Get Mystery Box with random crypto!

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን ነሐሴ 30-ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሚልክ | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ነሐሴ 30-ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሚልክያስ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ጌታችን ለሐዋርያው ለቅዱስ እንድርያስ በባሕር ውስጥ በሊቀ ሐመር አምሳል የተገለጠለትና ድንቅ ተአምር ያደረገበት ነው፡፡
+ዳግመኛም በዚኽች ዕለት የሀገረ ፈርማው ኤጲስቆጶስ አባ ሙሴ ዕረፍቱ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል፡፡ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
✞✞✞✞✞
ነሐሴ ሠላሳ በዚች ቀን ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያት አንዱ ታላቅ ነቢይ ሚልክያስ አረፈ። ይህም ነቢይ የእስራኤል ልጆች ከተሰደዱበት ከባቢሎን ሀገር በተመለሱ ጊዜ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፋቸው ገሥጿቸዋል።
ሁለተኛም ነቋር ስለሆነ መሥዋዕት ስለ አሥራትና በኵራት ገሥጿቸዋል። በዚህ ነቢይ አንደበት እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና ርኅራኄ አድርጋችሁ ምጽዋትን መጽውቱ፣ ዐሥራቴንና በኵራቴንም አስገቡና እስቲ ፈትኑኝ እኔ ከሰማይ ዝናሙን ባላወርድላችሁ በረከትንም አስቲበቃችሁ ባልጨምርላችሁ የምድራችሁንም ፍሬ ነቀዝና መሰክ እንዳይበሉት እከለክላለሁ።
ዳግመኛም ከክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አስቀድሞ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ መምጣቱ ስለ ነቢዩ ኤልያስም ተናገረ። ደግሞ ስለ አይሁድ የሥርዓተ ክህነት ፍጻሜ ተናገረ በአሕዛብም አገር ውስጥ ለእግዚአብሔር የሚቀበላቸውን መሥዋዕት የሚያሳርጉ ዕውነተኞች ንጹሐን ካህናት እንዳሉ ገለጠላቸው።
በበጎ ተጋድሎውም እግዚአብሔርን ከአገለገለ በኋላ ከዚህ ዓለም በመፍለስ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን ጌታችን በባሕር ውስጥ ለሐዋርያ እንድርያስ በሊቀ ሐመር አምሳል ተገልጦ ድንቅ ተአምር አደረገለት።
እንድርያስም ጌታችንን በመርከብህ አሳፍረን ነገር ግን የምንከፍልህ የመርከብ ዋጋ የለንም አለው። በሊቀ ሐመር የተመሰለ ጌታችንም ስለምን የላችሁም አለው እንድርያስም በከረጢታችን ወርቅን፣ ብርን እንዳንይዝ ጌታችን ስለአዘዘን ነው አለው። ጌታችንም እንዲህ ከሆነ ወደ መርከቤ ወጥታችሁ ተሳፈሩ አላቸው ያንጊዜም ወደ መርከብ ወጥተው ተሳፈሩ።
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን ከባሕሩ ማዕበል የተነሣ መታገሥ እንድትችሉ ተነሥታችሁ እንጀራ ብሉ አለ። አንድርያስም አድንቆ እንዲህ አለው በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት እንጀራ እግዚአብሔር ይስጥህ። ደቀ መዛሙርቱ ግን በባሕር ላይ ጉዞ ስለአልለመዱ ከባሕሩ ማዕበል ፍርሀት የተነሣ መብላት መነጋገርም ተሳናቸው ።
ጌታችንም እንድርያስን ደቀ መዛሙርትህን ወደ ምድር እንዲወርዱ እዘዛቸው ሲፈሩ አያቸዋለሁና ይህ ካልሆነ እንዳይፈሩ አንተ የኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ ከሆንክ ጣዕም ባለው ቃል አስተምራቸው እነሆ ከየብስ ርቀናልና አለው። ጌታችንም መርከቡን መቅዘፍ ጀመረ እንድርያስም ማስተማርና ማጽናናት ያዘ በልቡም ጸለየ ያን ጊዜም ከባድ እንቅልፍን አንቀላፉ ስለተኙለትም እንድርያስ ደስ አለው።

እንድርያስም ወደ ጌታችን ተመልሶ እንዲህ አለው ዐሥራ አራት ጊዜ በባሕር ላይ ጒዞ አድርጌአለሁ እንዳንተ የሚቀዝፍ አላገኘሁም። ጌታም መልሶ እንዲህ አለው እኛስ በባሕር ላይ ስንጓዝ ሁል ጊዜ እንቸገራለን። ነገር ግን አንተ የክብር ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሆንክ ባሕር ስለአወቀችህ ማዕበሏን በአንተ ላይ አላነሣችም እንድርያስም በታላቅ ቃል እንዲህ ብሎ ጮኸ። የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግንሃለሁ ከሚያከብርህ ሰው ጋር ተገናኝቼ ተነጋግሬአለሁና።
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንድርያስን እንዲህ አለው አንተ የክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ነህና ንገረኝ። አይሁድ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ስለምን አላመኑም የሠራውን ብዙ ድንቅ ተአምርን ሰምተናልና አለው። እንድርያስም እንዲህ አለው አዎን ወንድሜ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ገልጦልናል አንካሶችንም በትክክል እንዲሔዱ አድርጓልና፣ ደንቆሮዎችንም አሰምቷልና፣ ዲዳዎችንም አናግሮአልና፣ ለምጻሞችንም አንጽቷልና፣ ውኃውንም ወይን አድርጓልና፣ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን አንሥቶ ያዘ ሕዝቡንም በመስክ ሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ ሣሩም እንጀራ እስቲለብስ ድረስ በልተው ጠገቡ የተረፈውንም በብዙ ቅርጫቶች አነሣን ይህም ሁሉ ሲሆን አላመኑም።
ጌታ ኢየሱስም እንዲህ አለው ይህን ያደረገ በግልጥ ነው ወይስ በሥውር። እንድርያስም እንዲህ አለው ይህንስ በግልጥ ነው ያደረገ በሥውር ያደረገውም አለ ግን የምትፈትነኝ መሰለኝ ጌታችንም እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ልቤን ደስ ስለሚላት ነውና ንገረኝ።
እንድርያስም እንዲህ አለው ልጄ ሆይ በጎ ሥራህን ሁሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ አሁንም ስማ ጌታችን ያደረገውን ተአምር እኛ ዐሥራ ሁለታችን ሐዋርያቶቹ ከእርሱ ጋራ ስንጓዝ ከሊቃነ ካህናትና ከሕዝቡ ብዙዎች አሉ። ወደ ምኵራብም ደረስን ጌታችንም እንዲህ አለ በሰማይ ባሉ በኪሩቤልና በሱራፌል አምሳል በምድር ላይ ሰው የሠራትን ይቺን የተቀረጸች ሥዕል ታያላችሁን።
ከዚህም በኋላ ወደሥዕሊቱ ተመልሶ ብልህ ሰው የተጠበበብሽ የሰማያውያን መልክን ያደረግሽ አንቺን እላለሁ ከቦታሽ ተነቅለሽ ውረጂ የካህናት አለቆችንም ውቀሻቸው እኔም ዕሩቅ ብእሲ ወይም እግዚአብሔር እንደሆንኩ መስክሪ አላት። ወዲያውኑ ከቦታዋ ተነቅላ ወረደች እንደሰውም በመናገር እንዲህ አለች እናንተ የደነቆራችሁ አይሁድ የራሳችሁ መደንቆር ያልበቃችሁ ሌሎችንም ለማደንቆር የምትሹ ለድኅነታችሁ ሰው የሆነ እግዚአብሔርን እንዴት ዕሩቅ ብእሲ ትሉታላችሁ አስቀድሞ ሰውን የፈጠረው በንፍሐት ልጅነትንም የሰጠው ይህ ነው።
አብርሃምን የተናገረው፣ ይስሐቅንም ከመታረድ ያዳነው፣ ያዕቆብንም ወደ አገሩ ያስገባው ይህ ነው ለሚፈሩት በረከትን የሚሰጥ ለማይታዘዙለት ቅጣትን የሚያዘጋጅ ይህ ነው ።
እውነት እነግራችኋላሁ እናንተ ስለምትክዱት ሕጉንና ሥርዓቱንም ትለውጣላችሁና ስለዚህ እነሆ መስዋዕታችሁ ይሻራል ምኵራቦቻችሁም በዋሕድ ወልደ እግዚአብሔር ስም አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ። ይህንንና የሚመስለውን ተናግራ ዝም አለች።
እኛም የካህናት አለቆችን መልሰን እንዲህ አልናቸው እነሆ ቅርጺቱ ሥዕል ተናግራ ወቀሰቻችሁ ታምኑ ዘንድ ይገባችኋል። የካህናት አለቆችና አይሁድም እንዲህ አሉን ይህ የሚያናግረው በሥራይ ነው አብርሃምን በወዴት አገኘው ከሞተ ዘመኑ ብዙ ነውና።
ጌታ ኢየሱስም ወደ ቅርጺቱ መለስ ብሎ እንዲህ አላት አብርሃምን እንዳነጋገርኩት አላመኑምና ሔደሽ እንዲህ በይው። አስቀድሞ አዳምን የፈጠረው፣ አንተንም ወዳጁ ያደረገህ፣ አንተ ልጆችህ ይስሐቅና ያዕቆብን ይዘህ ተነሥ ከመቃብርም ወጥተህ ወደዚህ ኑ የካህናት አለቆችን ትወቅሱአቸው ዘንድ እኔ የማውቃችሁና የተነጋገርኳችሁ መሆኔን አስረዷቸው። ቅርጺቱም ሥዕል ይህን ሰምታ እያየናት ሔደች ወደ አብርሃምም መቃብር ደርሳ በውጭ ቁማ ጠራቻቸው። ወዲያውኑ ከሦስቱ አርእስተ አበው ጋር ዐሥራ ሁለቱ ወጡ ከእኛ ውስጥ ወደ ማን ነው የተላክሽ አሏት። ቅርጺቱም እንዲህ ብላ መለሰች ወደ ሦስቱ የአባቶች አለቆች ነው እናንተ ግን እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ ተኙ ያን ጊዜም ወደ መቃብራቸው ተመለሱ።