Get Mystery Box with random crypto!

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ እና ሀገሪቱን ለማገዝ መወሰኑ | AddisWalta - AW

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ እና ሀገሪቱን ለማገዝ መወሰኑን ኢትዮጵያ በበጎ እደምታየው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

ሚያዚያ 18/2015 (ዋልታ) የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያ በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ትልቅ እምርታ ማስመዝገቧን እ.ኤ.አ ሚያዚያ 24 ቀን 2023 መግለጫ ማውጣቱን ጠቅሶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ ከህብረቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ብዙ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን እና ይህ የህብረቱ ውሳኔም ወደላቀ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው ሚኒስቴሩ ጠቅሷል፡፡

ህብረቱ መደበኛውን የባለብዙ- አመላካች አመታዊ ፕሮግራምን እንደገና ለማንቀሳቀስ መወሰኑ፣ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የማረጋጋት ጥረት እንዲደግፉ ማበረታታቱን እና አበዳሪ ተቋማትም የእዳ አከፋፈል ሽግሽግ እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረጉን ኢትዮጵያ በበጎ እንደምትቀበለው አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላሟን በማጠናከር፣ በጦርነቱ የተጎዳውን የህብረተሰብ ክፍል መልሶ በተማቋቋም፣ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን እና የአየር ንብረት ለውጥን ሊቋቋም የሚችል እድገትን ለማሳካት ጥረት በምታደርግበት ወቅት ወዳጅ አገሮች ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ መሆናቸውንም መግለጫው ያመለክታል፡፡

የአውሮፓ ህብርት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባህር እና አካባቢው ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗን እና አገሪቱ ወደ ዘላቂ ሰላም የምታደርገውን ጉዞ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።