Get Mystery Box with random crypto!

[ነሐሴ 7 ፅንሰታ ለማርያም (የአምላክ እናት የተፀነሰችበት)] በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደ | 💖 ዕፀጳጦስ 💖

[ነሐሴ 7 ፅንሰታ ለማርያም (የአምላክ እናት የተፀነሰችበት)]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
❖ ነሐሴ 7 የአምላክ እናት የፅንሰቷ በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል። በነገረ ማርያም ላይ እንደተጻፈ በእናቷ በሐና በኩል ያሉ የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ጴጥሪቃ ቴክታ ሲባሉ “ወኮኑ ክልኤሆሙ ጻድቃን ወፈራህያነ እግዚአብሔር ወይትአመንዎ ለአምላኮሙ በጥቡዕ ልብ እንበለ ኑፋቄ” ይላል (ኹለቱም ሰዎች ደጋጐችና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ያለምንም መጠራጠር በፍጹም ልቡናቸው በአምላካቸው የሚተማመኑ ነበሩ)።

❖ እነርሱም በጊዜው ይኽ ቀራችኊ የማይባሉ ባለጠጎች ነበሩ፤ ከሀብታቸው ብዛት የተነሣ ወርቁን ብሩን እንደ ዋንጫ እያሠሩ በላሙ በበሬው ቀንድ ላይ ይሰኩት ነበር፤ ይኽን ያኽል አቅርንተ ወርቅ፣ አቅርንተ ብሩር እየተባለ ይቈጠር ነበር፤ የዕንቊ ጽዋ እንኳ ፸፣ ፹ ያኽል ነበራቸው ይላል ፡፡

❖ ከዕለታት ባንዳቸው ጴጥሪቃ ወደ ቤተ መዛግብቱ ገብቶ የሀብቱን ብዛት አይቶ ሚስቱ ቴክታን “ለመኑ ዘዘገብነ መዛግብቲነ አልብነ ውሉድ ዘይወርሰነ አንቲኒ ወአነሂ መካን ንሕነ” (የሰበሰብነው ገንዘብ ስንኳን ለኛ ለልጅ ልጅ ይተርፍ ነበር አንቺም እኔም መካኖች ነንና የሚወርሰን ልጅ የለንም) በማለት ተናገራት፤ ርሷም እንዲኽ ማለቱ ወላድ የፈለገ መስሏት በሐዘን ኾና “አምላከ እስራኤል ከኔ ልጅ ባይሰጥኽ ከሌላ ይሰጥኽ ይኾናልና ሌላ አግብተኽ ውለድ” አለችው።

❖ ርሱም “አነሂ ኢይፈቅድ የአምር አምላከ እስራኤል ከመ ኢየሐስቦ ለልብየ” (ይኽንስ እንዳላደርገው በልቤም እንዳላስበው የእስራኤል አምላክ ያውቃል) በማለት ተናገረ፡፡ ርሷም ዐዝና ሳለ ራእይ ታያለች፤ ነጭ እንቦሳ ከማሕፀኗ ስትወጣ እንቦሳዪቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ሰባት ስትደርስ ሰባተኛዋ ጨረቃን ስትወልድ፤ ጨረቃ ፀሓይን ስትወልድ አየች።

በአድናቆት ለባሏ “ግሩም ግብሩ ለእግዚአብሔር ትማልም ርኢኩ በሕልምየ ጸዐዳ ጣዕዋ ወጽአት እምከርሥየ ይእቲኒ ወለደት ጸዐዳ ጣዕዋ እስከ ሰብዐቲሆን ወሳብዕታኒ ወለደት ወርኀ ወወርኅኒ ወለደት ፀሓየ” (የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤ ትናንትና ማታ በሕልሜ ነጭ ጥጃ ከማሕፀኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ደግሞ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንደዚኽ እየኾነ እስከ ሰባት ትውልድ ሲደርሱ ሰባተኛዪቷም ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋ ደግሞ ፀሓይን ስትወልድ አየኊ) በማለት አስረዳችው።

❖ ርሱም በእጅጉ ተደንቆ ሕልም ወደሚፈታ ሰው ዘንድ በመኼድ የሚስቱን ራእይ ነገረው፤ ያም ሕልም ተርጓሚ ምስጢር ተገልጾለት ሰባት አንስት ጥጆች መውለዳችኊ ሰባት ሴቶች ልጆች ይወለዳሉ፤ ነጭ መኾናቸው ደጋጎች ልጆች መኾናቸው ሲኾን “ወሳብእታኒ ትከብር እመላእክት ወትትሌዐል እምኲሉ ሰብእ ወበእንተ ፀሓይኒ ኢያእመርኩ” (ሰባተኛዪቱ ጨረቃን መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ናት፤ የፀሓይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም) በማለት ተረጐመለት፤ ርሱም ለሚስቱ ነገራት፤ ርሷም “የእስራኤል አምላክ የሚያደርገውን ርሱ ያውቃል” በማለት ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡

❖ ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች ስሟንም ሔሜን አሏት፤ ሔሜን → ዴርዴን ወለደች፤ ዴርዴም → ቶናን፤ ቶናም →ሲካርን ወለደች፤ ሲካርም→ ሴትናን፤ ሴትናም →ሔርሜላን ወለደች፤ ሔርሜላም የተከበረችና የተመረጠች ዓለሙን ኹሉ ለፈጠረ ጌታ አያት ለመኾን የበቃች ሐናን ወልዳለች።

የዝማሬና የትንቢት ጸጋ ከእግዚአብሔር የተሰጡት ክቡር ዳዊት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በተለይም ስለ ሥርወ ልደቷ አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት በመዝ ፹፮፥፩‐፯ ላይ “መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን” (መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ላይ ናቸው) በማለት የእመቤታችን ሥርወ ልደት ከቤተ መንግሥት ከቤተ ክህነት ከኾኑት ከተቀደሱት ከቅዱሱ ኢያቄምና ከቅድስቲቱ ሐና የመኾኑን ነገር በምሳሌ የገለጸው።

❖ ሐና በመልካም አስተዳደግ አድጋ አካለ መጠን ስታደርስ ከነገደ ይሁዳ ከመንግሥት ወገን የተወለደ የቅስራ ልጅ የአልዓዛር የልጅ ልጅ ከሚኾን ከኢያቄም ጋራ አስተጫጭተው አጋቧት፡፡ ሐናና ኢያቄምንም “ወክልኤሆሙ ኄራን ወሥሙራን እሙንቱ ወየሐውሩ በሕገ እግዚአብሔር እስመ እግዚአብሔር ኀረዮሙ ወአፍቀሮሙ ትካት” ይላቸዋል።

እግዚአብሔርን የሚወድዱ በሕጉ የሚኖሩ ደጋጎችና አምላክም የመረጣቸው ሲኾኑ ሐና መካን በመኾኗ ምክንያት ኹለቱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት በመኼድ ለዐይናቸው ማረፊያ ለልባቸው ተስፋ የሚኾን ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ እንደነበር፤ “Protoevangelium of James” (ፕሮቶቫንጊሊዩም ኦፍ ጀምስ) የሚለው ያዕቆብ የጻፈው ጥንታዊዉ መጽሐፍ በስፋት ይገልጻል፡፡

❖ ከዕለታት ባንደኛው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ሲመለሱ “ወርእዩ አርጋበ እንዘ ይትፌሥሑ ምስለ ውሉዶሙ” ይላል ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አይተው ሐና “አቤቱ ጌታዬ ግዕዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠኽ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሣኸኝ” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፤ ወዲያው ሱባዔ ይገባሉ፤ ኢያቄም ወደ በረሓ ኼዶ ሲጸልይ ሐና ደግሞ በቤቷ ዙሪያ ባለው የተክል ቦታ ሱባዔ ያዘች፤ በሱባዔያቸው ፍጻሜ ኹለቱም ራእይ አይተው ተነጋግረዋል፡፡

❖ “ይቤላ ኢያቄም ለሐና ብእሲቱ እንዘ ይትረኀዉ ሰብዐቱ ሰማያት ዖፍ ጸዐዳ መጽአ ኀቤየ ወነበረ ዲበ ርእስየ” ይላል ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዎፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየኊ ብሎ የተገለጸለትን ለሐና ነግሯታል፤ ይኸውም የራእዩ ምስጢር፡- ዎፍ የተባለው አካላዊ ቃል ክርስቶስ ሲኾን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፤ ከላይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየኊ ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ ሲያጠይቅ ሲኾን፤ ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ምልአቱ፣ ስፍሐቱ፣ ርቀቱ፣ ልዕልናው፣ ዕበዩ ናቸው፡፡

❖ ሐናም ተገልጾላት “ትቤሎ ሐና ለኢያቄም ብእሲሃ አነኑ ርኢኩ በሕልምየ ርግብ ጸዐዳ መጽአት ኀቤየ ወነበረት ዲበ ርእስየ ወቦአት ውስተ እዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርሥየ” ይላል ለባሏ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በዦሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየኊ ብላዋለች።

ይኽ የራእይ ምስጢር፡- ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትኾን፤ ነጭነቷ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፤ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ ወደ ዦሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየኊ ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በዦሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መኾኗን ሲያጠይቅ ነው፡፡

❖ ኢያቄምና ሐናም ይኽነን ራእይ ሐምሌ ፴ ቀን ካዩ በኋላ “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል፤ ሴትም ብንወልድ ለቤተ እግዚአብሔር መጋረጃ ፈትላ ትኑር” ብለው ስእለት ከተሳሉ በኋላ ራእይ አየን ብለው ዕለቱን አልተገናኙም፤ አዳምንና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሏት” ብሎ የተናገረው አምላክ ለእኛም ይግለጽልን ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ እየብቻቸው ሰነበቱ።