Get Mystery Box with random crypto!

❖ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን “ከሰው የበለጠች ከመላእክት ኹሉ የከበረች ልጅ ትወልዳላችኊ' ብሎ | 💖 ዕፀጳጦስ 💖

❖ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን “ከሰው የበለጠች ከመላእክት ኹሉ የከበረች ልጅ ትወልዳላችኊ" ብሎ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለሐና ነግሯት በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን ነሐሴ ሰባት እሑድ ተፀንሳለች፤ በእናቷ ማሕፀን ሳለችም “መንፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ” እንዲል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጥንተ አብሶ ባመጣው መርገም እንዳትያዝ ጠብቋታል፡፡

❖ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም መፀነስ ከሊቃውንት መኻከል አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ
“ሚ ቡርክት ወቅድስት ይእቲ
ሰዓተ ትፍሥሕት ሐና ዘጸገየተኪ ባቲ
ወፈረየኪ ለሕይወት ኢያቄም መዋቲ
እሴብሕ ተአምረኪ ርግብየ አሐቲ
ወድኀኒተ ኲሉ ዓለም እስመ ኮንኪ አንቲ”
(ሐና አንቺን የፀነሰችባት የደስታ ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ ሟች ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን ያፈራባት ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ አንዲቱ ርግቤ ማርያም አንቺ የዓለሙ ኹሉ መድኀኒት ኾነሻልና ታምርሽን አመሰግናለኊ) በማለት ዓለምን ኹሉ በደሙ ፈሳሽነት ያዳነ ንጉሣችን፣ ፈጣሪያችን ክርስቶስን በድንቅ ተአምር ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ የወለደችልን ምክንያተ ድኂን ርግበ ሰሎሞን የተባለች የቅድስት ድንግልን የመፀነሷን ነገር በአድናቆት ገልጸዋል፡፡

❖ ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በአርጋኖን መጽሐፉ ላይ የዜና ጽንሰቷን ነገር ሲገልጽ “ወይእዜኒ ኦ ውሉደ እግዚአብሔር ወማኅበረ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናስተብፅዖሙ ለሐና ወለኢያቄም ...” (አኹንም የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆችና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማኅበሮች ሆይ ይኽቺን የተባረከችና የተመረጠች ሙሽራ የወለዱልንን ኢያቄምንና ሐናን እናመስግናቸው የማትነቀፍ የእስራኤል ድንግልን የተባረከችዋን ፍሬ ያፈራችበትን ንጽሕት የምትኾን የሩካቤያቸው ዕለት እንደምን ያለች ዕለት ናት? ከይሁዳ ወገን ለኾነችው ንጽሕት ርግብ መፀነስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ የጾታዊ ተዋሕዷቸው ቀን ይኽቺ እንዴት ያለች የተመረጠች ቀን ናት፤ ለንጉሥ ማደሪያ አዳራሽ መመሥረት የተደረገባት (የኾነባት) የደስታ ቀን እንዴት ያላት ቀን ናት?) በማለት የፅንሰቷን ነገር አድንቋል።

❖ ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም መጽሐፉ በቊ ፴፰ ላይ “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ” (ድንግል ሆይ በኀጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለሽም በሕግ በኾነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ) በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንተ ኀጢአት ካመጣው መርገም በፅንሰቷ ጊዜ እንዳትያዝ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተጠበቀ መኾኑን ተናግሯል፡፡

❖ “ወእምድኅረ ስድስቱ አውራኅ ተዐውቀ ፅንሳ ለሐና” ይላል፤ ከስድስት ወርም በኋላ የሐና ፅንሷ እየታወቀ ሲመጣ ጎረቤቶቿ መፅነሷን ይረዱ ዘንድ በአድናቆት ማሕፀኗን ይዳስሱ ነበር፤ በተለይም ዐይኗ የታወረ የሐና ዘመዷ የአርሳባን ልጅ የምትኾን አንዲት ሴት የሐናን ማሕፀን ዳስሳ ዐይኗን ብትነካው በርቶላት በታላቅ ደስታ ኾና “ብፅዓን ለኪ ኦ ሐና እስመ እም ፍጥረተ ዓለም አልቦ ዘከማኪ ዘይፌውስ በከርሡ አዕይንተ ዕውራን” (ሐና ሆይ ብፅዓን ይገባሻል ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እንዳንቺ በማሕፀኑ የዕውራንን ዐይን የሚያበራ የለምና) በማለት አመስግናታለች፤ ከዚኽ በኋላ ዝናዋ በሀገሩ ኹሉ ተሰምቶ ሕሙማን ኹሉ ማሕፀኗን እየዳሰሱ ይፈወሱ ነበር፡፡

❖ አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ ይኽነን ሲገልጹ፦
“ጸግይየ ሣዕረ ዘኪሩቤል ልሳነ
ተአምረኪ በነጊር እመ ኢፈጸምኩ አነ
ባሕቱ አአኲት ማርያም ዘጾረተኪ ማሕፀነ
እንዘ ሀለወት ፀኒሳ ኪያኪ ርጢነ
ለለገሰስዋ ላቲ ትፌውስ ዱያነ”
(ሳርን የኾንኊ እኔ የኪሩቤል አንደበትን ገንዘብ አድርጌ ታምርሽን በመንገር በማስተማር ባልፈጽምም ነገር ግን ማርያም የተሸከመቺሽን ማሕፀን አመሰግናለኊ፤ መድኀኒት አንቺን ፀንሳ ሳለች ርሷን የዳሰሷትን ድዉያንን ኹሉ ትፈውስ ነበር) በማለት እመ መድኅነ ዓለም ገና ሳትወለድ የተሠራውን ድንቅ ተአምር አመስግነዋል፡፡

❖ ይኽ የቅድስት ድንግል ማርያም የፅንሰት በዓል በመላው ዓለም የሚታወቅ ሲኾን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የአምላክ እናት የተፀነሰችበት ይኽነን በዓል ነሐሴ ፯ ቀን በታላቅ ድምቀት በማሕሌት፣ በቅዳሴ የምታስበው ሲኾን በዓሉም “ፅንሰታ ለማርያም” በመባል ይታወቃል፤ በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በዓሉን “The conception of the Theotokos” (የአምላክ እናት መፀነስ) በማለት ሲያከብሩት ወሩን ግን የልደት በዓልን ለማክበር በሚዘጋጁበት በታኅሣሥ አድርገው በ፱ኛው ቀን “December 9” ላይ ያስቡታል፡፡
(ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ፤ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ የታተመ)
[የአምላክ እናት ሆይ እንወድሻለን]
❖መልካም በዓል❖