Get Mystery Box with random crypto!

ምስጋና እና የመረጃ ማቃኛ! ___ ሰሞኑን አሜሪካ ወደሚገኘው IOWA ዩኒቨርስቲ ከማምራቴ ጋር ተ | Walia bookstore gallery

ምስጋና እና የመረጃ ማቃኛ!
___

ሰሞኑን አሜሪካ ወደሚገኘው IOWA ዩኒቨርስቲ ከማምራቴ ጋር ተያይዞ እዚሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሃሳቦች ሲንሸራሸሩ ሶስት ነገሮችን አስተዋልኩ።

የመጀመርያው በደግ ዐይናቸው የሚያዩኝና ስኬቴን የሚናፍቁ ሰዎች መብዛታቸው! የምሥራቹን ለማብሰር መጣደፋቸው! (ክብረት ይስጥልኝ ከማለት ውጪ ምን እላቸው ኖሯል?)

ሁለተኛው ማቃኛ የሚፈልጉ መረጃዎች በፍጥነት መራባታቸው። አንዳንድ ቦታ እንደተባለው ቆይታዬ ለአመታት አይደለም ለጥቂት ወራት እንጂ። IOWA ዩኒቨርስቲ ብቻ ለአስር ሳምንታት ስንቆይ ሶስት አራት ሳምንቱን ደግሞ ይህን በመሰለ በሌሎች ፕሮግራሞች እንጠመዳለን። እርግጥ ለዚህ ፕሮግራም ተመራጭ ሆኖ መገኘት ይህን ለመሰለ ሌላ ዕድል በር የሚያስከፍት መሆኑን የቀደመ ተመክሯቸውን አንስተው ነግረውናል።

ሶስተኛው ደግሞ " አንተ ከሄድክ ዘወትር ቅዳሜ ከአስር እሰከ አስራሁለት ሰአት ከተለያዩ ደራስያን ጋር የምናደርገው (ዛጎል የመጻሕፍት ባንክና ዋልያ መጻሕፍት አንድ ላይ የሚያሰናዱት) ቆይታስ? ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ መጻሕፍት እየሰበሰበ መልሶ በገጠር ከተማው የሚያሰራጨው ነገርስ? በእጥልጥል ሊቀር?" የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱልኝ ነው። ከደራስያን ጋር የሚደረገው ውይይት እኔን ተክቶ ሌላ ሰው እንዲያወያየው ተወጥኖ የነበረ ቢሆንም ይህም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሳይሆንልን ቢቀርም: ፕሮግራሙ ግን በተለመደው ሰአት በልዩ ልዩ ኪናዊ ስራዎች ዝግጅቱን ያቆዩታል። ውይይቶች ዲስኩሮችና የመጻሕፍት ምርቃቶች ይካሄዱበታል። የመጻሕፍት ባንካችን አገልግሎትም አይቋረጥም። (እስካሁን ከሰላሳ አራት ሺህ በላይ መጻሕፍት በገጠር ከተማው እንዲዳረስ ምክንያት በመሆናችን እና ከዋልያ መጻሕፍት ጋር ሆነንም
ከሰባ በላይ የሆኑ መጻሕፍት ላይ ትኩረት ማድረጋችን ደስታ ቢሰማንም ካደረግነው ይልቅ ልናደርግ ያሰብነው እንደሚልቅ ደግሞ ደጋግመን ልንነግራችሁ እንወዳለን)

በመጨረሻም አሸናፊ ስለሆንኩበት ፕሮግራም በአጭሩ! (ወደፊት ዘለግ አድርገን እስክናወጋ)

IOWA ዩኒቨርስቲ በየአመቱ ከየአለማቱ ደራስያንን መርጦ ፕሮግራም የማሰናዳት ልማድ አለው። ጉምቱ ጉምቱ የብዕር ሰዎችም የኖቤል ሽልማት ወሳጆችም የዕድሉ ተቋዳሽ ሆነዋል። እንዲህ ያለው አጋጣሚ ኢትዮጵያ ሊያልፋት አይገባም በማለት ሲብሰከሰክ የምናውቀው ጌዲዮን ማሞ እንዳጫወተኝ ኤምባሲው በየአመቱ ያለመታከት አወዳድሩልኝ ብሎ ምርጦቹን ቢልክም እንደዘንድሮ ግን በለስ ቀንቶት አያውቅም።

የሆነው ሆኖ ዘንድሮ ውድድሩ የተከናወነው በሚከተለው መንገድ ነው። መጀመርያ እያንዳንዱ አገር ለዚህ ዕድል ብቁ ናቸው የሚላቸውን ደራስያን ስም ዝርዝር ላከ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የሚገኘው ኤምባሲ ሶስት ደራስያንን መርጦ ስለሚጽፉበት ርዕሰጉዳይ ገልጾ "አርአያ ናቸው: ኢትዮጵያን ይወክሉልኛል: ቢያሸንፉ እነሱም እናንተም ደስታና ኩራት ውስጥ ትገባላችሁ!" ብሎ ዝርዝር መረጃ ላከላቸው። እነሱ ደግሞ ስለደራስያኑ የተባለውን በራሳቸው መንገድ አጠኑ። ከዚያም ከሶስቱ አንዱን ብቻ ለይተው ዕጩ አደረጉ። እንደገና እሱንና የሌሎች አገራት ዕጩዎቹን ደግሞ አወዳደሩ። መቶ አስራአምስት ገደማ(?) ደረሱ። የሚፈልጉትና እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጡ የሚፈልጓቸው የደራስያን ቁጥር ደግሞ ከሰላሳ እስከ ሰላሳአምስት ባለው ቁጥር ቢወሰኑ እንጂ እንዲበዙባቸው አይፈልጉም።
ስለዚህ የአሸናፊዎች አሸናፊን ለይቶ ለማውጣት ቃለመጠይቅ አደረጓቸው። መረጃዎቻቸውን አሰባሰቡ። ስለሚያተኩሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መረመሩ።

በመጨረሻም አሸናፊ ሆኖ ሲገኝ ለኤምባሲውም ለደራሲውም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ። ሙሉ ወጪውም በአሜሪካ ኤምባሲና በዩኒቨርስቲው እንደሚሸፈን አበሰሩ።

(እኛም ተደሰትነ!)

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በዚህ ዩኔስኮ የሥነጽሑፍ ከተማ ብሎ በሰየማትና በየዓመቱ ታላላቅ የሥነጽሑፍና የቴአትር መሰናዶዎች በሚኮመኮምባት IOWA CiTY ስሟ ሲነሳ ይህ መጀመርያዋ አይደለም። እኤአ በ1967 ስመጥሩው ደራሲ ዳኛቸው ወርቁም (የ"አደፍርስ" ደራሲ) አሸናፊ ሆኗል::

ወደፊት ደግሞ እንበዛለን ብዬ አምናለሁ።

ሰላም!!!!!