉ
ስገፋ ተስፋ ቆረጠችና ያልቃል ብዬ ያልገመትኩትን ለኔ ያላትን ፍቅር ለሌላ አጋርታ አገኘኹዋት። በኔ ግዕዟ ላይ እዝል ደርባ የምታዜም ሆነች። ፀፀት ልቤን ሲበላኝ እስከዛሬ ትምክህት የሸበበው አንደበቴን ከፍቼ እንደምወዳት
ነገርኳት። ሁለተኛ ፍቅሯ ከኔ እንደማይበልጥባት አውቃ ይሁን የዘመናት ህልሟ ስለሆንኩ ብቻ ግን መውደዴን ስነግራት ደስ አላት አቅፋኝ አለቀሰች። "ሁሌም አለሁልህ "አለችኝ።
ፍቅሬ በእኔ በግዕዟ እና በሁለተኛዋ እዝሏ ዜማ የምትንገላታ አሳዛኝ አራራይ
ሆነች። በዚህ ዜማ የታመምን ሶስት ሰዎች ነበርን። ከእርሱ ጋር አሸብሽባ
እንደምትመጣ እያወኩ በቅዳሴዋ ልዘምም ደፋ ቀና ስል ከጠይም ገላዋ ላይ የሚነሳ የእዝሏ ጠረን፣ ከሴትነቷ የሚተን የእርሱ ጢስ ዜማዬን እና አቋቋሜን ቢያዛባውም። በ"የኔ ነበረች፤ ሁሌም የኔ ነች። " እምቢተኝነት በቅኝት መኻል ሽብርክ የሚል ልቤን ታቅፌ ወረቧ ላይ ከርሚያለሁ። አሁን ይሄን እኔ እና እርሷ የተጋፈፍነውን የመስከረም ብራ ሰማይ ቀና ብዬ ባይ በተመሳሳይ ቀን እኔ ጋር ከመምጣቷ በፊት ከእዝሏ ጋር የነበራትን ወረብ በበራሪ ኮከብ እንደ ስዕል አስቀምጦ ያሳየኛል። ግን አይኔን አቅንቼ ሰማዩን ሳይ ትዝ ባለችኝ ቅፅበት አንገቴን መልሼ እጄን ደረቴ ላይ አጣምሬ የልቤ ድሪቶ ውስጥ ቀበርኳት። ቢሆንም እኔ ምንም የልቤ ስርቻ ውስጥ እንደመነኛ ልጥላት ብሞክር በእርሷ ልብ ውስጥ ግን ያለኝን ቦታ አውቃለሁ፤ ብዙ ሁለተኞች ያልሻሩኝ የሁሉ ነገር አሃዱዋ ተቀዳሚ ግዕዟ ነኝ። [እዝል፤ ተደራቢ]
ትዝ የምትለኝ በእኩለ ሌሊት ነቅቼ ሲጋራዬን ለኩሼ ያጨስኩ ቀን ነው። ከሁሉ ከሁሉ የምትወደው ከንፈሬን ነው። ከንፈሬ ላይ ባለችው ጥቁር ነቁጥ ሁሉ ሳትቀር ትቀና ነበር "ማርያም ለምን ሌላ ቦታ አልሳመችህም?" ብላ ታኮርፈኛለች። ሌሊት እንዳልቀሰቅሳት ተጠንቅቄ ተነስቼ ወንበር ስቤ ተቀምጬ
ሲጋራዬን ስለኩስ ከእንቅልፏ ትነቃለች። በቅጡ ያልተከፈቱ አይኖቿን ገርበብ
አድርጋ " ጭሱን ከአፍህ ልውሰድ?" ትለኛለች። ቀጥላ ከመኝታዋ ተነስታ ጭኔ
መሃል ትንበረከክ እና አጭሼ የምተነፍሰውን ጭስ ከአፌ አንደ ወፍ ትቀበላለች። የዛኔ ከንፈሮቻችን ተጋጥመው ቅጡ በማይገባን ወረብ ቆመን መወዛወዝ እንጀምራለን።
ሁሉም እንደሚያውቀው ከኔ ቀድሞ በገጠማት ዜማ ያልተደሰተች ዘማሪ ነች እኔ አፍላነቷ ጎትቶ ከቀሚሷ ስር ከገላዋ ላይ ያዋለኝ እዝሏ ተደራቢ ዜማዋ ነኝ።
አለ አይደል በግዕዝ የጋለ እሳቷን አቀዝቅዤ አረጋጋታለሁ። ቀልበ ቢስ ቀልቃላ እና ሃይለኛ ቅላፄዋን ዳብሼ ገርቼ እመልስላታለሁ። የመጀመሪያዋ ነውና ለግዕዟ ያላትን ስሜት በአንዴ አውጥተሽ ጣይ ባልላትም። በኔ እርጋታ አገግማለች። ፍቅር ከጀመርን ከጥቂት ጊዜ በኹዋላ በወረባችን መኻል የቀደመ ትትርናዋን ችላ ብላ ሁሉ ነገሯ ሲቀየርብኝ ግራ ገባኝ ። ቆይቼ አስቸጋሪ ግዕዟን አስጣልኳት ያልኳት እርሷ የቀደመ ቅላፄዋን ሳትተው በእኔ ላይ ደርባ ማዜም መጀመሯን አወኩኝ ። ይህን ሳውቅ እውነቱን በልቤ ደብቄ ሸፋች ልቧን ላረጋጋ ርቃኗን አስተኝቼ ከላይ እስከ ታች በከንፈሬ እየዳበስኩ በእንባዬ አርጥቤ አጠብኳት። እንዲህ ሳደርግ በሃይለኛ እና እምቢተኛ የሚማረክ እርሷነቷ ለኔ መለማመጥ
ትኩረት መስጠት ተሳነው። እናም ያኔ የጀመርነው ለስላሳ ቅኝት ዜማችን
ተቆራረጠ። አሁን ዛሬ ላይ ስለ እርሷ ሳስብ ሃዘን በልቤ ያልፋል ። በህይወቷ ከተጣባት ጠንካራ ግዕዝ ላሳርፋት የጣርኩ ለስላሳ እዝሏ ብሆንም እዚያና እዚህ የሚረግጥ አሳዛኝ አራራይ ነፍሷ ግን ያን እንድታደርግ አልፈቀደም። ከብዙ ጊዜ በኹዋላም ቢሆን እኔ ላይ ካደረገችው ክህደት ይልቅ ለቅብዝብዝ እርሷነቷ እና በዚህ ምክንያት ለሚበላሹ ዜማዎቿ የማዝን ተደራቢ ዜማዋ እዝሏ ነኝ። [አራራይ፤ አሳዛኝ] ሰዎች በሰራኹዋቸው ነገሮች በሙሉ ይበሳጫሉ። ይበሳጩና ያዝናሉ።
የበደልኳቸው እንኳን ትንሽ ተበሳጭተውብኝ ቀጥሎ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ለእኔ ማዘን ነው። እኔነቴ ሰው ጨክኖ ጆሮ እንደ ማይነፍገው አሳዛኝ ዜማ ነው፤ እንደ አራራይ። ስለ ዜማ ሳስብ ስለ ሁለቱ የቀድሞ ፍቅረኞቼ አስባለሁ። የመጀመሪያው ግዕዜ
ነው ...... ልጅነቴን በጥበቃ የጨረሸ፤ የኮራብኝ፤ የተጀነነብኝ፣ ደጅ ያስጠናኝ፣
ያስለመነኝ፣ እልህ ያጋባኝ ፣ የፈተነኝ። ሁለተኛው ደግሞ እዝሌ ነው ......የደረብኩት ፣ ያረጋጋኝ ፣ያበረደኝ ፣የወደደኝ። ስለምነው የከረምኩት ግን የገፋኝ። በኋላም ከሚያሳርፈኝ ጋር እፎይ ማለቴን ሲያይ ስመኘው የኖርኩት ፍቅር ካልሰጠሁሽ ብሎ ፊቴ ቆመ። አመታት እርሱን የኔ በማድረግ ምኞት አልፈው በመጨረሻ ፊቴ ሲቆም አይሆንም ማለት አቅቶኝ፤ እዝሌንም በቃኸኝ ግዕዜን አግኝቻለሁ ብዬ እንዳልለው የምጠለልበት የምሰክንበት ጥጋቴ ነውና እንዳላጣው ፈርቼ በሁለት ቢላ የምበላ ሆንኩኝ ። ሁለቱንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳላስባቸው ውዬ አላውቅም። ባስታወስኳቸው ቁጥር ግን ሃዘን ይከበኛል። ሁለቱም በመቅበዝበዝ እና በመንገብገብ ያበላሸኹዋቸው የህይወቴ ዋና ዋና ዜማዎች ናቸው። በእርግጥ ከነርሱ በኋላም ያማረብኝ ቅላፄ የተዋጣልኝ አቋቋም የለም ግን እንደ ሁለቱ ያበላሸሁት የለም። አሁን ላይ ከግዕዜና ከእዝሌ የተረፈኝን አራራይ ዜማ ለራሴ ወስጄ ሌት ተቀን እህህ እላለሁ።
ሁሉን የእኔ ይሁን የሚል ልጅነቴን ለተከተለ ደመነፍሴ ፣ በሁለት ዜማ አንድ ቅኝት ለናፈቀ ለጋነቴ ፣ ለባተልኩት ፣ ለባከንኩት ፣ ከሁሉ ከሁሉ በአንድ እለት ግዕዝም እዝልንም ለተቀበለ ሴትነቴ በአራራይ ዜማ እህህ እላለሁ ። በመጨረሻ የገባኝ ግን ሁሉ በአሳዛኝ ዜማ እንደሚቋጭ ነው ፤ ህይወት የሚባል ውብ ነገርም ቢሆን

@wegoch
@wegoch
@paappii

#elssa mulugeta