Get Mystery Box with random crypto!

የአሏህ ህልውና በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 22፥6 ይህ አ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

የአሏህ ህልውና

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

22፥6 ይህ አላህ እርሱ መኖሩ የተረጋገጠ፣ እርሱም ሙታንን ሕያው የሚያደርግ፣ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ በመሆኑ ነው፡፡ ذَٰلِكَ بِأَنَّ اللَّهَ هُوَ الْحَقُّ وَأَنَّهُ يُحْيِي الْمَوْتَىٰ وَأَنَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ

በአንድ ወቅት የነገረ ልቦና ምሁር ሲይግመን ፍሮይድ፦ "ሁሉን የሚቆጣጠር እና የሚመግብ አምላክ ፍቅር፣ እንክብካቤ እና ጥበቃ በሚያስፈልገው በሰው ሥነ ልቡና የተፈጠረ ነው"The God who controls and provides everything, is created by the human psyche in response to its need for love, saftey and security" በማለት ኢ-አማኝነቱን ገልጿል። ይህ የኢልሓድ እሳቤ ነው፥ በፈጣሪ እሳቦት ውስጥ ኢማን፣ ኩፍር እና ኢልሓድ ተጠቃሽ ናቸው።
"ኢልሓድ" إِلْحَاد የሚለው ቃል "አልሐደ" أَلْحَدَ‎ ማለትም "ኢ-አመነ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን በአምላክ መኖር "ኢ-አማኒነት"atheism" ማለት ነው፥ በነጠላ "ሙልሒድ" مُلْحِد ማለት "ኢ-አማኝ"atheist" ማለት ሲሆን "ሙልሒዱን" مُلْحِدُون‎ ደግሞ የሙልሒድ ብዙ ቁጥር ነው። ሙልሒድ የኢልሓድ እሳቤ የሚያራምዱ ናቸው፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 87 ሐዲስ 21
ኢብኑ ዐባሥ እንደተረከው፦ “ነቢዩም፦ “ﷺ” እንዲህ አሉ፦ “አሏህ ዘንድ የተጠሉ ሦስት ሰዎች አሉ፦ “በሐረም ውስጥ ያለ ሙልሒድ፣ የጃሂሊያህን ሡናህ ኢሥላም ውስጥ ለማስቀረት የሚፈልግ እና ያለ ሕግ የአንድ ሰው ደም ማፍሰስ የሚፈልግ ናቸው"። عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ، أَنَّ النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم قَالَ أَبْغَضُ النَّاسِ إِلَى اللَّهِ ثَلاَثَةٌ مُلْحِدٌ فِي الْحَرَمِ، وَمُبْتَغٍ فِي الإِسْلاَمِ سُنَّةَ الْجَاهِلِيَّةِ، وَمُطَّلِبُ دَمِ امْرِئٍ بِغَيْرِ حَقٍّ لِيُهَرِيقَ دَمَهُ. ‏

"ዉጁድ" وُجُود የሚለው ቃል "ወጀደ" وَجَدَ ማለትም "አለወ" "ኖረ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መኖር" ሃልዎት" "ህልውና" ማለት ነው፥ "ዉጁዱል ሏህ" وُجُود الله ማለት "የአሏህ ህልውና"the existence of Allah" ማለት ነው። የአሏህ መኖር የተረጋገጠ ነው፦
22፥6 ይህ አላህ እርሱ "መኖሩ የተረጋገጠ"፣ እርሱም ሙታንን ሕያው የሚያደርግ፣ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ በመሆኑ ነው፡፡ ذَٰلِكَ بِأَنَّ اللَّهَ هُوَ الْحَقُّ وَأَنَّهُ يُحْيِي الْمَوْتَىٰ وَأَنَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ
24፥25 በዚያ ቀን አላህ እውነተኛ ዋጋቸውን ይሞላላቸዋል፡፡ አላህም እርሱ "መኖሩ የተረጋገጠ" ሁሉን ነገር ገላጭ መኾኑን ያውቃሉ፡፡ يَوْمَئِذٍ يُوَفِّيهِمُ اللَّهُ دِينَهُمُ الْحَقَّ وَيَعْلَمُونَ أَنَّ اللَّهَ هُوَ الْحَقُّ الْمُبِينُ

"አል ሐቅ" الْحَقّ ማለት "መኖሩ ተረጋገጠ" ማለትም ሲሆን አንድ ሰው የአሏህን መኖር የሚረጋገጠው እንደ ሲይግመን ፍሮይድ ማየት፣ መስማት፣ ማሽተት፣ መቅመስ እና መዳደስ በሚባሉት አምስት የስሜት ሕዋሳት ሳይሆን በመኽሉቅ፣ በፊጥራህ፣ በዐቅል፣ በነቅል፣ በአደብ ነው። እነዚህ ማረጋገጫዎች እንመልከት፦

፨ "መኽሉቅ" مَخْلُق ማለት "ፍጥረት" ማለት ሲሆን ፍጥረት ውጤት ከሆነ ፈጣሪ መንስኤ ነው፥ አሏህ ስለመኖሩ ጉልኅ ማረጋገጫ የፍጥረት ሙግት"cosmological argument" ነው፦
56፥58 በማኅፀኖች የምታፈሱትን አያችሁን? أَفَرَأَيْتُم مَّا تُمْنُونَ
56፥59 እናንተ ትፈጥሩታላችሁን? ወይስ እኛ ፈጣሪዎቹን ነን? أَأَنتُمْ تَخْلُقُونَهُ أَمْ نَحْنُ الْخَالِقُونَ

በተራክቦ ጊዜ በሴት ብልት ውስጥ የሚፈሰውን የወንድ ሕዋስ"sperm cell" ሰው አርገን መፍጠር አለመቻላችን በራሱ የተፈረጠውን የሚፈጥር ፈጣሪ እንዳለ አመላካች ነው፥ በመንስኤ እና በውጤት ሕግ ያለ ሠሪ ተሠሪ እንደሌለ ሁሉ ያለ ፈጣሪ ተፈጣሪ የለም። የፍጥረት ሙግት በመቀጠል ሰው እራሱን እራሱ አለመፍጠሩ የፈጠረውን ፈጣሪ እንዳለ በቂ ማሳያ ነው፦
52፥35 ወይስ ያለ አንዳች "ነገር" ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን? أَمْ خُلِقُوا مِنْ غَيْرِ شَيْءٍ أَمْ هُمُ الْخَالِقُونَ
52፥36 ወይስ ሰማያትን እና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም አያረጋግጡም፡፡ أَمْ خَلَقُوا السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ ۚ بَل لَّا يُوقِنُونَ

ፍጥረት ያለምንም ፈጣሪ እንዳልተፈጠረ እሙን እና ቅቡል ነው፥ ፍጥረትን ፍጡር አልፈጠረም። ሰማያትን እና ምድርን ሰው አለመፍጠሩ በራሱ ፈጣሪ መኖሩን ማረጋገጫ ነው። ይህንን ሙግት በምንጨታዊ፣ በስሙር፣ በርቱዕ ሙግት ስናዋቅረው፦
1. ማንኛውም ነገር መነሾ አለው፣
2. መነሾ ያለው ነገር መንስኤ"cause" አለው፣
3. ስለዚህ ፍጥረትን ያስገኘው መንስኤ ፈጣሪ ነው፦
46፥3 በሰማያት እና በምድር ውስጥ ለምእምናን ሁሉ እርግጠኛ ምልክቶች አሉ፡፡ إِنَّ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ لَآيَاتٍ لِّلْمُؤْمِنِينَ
7፥54 ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ አላህ ነው፡፡ إِنَّ رَبَّكُمُ اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ فِي سِتَّةِ أَيَّامٍ