Get Mystery Box with random crypto!

እንደ ኢትዮጲያ ከሞላ ጎደል Progressive Capitalism (ማለትም በመንግስት፤ የግል ሴክተ | The Ethiopian Economist View

እንደ ኢትዮጲያ ከሞላ ጎደል Progressive Capitalism (ማለትም በመንግስት፤ የግል ሴክተሩ እና የምርምር ተቋማት በመቀናጀት ስትራቴጂክ የሆነ አቅም በመፍጠር አቅርቦት እና ፍላጎትን ማቀራረብ ላይ ያነጣጠረ) ስርዓት ለመተግበር በምትሞክር ሃገር ውስጥ ነጻ ገበያ በመሆኑ ማሰገደድ አንችልም የሚሉ መግለጫዎች፤ ነጻ ገበያ በመሆኑ መብታችን ነው ተባልን የሚሉ ሸማቾች እና ነጻ ገበያ በመሆኑ ዋጋ ተማኝ ነን የሚሉ አምርቾች/ሻጮች፤ መስማት በጣም  እንግዳ ነገር ነው፡፡

ነጻ ገበያ ማለት በጥቂት የመንግስት ጣልቃ ገብነት ወይም ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት ገበያውን አቅርቦት እና ፍላጎትን ተከትሎ እንዲመራ መፍቀድ ማለት ነው (ነጻ ገበያ ስለዋጋ ያለ ጉዳይ ብቻ ማለትም አይደለም)፡፡

ነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ዋና ተዋናይ የሆኑት ሸማቾች እና አምራቾች/ሻጮች ሌላው ተዋናይ መንግስት ተቀንሶ ገበያው ላይ የመወሰን መብት እዲወስዱ የተሰጠ የውክልና አካሄድ ነው፡፡ በዜጎች መካከል ያለው የሃብት ክፍፍል ሲዛነፍም ሆነ ፍታዊነትን ለመጠበቅ ሲባል ገበያን ለብዙሃን ምቹነት ሲባል በመንግስት መጎብኘቱ አይቀርም! ምክንያቱም ነጻ ገበያን ይዞ ብቅ ካለው አዳም ስሚዝ (1723-1790) ጀምሮ ላለፉት 250 ዓመታት በወረቀት እንጂ በተግባር አሟልቶ መተግበር የቻለ አንድም ሃገር የለም፡፡

በዓለም የኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ ነጻ ገበያ ስርዓት ምናባዊ ነው ተብሎ የሚተችበት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መተግበር አለመቻሉ ነው፡፡ ምክንያቱም መንግስታት በጥቂቱም ቢሆን ገበያውን ማየት አለመቻላቸው የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ጣልቃ መግባታቸው ወደው ሳይሆን ተገደው ነው::

ሃገራት በተለይ ፖለቲከኞች ነጻ ገበያ ላይ ገደብ ለማስቀመጥ የሚደፍሩበት መሰረታዊ ምክንያት የሚመነጨው ለፖለቲካል ኢኮኖሚው ደህንነት፤ ፍታዊነትን ለመጠበቅ እና የህዝብ የጋራ መጠቀሚያ ሃብቶችን ለመፍጠር ሲባል ነው፡፡ ገበያ ቸል በተባለ ቁጥር የጥቁር ገበያ መጠንከር፤ የብቸኛ አምራች እና አቅራቢነት ባህሪ መፈጠር እንዲሁም ወደ ኢኮኖሚው ስርዓት መግባትን ከባድ የማድረግ ልምምድ ስለሚፈጠር ነው፡፡

ለነጻ ገበያ የቀረበ የኢኮኖሚ ስርዓት አመክንዬ ያላቸው ሃገራት ነጻ ገበያን የግለሰቦችን ሃብት የመፍጠር ነጻነት እና የግለሰቦችን መብት ማክበር ድረስ ነው የሚተገብሩት ምክንያቱም ነጻ ገበያ የመንግስት ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን የመንግስት ድጎማንም ማስቀረት አለበት ስለሚል ነው፡፡ በአይነትም ሆነ በፖሊሲ ባልተደጎመ አርሶ አደር በተመጣጣኝ ዋጋ እና በገፍ ሰብል ወደ ገበያ ለማቅረብ ላደጉም ሃገራት ቀላል አይደለም፡፡

ስለ ካፒታሊዝም በተለይ የነፃ ገበያ አቀንቃኞች የማይነግሩን 23 ቁልፍ ጉዳዮች! በሚለው ድንቅ መጽሃፉ ፕሮፌሰር ሃ ጁን ቻንግ እንደሚለው በእውነት ነፃ ገበያ የሚባል ነገር የለም There is Really No Such Thing as a Free Market ወይም ብዙ ኢኮኖሚስቶች እንደሚስማሙት No Pure Free Market Economies Actually Exist, and All Markets Are in Some Ways Constrained):: ይህ ከኢትዮጰያ እስከ አሜሪካ ገበያ ያለ ሃቅ ነው፡፡

አስታውሱ የነጻ ገበያ መስፈርቶች በሙሉ ተተገበሩ ማለት መንግስት የገበያ ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን ድጎማንም ማስቀረት አለበት ማለት ነው፡፡ በተለያየ መልኩ በድጎማ ስርዓት ውስጥ የማያልፍ አምራች እና ሻጭ ለማግኘት ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በሚደጎም ነዳጅ፤ በሚደጎም ውሃ፤ በሚደጎም መብራት፤ በሚደጎም የህዝብ መገልገያ እየተጠቀሙ የሚያመርቱ አምራቾች ሸማቾችን መግፋት መብታቸው ሊሆን አይችልም፡፡

ነጻ ገበያ ነው ከፈለክ ግዛ ካልፈለህ ትተህ ሂድ፤ ከፈለኩ እሸጣለሁ ካልፈለኩ አልሸጥም፤ በገዛ ንብረቴ ዋጋ መወሰን እችላለሁ፤ ወዘተ ማለት ነጻ ገበያ ማለት አይደለም፡፡ ህግን ማስከበር ባለመቻል የሚመጡትም ሆነ በህግ ያለመገዛት አዝማሚያዎች ሁሉ የነጻ ገበያነት መገለጫ አይደሉም፡