Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!            #ተዝካራ_ለጽዮን_ማር | ጸያሔ ፍኖት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
           #ተዝካራ_ለጽዮን_ማርያም _(ኅዳር ፳፩)
    እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከምድረ ግብጽ በሙሴ መሪነት ጠላት ገድሎ ባሕር ከፍሎ ካሻገራቸው በኋላ በደብረ ሲና ተራራ ታቦተ ጽዮንን ሰጥቷቸዋል፤ (ዘጸ 12፥51 ፣ ዘጸ 31፥18 ፣ ዘጸ 34፥1)፡፡ ፵ ዘመን ሙሉ መና ከደመና አውርዶ ውኃ ከጭንጫ አፍልቆ እየመገበ በሙሴ ምትክ ኢያሱን በአሮን ምትክ አልዓዛርን ሰጥቶ ምድረ ርስት አገባቸው፡፡ ከዚያ መስፍን ሲሞት መስፍን ካህን ሲሞት ካህን እያስነሳ ከዔሊ ደረሰ፡፡ ዔሊ ክህነት ከምስፍና ይዞ ፵ ዘመን አስተዳድሮ ሲደክም አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉ ልጆቹን የበላይና የበታች አድርጎ ሾማቸው፡፡ የዔሊ ልጆች ግን ክፉዎች ነበሩና በዔሊ ሥርዓት አልተጓዙም፤ በፊት የነበረውንም ሥርዓት አጠፉ፡፡ ካጠፉት ሥርዓት የተወሰኑት ቀጥሎ ተዘርዝረዋል፡፡
1. በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርቶ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት የሚጠፋ የደብተራ ኦሪት የሙሴና የአሮን ሥርዓት ነበር፤ ምን ያደርጋል ብለው አስቀርተዋል፡፡
2. መሥዋዕት የሚሠው ሰዎች ሲመጡ ከታረደው ስጡን ይላሉ፤ መሥዋዕት አቅራቢዎቹም ‹‹መጀመሪያ ስቡ ይጢስ፣ ደሙ ይፍሰስ ዐጥንቱ ይከስከስና ከዚህ በኋላ የወደዳችሁትን ታደርጋላችሁ›› ሲሏቸው ‹‹ብትሰጡን ስጡን ባትሰጡን በግድ እንወስዳለን›› እያሉ ብልት ብልት ስጋ እየነጠቁ ይወስዱ ነበር፡፡
3. ጽዮንን  መቃጠሪያ አደረጓት፤ ሴቶችም ይህንማ መቼ ከባሎቻችን አጣነው ብለው ቀርተዋል፡፡
   ዔሊም ይህን ሰምቶ ‹‹ልጆቼ የምሰማባችሁ ይህ ነገር መልካም አይደለም፤ እንዲህ አታድጉ ሰውስ ሰውን ቢበድል በእግዚአብሔር ያስታርቁታል ሰው ግን ከእግዚአብሔር ጋራ ቢጣላ በማን ያስታርቁታል? ተው›› አላቸው፤ ልጆቹ ግን አልሰሙትም፤ (1ሳሙ 2÷22-26)፡፡ በቤተ መቅደስ ውስጥ ጽዮንን ለሚያገለግል ለሳሙኤል እንደነገረው እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ጋራ ጦርነት ገጥመው ድል ኾኑ፡፡ እነሱም ‹‹ታቦተ ጽዮንን ባንይዝ ነው›› አሉ፡፡ እግዚአብሔር የአፍኒንና ፊንሐስ ሞት ፈቃዱ ነውና ታቦተ ጽዮንን ይዘው አብረው ዘመቱ፡፡ አሕዛብም እልልታውን ሰምተው ‹‹ወዮልን የእስራኤል አማልክት መጡብን›› ብለው ተጨነቁ፡፡ ነገር ግን አሕዛባውያኑ በድፍረት ጦርነቱን ገጠሙ፡፡ በጦርነቱም አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ፤ ታቦተ ጽዮንም ተማረከች፡፡ እስራኤል ከቀድሞው የበለጠ ፴ ሺህ እግረኞች አለቁ።

በዚህም ካህኑ ዔሊ በደብተራ ኦሪት ፊት ለፊት በወንበር ላይ ተቀምጦ የታቦተ ጽዮንን ነገር ያወጣ ያወርድ ነበር፡፡ ከዚያም አንድ የብንያማዊ ሰው ልብሱን ቀዶ እየሮጠ ሲመጣ ዔሊ ‹‹ከወዴት መጣህ?›› ብሎ ቢጠይቀው ‹‹ትናንት ከሰልፍ አምልጨ የመጣሁ ነኝ›› አለው፡፡ ከጦርነቱ አምልጦ የመጣው ብንያማዊም ለዔሊ ልጆቹ እንደሞቱ፣ እስራኤላውያን እንዳለቁና ታቦተ ጽዮን እንደተማረከች ነገረው፡፡ ዔሊም ‹‹ልጆቼ ብመክራቸው እንቢ ብለዋል ታቦተ ጽዮን ግን እንዴት ትማረካለች?›› ብሎ አለቅሳለሁ ሲል ከወንበሩ ወድቆ ሞቷል፡፡ ‹‹ዔሊ የ፺፰ ዓመት ሽማግሌ ነበርና ከወንበሩ ወደቀ ዐንገቱ ተሰብሮ ሞተ›› እንዲል (1ሳሙ 4÷9-18)።
   
   ፍልስጥኤማውያንም ታቦተ ጽዮንን ማርከው ወደ አዛጦን ወስደው በዳጎን አጠገብ አድርገው ሄዱ፡፡ በነጋታው ሲገቡ ዳጎን በግንባሩ ወድቆ አገኙት፤ እንደነበረው አድርገውት ቢሄዱም አሁንም በነጋታው ሲመለሱ እጅ እግሩ ተቆራርጦ ደረቱ ቀርቶ አገኙት፡፡ ከዚያ ታቦተ ጽዮንን ወደ ጌት ሰደዷት፤ ከዚያም ወደ አስቀሎና ኢሎፍሊ እየተዘዋወረች ለሰባት ወር ከተቀመጠች በኋላ ባደረገችው የኃይልና የመቅሰፍት ተአምር ቀንበር ያልተጫነባቸው ላሞች ጠምደው በአዲስ ሠረገላ ጭነው ካሳ ወርቅ ሠርተው ላኳት፡፡ ላሞቹም ያለ ነጅ ወደ እስራኤል ሀገር አምጥተው በቤትሳሚስ ከኢያሱ እርሻ አጠገብ ደርሰው ቆሙ፡፡ የቤትሳሚስም ሰዎች ሠረገላውን ፈልጠው ላሞቹን አርደው መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚያ ወደ አሚናዳብ ቤት መጥታ ልጁ አልዓዛር እያገለገላት ዳዊት እስኪያመጣት ድረስ በዚያው ሃያ ዓመት ተቀምጣለች፡፡ ከዚያም ታቦተ ጽዮን ከአሚናዳብ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ (እስራኤል) በዳዊት የንግሥና ዘመን ተመልሳለች፤ (2ሳሙ 6፥1-19)፡፡

    በተጨማሪም ነቢዩ ዘካርያስ ጽዮንን በተቅዋመ ማኅቶት አምሳል ያየበት፣ ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የገባበት፣ በዮዲት ጉዲት ጊዜ በዝዋይ ደሴት ከ፵ ዓመት በላይ ቆይታ ሰላም ሲሆን ተመልሳ አክሱም የገባችበት ዕለት በመሆኑ እንዲሁም አብርሃና አጽብሐ በአክሱም ከተማ ከ፫፻፴፮-፫፻፴፱ ዓ.ም ቤተ መቅደሱን ሠርተው ቅዳሴ ቤቱን ያከበሩበት ስለሆነ የበዓሉ መታሰቢያ ኅዳር ፳፩ ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን አሜን!
(ውድ አንባቢያን ስለ ዔሊ ልጆች ጥፋት እና ስለ ታቦተ ጽዮን መማረክ ሙሉውን ታሪክ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ከምዕራፍ ሁለት እስከ ምዕራፍ ሰባት ያለውን ያንብቡት)፡፡

               ወስብሐት   ለእግዚአብሔር!
ምንጭ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ፣ መድበለ ታሪክ

@orthodoxy_eywet
@orthodoxy_eywet
@orthodoxy_eywet