Get Mystery Box with random crypto!

21፥19 በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉም የእርሱ ነው፡፡ *”እርሱ ዘንድ ያሉትም መላእክት እርሱን | Tiriyachen | ጥሪያችን

21፥19 በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉም የእርሱ ነው፡፡ *”እርሱ ዘንድ ያሉትም መላእክት እርሱን ከመገዛት አይኮሩም”*፡፡ አይሰለቹምም፡፡ وَلَهُ مَن فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۚ وَمَنْ عِندَهُ لَا يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِهِ وَلَا يَسْتَحْسِرُونَ
66፥6 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነፍሶቻችሁንና ቤተሰቦቻችሁን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጋዮች ከኾነች እሳት ጠብቁ፡፡ በእርሷ ላይ ጨካኞች፣ ኀይለኞች የኾኑ መላእክት አሉ፡፡ *”አላህ ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፤ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ”*፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا قُوا أَنفُسَكُمْ وَأَهْلِيكُمْ نَارًا وَقُودُهَا النَّاسُ وَالْحِجَارَةُ عَلَيْهَا مَلَائِكَةٌ غِلَاظٌ شِدَادٌ لَّا يَعْصُونَ اللَّهَ مَا أَمَرَهُمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ

መላእክት አላህ ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፤ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ። እዚህ ድረስ ከተግባባን የሚቀጥለውን አንቀጽ ጥልልና ጥንፍፍ ባለ መልኩ እንይ። በባቢሎት በሚገኙት በሀሩትና በማሩት ላይ የተወረደው የሲሕር ትምህርት ሰዎችን እንዴት እንደሚጎዳ ማስጠንቀቂያ ሆኖ ነው። ነገር ግን ሰይጣናትም በሱለይማን ዘመነ መንግስት ሰዎችን የሚያስተምሩት ለአሉታዊ ነገር ነበር፦
2፥102 *”ሰይጣናትም በሱለይማን ዘመነ መንግስት የሚያነቡትን ተከተሉ፡፡ ሱለይማንም አልካደም፤ ግን ሰይጣናት ሰዎችን ድግምትን የሚያስተምሩ ሲኾኑ ካዱ፡፡ ያንንም በባቢል በሁለቱ መላእክት በሃሩት እና ማሩት ላይ የተወረደውን ነገር ያስተምሩዋቸዋል፡፡ «እኛ መፈተኛ ነንና አትካድ» እስከሚሉም ድረስ አንድንም አያስተምሩም፡፡ ከእነሱም በሰውየውና በሚስቱ መካከል በእርሱ የሚለዩበትን ነገር ይማራሉ”*፡፡ وَٱتَّبَعُوا۟ مَا تَتْلُوا۟ ٱلشَّيَٰطِينُ عَلَىٰ مُلْكِ سُلَيْمَٰنَ ۖ وَمَا كَفَرَ سُلَيْمَٰنُ وَلَٰكِنَّ ٱلشَّيَٰطِينَ كَفَرُوا۟ يُعَلِّمُونَ ٱلنَّاسَ ٱلسِّحْرَ وَمَآ أُنزِلَ عَلَى ٱلْمَلَكَيْنِ بِبَابِلَ هَٰرُوتَ وَمَٰرُوتَ ۚ وَمَا يُعَلِّمَانِ مِنْ أَحَدٍ حَتَّىٰ يَقُولَآ إِنَّمَا نَحْنُ فِتْنَةٌۭ فَلَا تَكْفُرْ ۖ فَيَتَعَلَّمُونَ مِنْهُمَا مَا يُفَرِّقُونَ بِهِۦ بَيْنَ ٱلْمَرْءِ وَزَوْجِهِۦ

እዚህ አንቀጽ ላይ “ሃሩትና ማሩት” እንዳመጹ የሚያሳይ ኃይለ-ቃል ወይም ፍንጭ ሽታው የለም። ምናልባት፦ “እነርሱም በአላህ ፈቃድ ካልኾነ በእርሱ አንድንም ጎጂዎች አይደሉም” የተባለው ስለ ሃሩትና ማሩት መስሏችሁ ከሆነ ተሳስታችኃል፦
2፥102 *”እነርሱም በአላህ ፈቃድ ካልኾነ በእርሱ አንድንም ጎጂዎች አይደሉም፥ የሚጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውንም ይማራሉ”*፡፡ وَمَاوَمَا هُم بِضَارِّينَ بِهِ مِنْ أَحَدٍ إِلَّا بِإِذْنِ اللَّهِ ۚ وَيَتَعَلَّمُونَ مَا يَضُرُّهُمْ وَلَا يَنفَعُهُم

ምክንያቱም ሃሩትና ማሩት ሁለት ስለሆኑ ለእነርሱ የምንጠቀምበት ተውላጠ-ስም በሙተና “ሁማ” هُمَا ነው፥ ነገር ግን “በአላህ ፈቃድ ካልኾነ በእርሱ አንድንም ጎጂዎች አይደሉም” የተባሉትን ላይ “እነርሱም” ለሚለው የገባው “ሁም” هُم ሲሆን ከሁለት በላይ ጀመዕ መሆኑ “ሸያጢን” شَّيَٰطِين የሚለውን ተክቶ የመጣ ነው። ሸያጢን ሰዎችን ድግምትን የሚያስተምሩ ሲኾኑ ካዱ፥ ሰዎች ከሸያጢን የሚጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውንም ይማራሉ።
ሲጀመር እዚህ አንቀጽ ላይ “ወ” وَ የሚለው መስተጻምር ሕዝብን ሲሕር የሚያስተምሩት ሸያጢን እና ሀሩትና ማሩትን የሚያስጠነቅቁበትን ትምህርት ለመለየት የገባ መስተፃምር ነው። ከመነሻው ሸያጢን የሚያስተምሩት ድግምት እና ለሀሩትና ማሩት ተወረደ የተባለው ነገር ሁለት ለየቅል የሆኑ ሀረግ መሆናቸው ፍንትውና ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ሃሩትና ማሩት፦ “እኛ መፈተኛ ነንና አትካድ” እስከሚሉም ድረስ አንድንም አያስተምሩም፥ እነርሱ ላይ የተወረደው ስለ ሲሕር አውንታዊነት ሳይሆን አሉታዊነት የሚያስረዳ ትምህርት ነው።

ሲቀጥል “ማ” مَا የሚለው ቃል ሁለት ፍቺ ይኖረዋል፤ አንዱ “ማ” مَا “መውሱላ” ሲሆን ሁለተኛው “ማ” مَا “መስደሪያ” ነው።
1ኛ. “ማ” مَا የሚለውን “መውሱላ” ማለትም “አንፃራዊ ተውላጠ-ስም” ሆኖ ከተቀራ በባቢሎት በሚገኙት በሀሩትና በማሩት ላይ የተወረደ ነገር እንዳለ ያመለክታል፥ ያ ነገር ግን ከላይ ባየነው የሰዋስም ሙግት ከሸያጢን ሲሕር ተለይቶ በመስተፃምር ተቀምጧል።
2ኛ. “ማ” مَا የሚለው መስደሪያ ማለት “አፍራሽ-ቃል” በሚለው ከተቀራ ደግሞ በባቢሎት በሚገኙት በሀሩትና በማሩት ላይ የሸያጢን ሲሕር አልተወረደም የሚል ፍቺ ይኖረዋል። ምክንያቱም አይሁዳውያን ሚድራሽ በሚባለው መፅሐፋቸው ላይ፦ “ሲሕር በሁለቱ መላእክት በኩል ባቢሎን ላይ ከፈጣሪ የተወረደ ነው” የሚሉትን ቅጥፈት አላህ እያጋለጣቸው ነው። ምክንያቱም አይሁዳውያን አስማት የሰለሞን ጥበብ ነው የሚል እምነት አላቸው፤ ይህንን እሳቤ አንዳንድ ዐበይት ክርስትና በትውፊት ይጋሩታል። ይህንን ነጥብ ኢብኑ ዐባሥ፣ ኢብኑ ጀሪር፣ ቁርጡቢ ያነሱታል።

ሢሰልስ “ሀሩትና ማሩት” ማንና ምን ናቸው? የሚለውን ነጥብ ሁለት አመለካከቶች አሉት፤ ይህንም ጤናማ የተለያየ አመለካከት ያመጣው ጤናማው የቂርኣት ውበት ነው፥ “መለከይኒ” مَلَكَيْنِ የሚለው ቃል ”መለክ” مَلَك ማለትም ”መልአክ” ለሚለው ቃል ሙተና”dual” ሲሆን “ሁለት መላእክት” የሚል ፍቺ የሚኖረው “ላምን”ل ላም ፈትሓ “ለ” لَ ተብሎ ሲቀራ ነው። ሌላው “መሊከይኒ” مَلِكَيْنِ የሚለው ቃል “መሊክ” مَلِك ማለትም “ንጉሥ” ቃል ሙተና ሲሆን “ሁለት ነገሥታት” የሚል ፍቺ “ላምን” ل ላም ከስራ “ሊ” لِ ተብሎ ሲቀራ ነው። ሁለቱም ቂርኣት ከመለኮት የተወረደ እስከሆነ ድረስ በሁለቱም መቅራት ይቻላል። ይህ ነጥብ በጀላለይን፣ በአጥ-ጠበሪ፣ በዛማኽሻሪ፣ በባጋዊ እና በራዚ ተወስቷል። የውይይታችን ዋናውና ተቀዳሚው ሙግት ሀሩትና ማሩት ማንና ምን ናቸው? ሳይሆን መላእክት በፍጹም አምጸው አያውቅም የሚል ነው።

ከወንድም ወሒድ ዑመር

መልካም ቆይታ ከጥሪያችን ጋር
‐‐‐
Follow us on:
‐‐‐
https://fb.me/tiriyachen
https://t.me/tiriyachen
https://tiriyachen.org
https://bit.ly/3eVixKv
https://www.tiktok.com/@tiriyachen