Get Mystery Box with random crypto!

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከመስከረም 30 ጀምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይሰጣል። የተፈታኝ | Ministry of education®

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከመስከረም 30 ጀምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይሰጣል።

የተፈታኝ ተማሪዎች መብቶች፦

➭ ከፈተና ጥያቄ ውጪ ማንኛውንም ያልተረዳውን ነገር ጠይቆ የመረዳት መብት አላቸው።

➭ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የምግብ፣ የህክምና አገልግሎት፣ የማደሪያ ክፍል፣ ፍራሽ እና ትራስ የማግኘት መብት አላቸው።

➭ ማንኛውም ተፈታኝ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያለውን የቤተ መፅሐፍት፣ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የሻወር፣ የካፍቴሪያዎች፣ የሚኒ ሱፐር ማርኬቶች፣ የተለያዩ ሱቆች እንዲሁም የመናፈሻና መዝናኛ አገልግሎቶችን የመጠቀም መብት አላቸው።

➭ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የጋራ የደህንነት ጥበቃ የማግኘት መብት አላቸው።

➭ በፈተና ሰዓት መፈተኛ ክፍል ገብቶ ብርሃናማ የመፈተኛ ቦታ፣ ወንበርና መፃፊያ ጠረጴዛ የማግኘት መብት አላቸው።

➭ ፈተና ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀድሞ ስለፈተናው ገለጻ (ኦሬንቴሽን) የማግኘት መብት አላቸው።

የተፈታኝ ተማሪዎች ግዴታዎች፡-

➤ ማንኛውም ተፈታኝ በፈተና ማዕከልና መፈተኛ ክፍል አድሚሽን ካርድ ይዞ የመገኘት ግዴታ አለበት።

➤ ማንኛውም ተፈታኝ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጣ የትምህርት ቤት ወይም የነዋሪነት መታወቂያ ይዞ መገኘት አለበት።

➤ ማንኛውም ተፈታኝ ወደ ግቢ ከመግባቱ በፊትና ወደ መፈተኛ ክፍል ከመግባቱ በፊት ሙሉ አካላዊ ፍተሻ የመፈተሽ ግዴታ አለበት።

➤ ማንኛውም ተፈታኝ በዩኒቨርሲቲ ግቢና በመፈተኛ ክፍል የተከለከሉ ዕቃዎችን መያዝ የለበትም።

➤ ማንኛውም ተፈታኝ እርሳስ፣ ላጲስና የእርሳስ መቅረጫ ይዞ መገኘት አለበት።

➤ ማንኛውም ተፈታኝ የፈተና ደንብን የማክበር ግዴታ አለበት።

➤ ማንኛውም ተፈታኝ በፈተና ማዕከል/በመፈተኛ ክፍል ውስጥ የፈተና አስፈጻሚዎች የፈተና አስተዳደር ሥራን ውጤታማ ለማድረግና ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚያደርጉትን ጥረት የመተባበር ግዴታ አለበት።

➤ ማንኛውም ተፈታኝ ፈተና ከመጀመሩ በፊት መፈተኛ ክፍል የመገኘት ግዴታ አለበት።

➤ ተፈታኙ ፈተናው ሳይጠናቀቅ ከፈተና ክፍል የሚወጣ ከሆነ የፈተና ጥያቄ የያዘውን ቡኩሌት ለፈታኙ የማሰረከብ ግዴታ አለበት።

➤ ማንኛውም ተፈታኝ ወደተመደበበት ዩኒቨርሲቲ ሲመጣ አንሶላ፣ ብርድ ልብስ እና የትራስ ጨርቅ ይዞ የመምጣት ግዴታ አለበት።

ለተፈታኝ ተማሪዎች የተፈቀዱ ነገሮች፦

➣ አዲስ ወይም ቀድሞ ለመማር እና ለማጥናት ሲጠቀሙበት የነበሩ ማስተወሻ ደብተር፣ የትምህርት መፅሐፍ፣ መንፈሳዊ/ኃይማኖታዊ መፅሐፍት፣ ባዶ ወረቀት

➣ ደረቅ ምግቦች (ጩኮ፣ በሶ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ቆሎ….)

➣ ገንዘብ (ብር)

➣ የልብስ ወይም የእጅ ቦርሳ፣ የግል ልብስ፣ ጫማ

➣ የግል ንጽህና መጠበቂያዎች (ሳሙና፣ ሞዴስ፣ የጥርስ ብሩሽ፣ የጥርስ ሳሙና፣ ፎጣ፣ ሶፍት፣ ሻምፖ፣ ኮንዲሽነር፣ ሎሽን፣ ቻፕስቲክ፣ የጸጉር ቅባት፣ የፊት ቅባት)

ለተፈታኝ ተማሪዎች የተከለከሉ ነገሮች፦

➣ ማንኛውንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው፡፡

➣ ማንኛውንም ዓይነት ስለት እና ሹልነት ያላቸውን ብረታ ብረቶችና ጠንካራ ፕላስትኮች ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው።

➣ ማንኛውም ድምጽ የሚቀዳ፣ ፎቶ የሚያነሳ፣ ቪዲዮ የሚቀርጽ፣ ከቴሌ መስመርም ሆነ ከቴሌ መስመር ውጭ መልዕክት በዲጂታል መንገድ የሚሰጥ ወይም የሚቀበል የግል ዕቃ/መሳሪያ/የቴክኖሎጂ ውጤት፣ ስልክ፣ አይ-ፓድ፣ ታብሌት፣ ኮምፕዩተር፣ ላፕቶፕ፣ ስማርት ሰዓት፣ ማጂክ ብዕር/እስክሪብቶ፣ ማጂክ ኮት/ጃኬት እና ሌሎች ማንኛቸውም ፎቶ፣ ምስል እና ድምጽ የሚቀርጹ የኤሌክትሮኖክስ መሣሪያዎችን በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥም ሆነ ግቢ ዙሪያ ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡

➣ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት የግል ፍላሽ ዲስክ፣ ሃርድ ዲስክ፣ ሲዲ፣ ሚሞሪ፣ ሚሞሪ ሪደር፣ ኦ-ቲጂ ኮንቨርተርና መሰል ዕቃዎችን ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡

➣ ማንኛውም አደንዛዥ እጾች (ጫት፣ ሲጋራ፣ በሐኪም ማዘዣ የሌለው መድኃኒት)፣ ህክምና መስጫ መርፌ መያዝ ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡

➣ ማንኛውም ዓይነት የአልኮል መጠጥ ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡

➣ ማንኛውም ዓይነት የአንገት ሐብል፣ የጸጉር ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ የጣት ቀለበት፣ የእጅ አንባር፣ አድርጎ ወይም ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው፡፡ (ከልሙጥ የጋብቻ ቀለበት በስተቀር)

➣ ፈተና ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ወደ ፈተና ክፍል መግባት እና ፈተናው ተጀምሮ 45 ደቂቃ ሳይሞላ ከፈተና ክፍል መውጣት የተከለከለ ነው፡፡

➣ ተፈታኙ ፈተናው ሳይጠናቀቅ ከፈተና ክፍል የሚወጣ ከሆነ የፈተና ጥያቄ የያዘውን ቡኩሌት ይዞ መውጣት ተከለከለ ነው፡፡

➣ በፈተና ሰዓት በመፈተኛ ክፍል ውስጥ ማስቲካ መያዝም ሆነ መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡

➣ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በግልም ሆነ በቡድን መጮህ ወይም በጣም ከፍተኛ ድምጽ ማሰማት የተከለከለ ነው፡፡

ተጨማሪ ትምህርታዊ መረጃ ለማግኘት ቻናላችን ይቀላቀሉ

@TMIHIRT_MINISTER
@TMIHIRT_MINISTER