Get Mystery Box with random crypto!

የደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ ሀውልት እንደ አዲስ ለማሰራት እንቅስቃሴ ተጀመረ። ደራሲና ጋዜጠኛ አ | TIKVAH-MAGAZINE

የደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ ሀውልት እንደ አዲስ ለማሰራት እንቅስቃሴ ተጀመረ።

ደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ በምዕራብ ጎጃም ዞን በ አቸፈር ወረዳ ልዩ ስሙ ኮረንች አቦ በተባለ ቀበሌ ከአባቱ ከአቶ ጉበኛ አምባየና ከእናቱ ከወ/ሮ ይጋርዱ በላይ ሰኔ25 ቀን 1925 ዓ.ም ነው የተወለደው።

በዘመኑ በሚጽፋቸው መጽሐፍት፣ የግጥም መድብሎችና ተውኔቶች ፖለቲካዊ፣ ማበራዊና ሀይማኖታዊ ትችቶችን ይሰነዝር የነበረ ደፋር ደራሲ እንደነበር ሥራዎቹና የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።

በዚህም በተለያዩ ጊዜያት እስር ድብደባና የግዞት ህይወት ለመምራት ተገዷል። በ1957 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ በተካሄው የህዝብ እንደራሲነት ምርጫ ለመወዳደር የሚያስችለውን የህዝብ ድጋፍ ቢያገኝም በፀጥታ ሀይሎች ተያዞ ብዙ ስቃይና እንግልት አሳልፏል።

አቤ በህይወት ዘመኑ ከ27 በላይ መፅሀፍቶችን እንደጻፈ ይነገርለታል። ከእነዚህም ውስጥ አልወለድም፣ የሮም አወዳደቅ፣ ሰይፈ ነበልባል፣ የሀሜት ሱሰኞች፣ አንድ ለእናቱና ሌሎችም የጥበብ ሥራዎቹ ተጠቃሽ ናቸው።

የብዕር ታጋዩ ጋዜጠኛውና ደራሲው ታላቁ የጥበብ ሰው አቤ ጉበኛ ብዙ ስቃዮችንና እስሮችን አሳልፎ የካቲት 1/ 1972 ተደብድቦ ተገደለ። የካቲት 4 /1972 በይስማላ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስርአተ ቀብሩ ተፈጽሟል።

መታሰቢያ ሀውልቱ በዚህ ቤተ ክርስቲያን በር ላይ ተሰርቶ አሁንም ድረስ ያለ ቢሆንም ደራሲውን አይመጥንም በሚል በተለያዩ ጊዜያቶች ሲነሳ ይስተዋላል።

ይህን ተከትሎም የይስማላ ከተማና አካባቢዋ ወጣቶች የአቤን ሀውልት ጀግንነቱንና መልካም ስራውን በሚመጥን መልኩ ለማቆም ስራ መጀመራቸው ተገልጿል። እስካሁን በተሰራው ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን ሥራም ሀውልቱ በነሀስ እንደሚሰራ ተወስኗል። ዲዛይኑም በመሰራት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

@tikvahethmagazine