Get Mystery Box with random crypto!

#ዋጋ_እንዴት_ይወጣል? ቢዝነስ ለመጀመርም ሆነ በቢዝነስ ውስጥ ለመቆየት አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮች | The Ethiopian Economist View

#ዋጋ_እንዴት_ይወጣል?


ቢዝነስ ለመጀመርም ሆነ በቢዝነስ ውስጥ ለመቆየት አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮች መካከል ዋነኛው ለሚያቀርቡት ምርት ትክክለኛውን ዋጋ እንዴት ማስቀመጥ እንደሚቻል አለማወቅ ነው፡፡ ትክክለኛውን መስፈርት ጠብቆ ዋጋን መተመን አለመቻል ጠቅላላ የቢዝነስ እንቅስቃሴን ህልውና ያናጋል፡፡


የዋጋ ተመን የሸማችን ሁኔታ በቀጥታ ይነካል፤ ምክንያቱም ሸማች ከምንም በላይ ለሸመታ ውሳኔው ዋጋን በተመለከተ ስሜታዊ ነው (Price Sensitivity) ይህ ሁኔታ ደግሞ አምራች እና ሻጮችን ስለ ዋጋ ሁኔታ እንቅልፍ እንዲያጡ ያደርጋል (የእኛ ሃገርን ሁኔን ገላጭ ባይሆንም)፡፡ የምርትም ሆነ የአገልግሎት ዋጋ በተለመደ መልኩ ወይም ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ሊወሰን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋጋን ለመወሰን ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች መሰረታዊ መስፈርቶች ናቸው፡፡


ሸማች ለሚሸምተው ነገር በአብዛኛው በቂ መረጃ አለው ተብሎ ይታሰባል! ስለዚህ ጊዜው እና ገንዘቡ የሚመጥነውን ዋጋ በራሱ በማስላት እርካታውን ለመጠበቅ ይጥራል፡፡ ስለዚህ አምራቾች እና ሻጮች ትክክለኛውን ሸማች ማወቅ እና ለሚያቀርቡት ምርት እስከ ስንት ድረስ የመክፈል ፍላጎት እንዳለው (Willing to Pay) ማወቅ በሳይንስ (Pricing Strategy) መመራት ያለበት የገበያ ጥናት አካል ነው፡፡


የዋጋ ሁኔታን ለመወሰን ከቢዝነሱ አይነት (ኢንዱስትሪ፤ ግብርና፤ አገልግሎት፤ ቴክኖሎጂ፤ ወዘተ)፤ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ከሚሸምተው እና ከሚጠቀመው ደንበኛ አንጻር (Ideal Target Customers)፤ ምርቱ ወይም አገልግሎቱ ካስወጣው ወጪ አንጻር እንዲሁም ከተመሳሳይ ምርቶች ወይም አገልግሎቶች ካላቸው የዋጋ ንጽጽር አንጻር (Competitive Markets/Pricing) ከግምት መከተት አለባቸው፡፡


#ለምሳሌ፡ የችርቻሮ ሻጮች የዋጋ ተመን ከአምራቾች እኩል አሳሳቢ እና ሳይንሳዊ ለመሆን ላይገደድ ይችላል፡፡


አንድ ምርት ለመመረት ያስወጣውን ወጪ በጠቅላላ ደምሮ ይገባኛል የሚሉትን የትርፍ መጠን (Profit Margin) ጨምሮ ዋጋ ማውጣት በጣም ቀላሉ ነው (Cost-Plus Pricing):: ነገር ግን አምራቾችም ሆኑ ሻጮች ዋጋን አንዴ የሚወስኑት ጉዳይ ብቻ መሆን አይችልም! ምክንያቱም የሚያስቀምጡት ዋጋ የቢዝነሳቸውን ዘላቂነት የሚነካ መሆኑን ማወቅ ግድ ነው፡፡


#ለምሳሌ፡- የሚቀመጠው ዋጋ ወድ ሆኖ ሸማቾች የሚችሉት/የሚመርጡት ካልሆነ ከገበያ መውጣት ሊከሰት ይችላል በተቃራኒው ከመሰረታዊ ወጪ በታች ዝቅተኛ ዋጋ በማስቀመጥም በገበያው በቀጣይ ለመቆየት መቸገር ሊመጣ ይችላል፡፡ በርግጥ ሸማችን እና በገበያው የሚኖርን ዘለቄታዊ ቆይታ በማሰብ በውስን ክስረት መሸጥ ሊኖር ይችላል ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ አካሄድ ነው፡፡


አንዳንዴ አምራቾች ነባር ደንበኞቻቸውን መሰረት በማድረግ የተጨማሪን ዋጋ ሁኔታ መመርመር ይቻላሉ! ይህ የሸማችን የመግዛት አቅም እና ምክንያታዊነት ለማወቅ ይረዳል፡፡


ዋጋ ለማስቀመጥ የሚከተሉትን መስፈርቶች መከተል ተገቢ ነው እነሱም…..


1. ምርቱ ለመመረት ያስወጣውን ጠቅላላ ወጪ ማወቅ (Variable Costs)፡- አምራች ከሆኑ ለማምረት ያወጡት የግብዓት ወጪ፤ የሰራተኛ ወጪ፤ የማጓጓዝ ወጪ እና የስራ ማስኬጃ ወጪዎችን በመውሰድ እና የምርቱን መጠን ደምሮ ማስላት ማለት ነው:: እያንዳንዱ ምርት ተመርቶ ለመውጣት የፈጀው ሰዓት እንደወጪ ዝርዝር ይካተታል፡፡


#ለምሳሌ፡- አንድ ኪሎ ቲማቲም ለማምረት የግብዓት ወጪ 10 ብር ቢሆን፤ ለማምረት የፈጀው ጊዜ ወደ ገንዘብ ሲቀየር በኪሎ 2 ቢሆን፤ ተለቅሞ የሚሰበሰብበትን ሳጥን ለመግዛት የወጣው ወጪ በኪሎ 2 ብር ቢሆን፤ ምንአልባት ለማስተዋወቅ (ባነርም ቢሆን) ያስወጣው ወጪ በኪሎ 1ብር ቢደርስ፤ ቲማቲሙን ወደ ገበያ ለማድረስ ያስወጣው ወጪ በኪሎ 3 ብር ቢደርስ፤ ጫኝና አውራጆች የሚጠይቁት በኪሎ 1 ብር ቢደርስ፤ (ህጋዊም ሆነ ህገወጥ ቀረጥ እና ግብር ኖሮ) 1 ብር ቢያስወጣ……..አንድ ኪሎ ቲማቲም ገበያ ለመድረስ ያስወጣው ወጪ (Per-Product Cost) 20 ብር ደረሰ ማለት ነው፡፡


2.ቋሚ ወጪዎችን ማጠቃለል (Fixed Costs)፡- በማምረት ወቅት የቋሚ ንብረቶች ወጪ መታሰብ አለበት (የመሬት፤ የግንባታ፤ የማሽኖች፤ የመኪኖች፤ ወዘተ) ምክንያቱም ግንባታ ገንብቶ እና ማሽን ገዝቶ የሚያመርት አምራች በሂደት ወጪውን ማካካስ የሚችለው ከሚሸጠው ምርት ነው፡፡


#ለምሳሌ፡- በ10 ሚሊየን ብር ግንባታ ሰርቶ ቲማቲም ለማምረት ቢዝነስ የጀመረ አምራች የሚሸጡ ቲማቲሞች ላይ የቋሚ ንብረቶችን ወጪ መደመር አለበት ነገር ግን በነጠላ እያንዳንዱ ቲማቲም ላይ ለመደመር ሊያስቸግር ይችላል (ዋጋ ሳይንስ ነው የሚባለው ለዚህ ነው! ከጠቅላላው 10 ሚሊየን ብር ውስጥ አንዷ ቲማቲም ምን ያህል ብር ድርሻ ትያዝ?)


3.የትርፍ ጣሪያ (Profit Margin)፡- አምራች ማትረፍ የሚፈልገውን የትርፍ መጠን ለማስላት ሁለት ነገር ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ የመጀመሪያው ለቋሚ ንብረቶች (የመሬት፤ የግንባታ፤ የማሽኖች፤ የመኪኖች፤ ወዘተ) ያወጣው ወጪ እዚህ ላይ መደመር የለበትም ሁለተኛው የሚያጠቃልለው የትርፍ ጣሪያ ጭማሪ ምርቱ መጨረሻ ላይ ሲሸጥ ተቀባይነት ከሚኖራቸው ዋጋዎች በጣም የራቀ እንዳያደርገው መጠንቀቅ አለበት፡፡


#ለምሳሌ፡ ጠቅላላ የምርት ወጪው እና ለቋሚ ንብረት የወጣበት ወጪ ተደምር አንድ ምርት ገበያ ለመድረስ 20 ብር ቢያስወጣ እና አምራቹ የትርፍ መጠኑ 20%  እዲሆን ቢወስን በቀላል ስሌት/Profit Margin Calculator (20 ብር/1-20% (0.2) = 20/0.8 = 25 ብር ሊሸጥ ይችላል) ስለዚህ ምርቱ ያስወጣው ወጪ 20 ብር ሆኖ የምርቱ የመሸጫ ዋጋ 25ብር ደረሰ ማለት ሲሆን የአምራቹ ትርፍ ደግሞ 5 ብር ሆነ ማለት ነው፡፡


ከላይ የተጠቀሱ ሶስቱም መስፈርቶች በሙሉ ታሳቢ ቢደረጉም በመጨረሻ ግን ሸማች ለመሸመት የሚፈቅድበት የዋጋ መጠን (Willing to Pay) ከግምት ካልገባ ዋጋ የለውም፡፡