Get Mystery Box with random crypto!

የኢብራሂም ሣራህ በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 51፥29 ሚስቱ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

የኢብራሂም ሣራህ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

51፥29 ሚስቱም እየጮኸች መጣች፥ ፊቷንም መታች፡፡ «መካን አሮጊት ነኝ» አለችም። فَأَقْبَلَتِ امْرَأَتُهُ فِي صَرَّةٍ فَصَكَّتْ وَجْهَهَا وَقَالَتْ عَجُوزٌ عَقِيمٌ

ኢብራሂም የአሏህ ነቢይ ሲሆን ሚስቱ ደግሞ ሣራህ ትባላለች፥ የኢብራሂም ሚስት ሣራህ ማንነቷ እንጂ ስሟ በቁርኣን አልተጠቀሰም። ቅሉ ግን በሐዲስ ላይ ኢብራሂም ከከለዳውያን ወደ ከነዓን በነበረው ስደት ትረካ ላይ ስሟን ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" ነግረውናል፦
ቡኻርይ መጽሐፍ 51, ሐዲስ 67
አቢ ሁረይራህ"ረ.ዐ." እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ኢብራሂም ከሣራህ ጋር ተሰደደ"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ ـ رضى الله عنه ـ أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏"‏ هَاجَرَ إِبْرَاهِيمُ بِسَارَةَ،

አሏህ ለተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" የኢብራሂም እንግዶች ወሬ በቁርኣን ተርኮላቸዋል፥ አምላካችን አሏህ መላእክትን ወደ ኢብራሂም በመላክ በኢሥሐቅ አበሰረው፦
51፥24 የተከበሩት የኢብራሂም እንግዶች ወሬ መጥቶሃልን? هَلْ أَتَاكَ حَدِيثُ ضَيْفِ إِبْرَاهِيمَ الْمُكْرَمِينَ
37፥112 በኢሥሐቅም አበሰርነው፡፡ ከመልካሞቹ የሆነ ነቢይ ሲሆን፡፡ وَبَشَّرْنَاهُ بِإِسْحَاقَ نَبِيًّا مِّنَ الصَّالِحِينَ
11፥69 መልክተኞቻችንም ኢብራሂምን በልጅ ብስራት በእርግጥ መጡለት፡፡ ሰላም አሉት፡፡ ሰላም አላቸው፡፡ ጥቂትም ሳይቆይ ወዲያውኑ የተጠበሰን የወይፈን ስጋ አመጣ፡፡ وَلَقَدْ جَاءَتْ رُسُلُنَا إِبْرَاهِيمَ بِالْبُشْرَىٰ قَالُوا سَلَامًا ۖ قَالَ سَلَامٌ ۖ فَمَا لَبِثَ أَن جَاءَ بِعِجْلٍ حَنِيذٍ
51፥28 ከእነርሱ መፍራትንም በልቡ አሳደረ፡፡ «አትፍራ» አሉት፡፡ በዐዋቂ ወጣት ልጅም አበሰሩት፡፡ فَأَوْجَسَ مِنْهُمْ خِيفَةً ۖ قَالُوا لَا تَخَفْ ۖ وَبَشَّرُوهُ بِغُلَامٍ عَلِيمٍ

መላእክት ስለ ኢሥሐቅ ለኢብራሂም ያበሰሩትን ብስራት ሣራህ ቆማ ታዳምጥ ስለነበር፦ "መካን አሮጊት ነኝ" በማለት የማይሆን መስሏት በስላቅ ሳቀች፥ አሏህም እርሱ ጥበበኛ ዐዋቂ መሆኑን በመናገር አበሰራት፦
51፥29 ሚስቱም እየጮኸች መጣች፥ ፊቷንም መታች፡፡ «መካን አሮጊት ነኝ» አለችም። فَأَقْبَلَتِ امْرَأَتُهُ فِي صَرَّةٍ فَصَكَّتْ وَجْهَهَا وَقَالَتْ عَجُوزٌ عَقِيمٌ
11፥71 ሚስቱም የቆመች ስትኾን ሳቀችም፡፡ በኢስሐቅ አበሰርናት፡፡ ከኢስሐቅም በኋላ በያዕቁብ አበሰርናት፡፡ وَامْرَأَتُهُ قَائِمَةٌ فَضَحِكَتْ فَبَشَّرْنَاهَا بِإِسْحَاقَ وَمِن وَرَاءِ إِسْحَاقَ يَعْقُوبَ
51፥30 ጌታሽ እንደዚህ ብሏል፦ «እነሆ እርሱ ጥበበኛ ዐዋቂ ነውና» አሏት፡፡ قَالُوا كَذَٰلِكِ قَالَ رَبُّكِ ۖ إِنَّهُ هُوَ الْحَكِيمُ الْعَلِيمُ

ከሳቀች በኃላ በኢሥሐቅ ስለተበሰረች ሚሽነሪዎች፦ "ከምን አንጻር እንደ ሳቀች ቅድመ ተከተሉን አልጠበቀም" በማለት ይተቻሉ፥ ቆማ የሳቀችውማ ለእርሷ ከመበሰሩ በፊት ለኢብራሂም በተበሰረው ብስራት ነው። ይህንን በተመሳሳይ ባይብል ላይ አለ፦
ዘፍጥረት 18፥9-11 እነርሱም፦ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም፦ በድንኳኑ ውስጥ ናት፡ አላቸው። እርሱም፦ የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች" አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች።

ፈጣሪ በመላእክቱ ለአብርሃም ስለ ልጅ ሲነግረው ሣራ በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሆኖ ትሰማ ነበር፥ ሣራ የሳቀችበት ልክ እንደ ቁርኣኑ፦ "ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል" በማለት ነበር፦
ዘፍጥረት 18፥12 ሣራም በራሷ፦ "ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል" ስትል ሳቀች"። וַתִּצְחַ֥ק שָׂרָ֖ה בְּקִרְבָּ֣הּ לֵאמֹ֑ר אַחֲרֵ֤י בְלֹתִי֙ הָֽיְתָה־לִּ֣י עֶדְנָ֔ה וַֽאדֹנִ֖י זָקֵֽן׃

ባይብሉ ታሪኩን ያቀረበው ሣራ የሳቀችው መላእክት ለአብርሃም ስለ ልጅ በነገሩት መሠረት እንደሆነ ሁሉ ቁርኣኑም ያስቀመጠው መላእክት ለኢብራሂም ስለ ልጅ በነገሩት መሠረት እንደሆነ በተዛማች ሙግት"textual approach" የሥነ-አፈታት ጥናት"hermeneutics" መረዳት ይቻላል፥ የተዛማች ሙግት ማለት አንዱ ሡራህ ላይ የተንጠለጠለ አሳብ በሌላ ሡራህ ላይ የሚጨርሰው ሲሆን ከቁርኣን የአነጋገር ውበት አንዱ ነው። አምላካችን አሏህ ስለዚህ እሳቦት እንዲህ ይነግረናል፦
39፥23 አላህ ከዜና ሁሉ መልካምን፣ ተመሳሳይ፣ ተደጋጋሚ የኾነን መጽሐፍ አወረደ፡፡ اللَّهُ نَزَّلَ أَحْسَنَ الْحَدِيثِ كِتَابًا مُّتَشَابِهًا مَّثَانِيَ تَقْشَعِرُّ

አሏህ ጥንት የተከናወኑትን ድርጊቶች በዜና የሚተርክልን ሙተሻቢህ በማድረግ አንዱ ሡራህ ላይ ተናግሮ ያንጠለጠለውን በሌላ ሡራህ ላይ የቀረውን ተመሳሳይ በማምጣት እና መሳኒይ በማድረግ አንዱ ሡራህ ላይ ተናግሮ ያንጠለጠለውን በሌላ ሡራህ ላይ የቀረውን በመድገም ነው፥ "ሙተሻቢህ" مُتَشَٰبِه ማለት "ተመሳሳይ" ማለት ሲሆን "መሳኒይ" مَّثَانِى ማለት "ተደጋጋሚ" ማለት ነው። አምላካችን አሏህ ቀደም ብለው የተከሰቱትን ክስተቶች የሚተርክልን መልካም፣ ተመሳሳይ እና ተደጋጋሚ ዜና ለእኛ እንድንማርበት ግሳጼ እና ማስታወሻ ነው፦
11፥120 ከመልክተኞቹም ዜናዎች ሁሉንም ልብህን በእርሱ የምናረካበትን እንተርክልሃለን፡፡ በዚህችም እውነቱ ነገር ለምእምናን ግሳጼ እና ማስታወሻ መጥቶልሃል፡፡ وَكُلًّا نَّقُصُّ عَلَيْكَ مِنْ أَنبَاءِ الرُّسُلِ مَا نُثَبِّتُ بِهِ فُؤَادَكَ ۚ وَجَاءَكَ فِي هَـٰذِهِ الْحَقُّ وَمَوْعِظَةٌ وَذِكْرَىٰ لِلْمُؤْمِنِينَ

"ለምእምናን ግሳጼ እና ማስታወሻ መጥቶልሃል" የሚለው ይሰመርበት! ሲጀመር ቁርኣን ላይ የሚመጣ ትረካ "እከሌ እከሌን ወለደ" የሚል የቀበሌ እና የእድር መጽሐፍ አይደለም። ሲቀጥል ለነቢያችን"ﷺ" የወረደላቸው የኢብራሂም ወሬ ኩረጃ ሳይሆን የሁሉን ዓዋቂው፣ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለን ምስጢር የሚያውቀው የአሏህ ንግግር ነው፦
33፥54 አላህ ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው። فَإِنَّ اللَّهَ كَانَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمًا
25፥6 «ያ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለን ምስጢር የሚያውቀው አወረደው፡፡ እርሱ መሓሪ አዛኝ ነውና» በላቸው፡፡ قُلْ أَنزَلَهُ الَّذِي يَعْلَمُ السِّرَّ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۚ إِنَّهُ كَانَ غَفُورًا رَّحِيمًا

ስለዚህ ከላይ ያለው የእናንተ የሚሽነሪዎች ኂስ ያልተጠና ኂስ ነው፥ ያልተጠና ኂስ የሚኃይስ ኃያሲ ለማሳለጥ ከሆነ መጥኔ ያጣ መኳተት ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቤ እሥልምና ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም