Get Mystery Box with random crypto!

#ገብር _ኄር መምህር አብርሃም በዕውቀቱ መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም በጎ አገልጋይ ለጌታው | ትንሳዔ ዘኢትዮጵያ ✝✝✝

#ገብር _ኄር

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ

መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በጎ አገልጋይ ለጌታው ታምኝ እንደመሆኑ ‹‹ገብር ኄር›› ይባላል፡፡ ይህም ስያሜ ለዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት እንደተሰጠ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይገልጻል፡፡ የስያሜው መነሻ የሚገኘው ደግሞ በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው በማቴዎስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት የእገሌና የእገሊት ተብሎ ባይወሰንም ቤተ ክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የኃላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ ሐሳቦችን በአትኩሮት መመርመር  ጠቃሚ ነው፡፡

በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሄዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡ ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው እንዲያተርፉበት ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ኃላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡

ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ኃላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት እንደሚችል ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ኃላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት፣ ሁለኃ አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡ ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ እንዲያተርፉበት መክሊቱን ሰጥቷቸው በሄደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሢሰሩ የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ፣ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን እንዳደረገበት ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረና በዚህ ከፊቱ ያዘነውን ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው እናነባለን፡፡

በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ እግዚአብሔር ይርዳን።

ምንጭ:- ማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ የተወሰደ