Get Mystery Box with random crypto!

በስጋ ተገለጠ በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 5፥72 እነዚያ | Tiriyachen | ጥሪያችን

በስጋ ተገለጠ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

5፥72 እነዚያ *«አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው»* ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ لَقَدْ كَ. فَ. رَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ

በክርስትና ስልታዊ ሥነ-መለኮት”systematic theology” የአምላክ ሰው መሆን አስተምህሮት “ተሰግዎት”Incarnation” ሲባል በአገራችን “ሚስጥረ-ስጋዌ” ይሉታል፣ “ስጋዌ” የሚለው ቃል "ስግው” ማለትም “ስጋ” ከሚለው የመጣ ነው፣ መለኮት በትስብእት ተገለጠ ብለው ድምዳሜ ላይ ያደረሳቸው ይህ ጥቅስ ነው፦
1 ጢሞቴዎስ 3፥16 እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ *"እርሱ በሥጋ የተገለጠ"*፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ *"በክብር ያረገ"*። (NIV)

እዚህ አንቀጽ ላይ በ 330 ዓመተ-ልደት የተዘጋጀው ኮዴክስ ሳይናቲከስ እና በ 350 ዓመተ-ልደት የተዘጋጀው ኮዴክስ ቫቲካነስ ላይ እንዲህ ተቀምጧል፦
"እርሱ በሥጋ የተገለጠ" Ὃς ἐφανερώθη ἐνσαρκί,

"ሆስ" Oς ማለት አንጻራዊ ተውላጠ-ስም ሲሆን "እርሱ" ማለት ነው፤ "እርሱ" የተባለው "ክርስቶስ" ነው። ነገር ግን በ 400 ዓመተ-ልደት የተዘጋጀው ኮዴክስ አሌክሳንድሪየስ ላይ ሌላ ተቃራኒ ቃል ተቀምጧል፦
"አምላክ በሥጋ የተገለጠ" Θς ἐφανερώθη ἐνσαρκί,

በግሪክ ኮይኔ አስራ አምስተኛው ፊደል "ሆሞክሮን" O  መሃል ላይ "አግድም ሰረዝ" - ሲጨመርበት ስምተኛው ፊደል "ቴታ" Θ ይሆናል፤ በአስራ ስምንተኛው ፊደል "ሲግማ" ς መነሻ ላይ ሆሞክሮን ወይንም ቴታ ሲመጡ የትርጉም ልዩነት አላቸው፤ ይህም "ሆስ" Oς ማለትም "ሆሞክሮን ሲግማ" የነበረው "ቴስ" Θς ማለትም "ቴታ ሲግማ" ይሆናል ማለት ነው፤ "ቴስ" Θς የሚለው "ቴኦስ" θεός ለሚለው ምጻረ ቃል ሲሆን "አምላክ" ማለት ነው። እንግዲህ ኮዴክስ አሌክሳንድሪየስ ላይ "ሆስ" Oς (እርሱ) የነበረው "ቴስ" Θς (አምላክ) በማለት በርዘው የትርጉም ልዩነት አምጥተዋል። ሲበርዙ የአምላክ ንግግር ያልሆነውን የጳውሎስንም ንግግር አላስተረፉትም።
እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ 1690 ዓመተ-ልደት አይዛክ ኒውተን ሁለት የባይብል ብርዘት ካላቸው መካከል የመጀመሪያው 1 ጢሞቴዎስ 3፥16 ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 1 ዮሐንስ 5፥7 ናቸው። የሮሙ ቢሾፕ ጄሮም በ 382 ዓመተ-ልደት ባዘጋጀው በላቲን ቩልጌት ላይ ሆነ፥ በ 1611 ዓመተ-ልደት በተዘጋጀው በኪንግ ጀምስ ቨርዥን ላይ፦ "አምላክ በሥጋ የተገለጠ" የሚለውን አስቀምጠውታል። ይህ ስህተት ነው፤ ምክንያቱም 5800 የሚደርሱ የአዲስ ኪዳን የግሪክ እደ-ክታባት አሉ፤ ከኮዴክስ አሌክሳንድሪየስ ውጪ ሁሉም "ቴስ" የሚለውን አይጨምሩም።

ሲቀጥል ብዙ የአዲስ ኪዳን ንባባት፦ አምላክ ተገለጠ ሳይሆን የአምላክ ልጅ ተገለጠ ወይም ሰው ተገለጠ ነው የሚሉት፦
1 ዮሐንስ 3፥9 ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ *"የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ"*። the Son of God was manifested.
የሐዋርያት ሥራ 2፥22 የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም *ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ"*፤

እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ከአንዱ እግዚአብሔር የተገለጠው ሰው ነው፤ እግዚአብሔር ከተገለጠ "ከእግዚአብሔር ዘንድ እግዚአብሔር ተገለጠ" ትርጉም ይሰጣል? ግን የተገለጠ ሰው ነበረ። ስለዚህ በስጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ የተባለው ሰው ነው።
ሢሰልስ አንቀጹ፦ "በክብር ያረገ" ይላል። "እግዚአብሔር በስጋ ተገለጠ፥ እግዚአብሔር በክብር ያረገ" ትርጉም ይሰጣልን? ምክንያቱም ዐራጊው ማንነት የሚያርገው ወደ እግዚአብሔር ነው፤ ዐርጎም የሚቀመጠው በእግዚአብሔርም ቀኝ ነው፦
ማርቆስ 16፥19 ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ *ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ*።
ዮሐንስ 17፥11 *"እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ"*።
ዮሐንስ 20፥17 *እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ"* ብለሽ ንገሪአቸው፥ አላት።

ልብ አድርጉ ኢየሱስ እራሱን በመጀመሪያ መደብ "እኔ" እያለ እግዚአብሔር ደግሞ በሁለተኛ መደብ "አንተ" እያለ በጸሎት ሲናነጋግረው ተመልከቱ፤ ዓራጊው ኢየሱስ ሲሆን ከሚያርግበት ከእግዚአብሔር ማንነት ለመለየት "ወደ" የሚል መስተዋድድ ተጠቅሟል፤ "ወደ አምላኬ ዓርጋለሁ" የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት፤ "አምላኬ" ማለቱ የሚያርገው ማንነት አምላክ አለው። እግዚአብሔር ከሆነ ወደ እግዚአብሔር የሚያርገው እግዚአብሔር አምላክ አለውን? አዎ! ብሎ ማመን ምን አይነት ድራማና ቁማር ነው? ፈጣሪ ፍጡር ሆኖ በተፈጠረ ማንነቱ ተገለጠ ማለት ክህደት ነው። እነዚያ፦ "አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው" ያሉ በእርግጥ ካዱ፦
5፥72 እነዚያ *«አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው»* ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ لَقَدْ كَ. فَ. رَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ
5፥17 እነዚያ *"አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው"* ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ لَّقَدْ كَفَرَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ

ከኡስታዝ ወሒድ ዑመር