Get Mystery Box with random crypto!

እሊህ ሦስቱ አባቶችም የካህናት አለቆችና እኛ ወደ አለንበት ከቅርጺቱ ሥዕል ጋር መጥተው ወቀሷቸው | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

እሊህ ሦስቱ አባቶችም የካህናት አለቆችና እኛ ወደ አለንበት ከቅርጺቱ ሥዕል ጋር መጥተው ወቀሷቸው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ነገሩአቸው።
ከዚህም በኋላ ጌታችን አባቶችን ወደቦታችሁ ሒዱ አላቸው ወዲያው ተመለሱ ቅርጺቱንም ወደቦታሽ ተመለሽ አላት እርሷም ወደ ቀደመው አኗኗርዋ ተመለሰች ይህንንም አይተው የካህናት አለቆች አላመኑም ሌላም ብዙ አለ ብነግርህ መወሰን አትችልም ነገር ግን ለብልህ ጥቂት ቃል ትበቃዋለች ለሰነፍ ግን ቢነግሩት በቁም ነገር ላይ አይታመንም።
ከዚህም በኋላ ጌታችን ማነጋገሩን ገታ ራሱንም እንደሚያንቀላፋ አደረገ እንድርያስም አንቀላፋ እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲሸከሙአቸውና ሊገቡበት ወደሚሹት አገር በውጭ እንዲአኖሩዋቸው መላእክትን አዘዛቸው።
ከዚህም በኋላ እንድርያስ በነቃ ጊዜ ዐይኖቹን ገለጠ የከተማውንም በር ተመለከተ በየብስም ላይ እንዳለ አውቆ ደነገጠ አደነቀም። ደቀ መዛሙርቱንም አነቃቸውና እንዲህ አላቸው ጌታችንን በባሕር ላይ ሳለን ያላወቅነው ምን አደረገብን ሲፈትነን መልኩን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታይቶናልና።
ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት እኛም በጌትነቱ ዙፋን ላይ ሁኖ የመላእክት ሠራዊት ሁሉ በዙሪያው ሁነው ጌታችንን አየነው አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብንም ቅዱሳንን ሁሉ አየናቸው ንጉሥ ዳዊትም በመሰንቆ ይዘምር ነበር። እናንተንም ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት በፊቱ ቁማችሁ ዐሥራ ሁለቱንም የመላእክት አለቆች በፊታችሁ ሌሎች መላእክት በኋላችሁ ሁነው አየናችሁ። እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስንም መላእክትን እንዲህ ብሎ ሲያዛቸው ሰማነው የሚሉአችሁን ሁሉ ሐዋርያትን ስሟቸው።
እንድርያስም በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ይህን ድንቅ ምሥጢር ያዩ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ የሚገባቸው ሆነዋልና። ከዚህም በኋላ እንድርያስ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከእኛ ከባሮችህ ሩቅ እንዳልሆንክ አወቅሁ። ነገር ግን በመርከብ ላይ እኔ እንደማስተምረው ሰው መስለኸኝ በድፍረት ተናግሬሃለሁና ጌታዬ ይቅር በለኝ ።
በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእንድርያስ ዳግመኛ ተገለጠለት እንዲህም አለው። አዎን እኔ ነኝ በሊቀ ሐመር አምሳል በባሕር ውስጥ የተገለጥኩልህና መርከቡን የቀዘፍኩልህ። አትፍራ አትደንግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁ ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት በክብር ዐረገ እንድርያስም መንገዱን ሄደ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጌቶቻችን ሐዋርያት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፦ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

የዪቲዩብ ቻናል ስለከፈትኩ ለማበረታታት subscribers ያድርጉልኝ ✥ ✥

Bisrat negari kidus gebrel tube ብስራት ነጋሪ ቅዱስ ገብርኤል
https://youtube.com/channel/UCzj1rOCD7-WVTFN7VU8RmZw