Get Mystery Box with random crypto!

#ሰኔ_21 ዝ ክ ረ - ቅ ዱ ሳ ን በስመ አብ | ✝️(ትምህርተ ግዕዝ)✝️

#ሰኔ_21


ዝ ክ ረ - ቅ ዱ ሳ ን


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን፡፡


እ ን ኳ ን አ ደ ረ ሳ ች ሁ!


ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት...

✞ ሰ ኔ ጐ ል ጐ ታ ✞

ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም በዚህ ቀን (ሰኔ ፳፩) ልጇን ወዳጇን ጐልጐታ ላይ ለኃጥአን ምሕረትን ለምናዋለች። ጌታችንም "ስምሽን የጠራውን፣ በቃል ኪዳንሽ ያመነውን ሁሉ እምርልሻለሁ።" ብሏታል።

የድንግል እመቤታችን ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ጣዕመ ፍቅሯና በረከቷ በሁላችን ላይ ይደርብን።

✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣

ትናንት ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ ሐዋርያት ወረደ። ፊልዽስዩስ በምትባል ሃገር በዼጥሮስ እጅ የመጀመሪያዋን ቤተ_ክርስቲያን አነጸ። በዚህች ዕለት ደግሞ አእላፍ መላዕክትን: ሰማያውያን ቅዱሳንን እና እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዟት ወረደ።

ሐዋርያቱ አብዛኞቹ እዛው ሲጸልዩ አድረው ነበርና ጌታችን ከቅዳሴው በፊት 2 ነገሮችን አሳየ:-
1. አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያኗን በድንግል እናቱ ስም አክብሮ ሥርዓተ ቤተ ክርረስቲያንን አሳየ።
2. ቀጥሎ ደግሞ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ_ዼጥሮስን ከመካከል አቁሞ "አርሳይሮስ" ሲል ሾመው። ይኼውም የዓለም ሁሉ ሊቀ ዻዻሳት (ፓትርያርክ) ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት "አክዮስ" እያሉ 3 ጊዜ አሰምተው ጮሁ። አክዮስ ማለት በግዕዙ "ይደልዎ": በዐማርኛው ደግሞ "ይገባዋል: ያሥምርለት" እንደ ማለት ነው።

ጌታችን ይሕን ከከወነ በኋላ ይቀድስ ዘንድ ጀመረ።
✟ አማናዊት ማሕደሩን ድንግል ማርያምን መንበር አድርጎ:
✟ ቅዱስ ዼጥሮስ እንደ ተራዳኢ ካህን ቆሞ:
✟ ቅዱስ_እስጢፋኖስ ሠራኢ ዲያቆን ሆኖ:
✟ ሐዋርያት ድንግልን ከበው:
✟ መላእክተ ብርሃን በክብራቸው ቁመው ጌታችን ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወዳጆቹ አቀበለ።

በዚያች ዕለት በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይችል ደስታ ተደረገ። ከቅዳሴ በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን አዘዛቸው። "ከዚህ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም በእናቴ በማርያም ስም አብያተ ክርስቲያናትን እነጹ። ይህችን ዕለት የሚያከብራትን አከብረዋለሁ።" ብሏቸው ከድንግል እናቱ ከመላዕክቱ ጋር ዐረገ።

✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣

#ቅዱስ_ቶማስ

ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ይታሰባል። ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ። ቅዱስ ቶማስም ያመኑትን "ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሸሹ" ብሎ መከራቸው። ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ መሸታ ቤት ይገባል። ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ መሸተኛዋ ሴት እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል ሰይፍ አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት።

እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል። የሠራው ሥራ (መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው። በማግስቱ ቅዱስ ቶማስ ነገሩን ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ ማነው?" ሲል ጠየቀ። ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል ዝም አለ። ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና "ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ። ሰውየው ተራውን ጠብቆ ሊያነሳ ሲል እጁ ሰለለች።

ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው። እሱም እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ። ቅዱስ ቶማስ ግን ሕዝቡ ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን አምጡልኝ" አለ። የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል . . .
የገደልኩሽ እኔ: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው . . . ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው።

እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች። ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል።

ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን።

-----------------------------------------------------------
"ስለ ጽዮን ዝም አልልም . . .
አሕዛብም ጽድቅሽን: ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ። የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።" (ኢሳ. 62:1-3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"። /የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

#ስንክሳር_ዘወርሃ_ሰኔ
https://t.me/DIYAKONAE