Get Mystery Box with random crypto!

ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ አደገኛ ዕፅ ማስተላለፊያ ዋሻ ተገኘ። ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ አደገኛ ዕፅ ለ | TIKVAH-MAGAZINE

ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ አደገኛ ዕፅ ማስተላለፊያ ዋሻ ተገኘ።

ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ አደገኛ ዕፅ ለማስተላለፊያነት የሚያገለግለውና 531 ሜትር የሚረዝመው ዋሻ መገኘቱ ተገልጿል። ዋሻው ሐዲድ የተዘረጋለት፣ የአየር መቆጣጠሪያ ስርዓት (ቬንትሌሽን) የተገጠመለት ሁሉን ያሟላ ነው ተብሏል።

የሳውዘርን ካሊፎርኒያ አውራጃ የአሜሪካ አቃቢ ሕግ ጽሕፈት ቤት ዋሻው ከመሬት 18 ሜትር ጠልቆ የሚገኝ እና አንድ ሜትር መጠነ ዙርያ (ዲያሜትር) እንዳለው የገለጸ ሲሆን በዚህ ዋሻ ኮኬይን፣ ሜታመፌታሚን እና ሄሮይን የተባሉ ዕፆችን ሊያስተላልፉ የነበሩ ስድስት ሰዎችንም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ገልጿል።

ወደ ዋሻው የሚጠጉ መኪኖች ላይ በተደረገ ፍተሻ አደገኛ ዕፅ መገኘቱን ተከትሎ በተደረገ ምርመራ አንድ መጋዘን የተገኘ ሲሆን መጋዘኑ ውስጥ ደግሞ ድንበሩን ተከትሎ የተቆፈረ ምሥጢራዊ ዋሻ መግቢያን አግኝተዋል።

የአቃቢ ሕግ ጽሕፈት ቤት እንደሚለው 799 ኪሎ ግራም ኮኬይን፣ 74 ኪሎ ግራም ሜታፌታሚን እና 1.5 ኪሎ ግራም ሄሮይን በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ዕድሜያቸው ከ31 እስከ 55 የሚሆኑት እነዚህ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ዕድሜ ይፍታህ ሊፈረድባቸው ይችላል። ከዚህ በላይ የ1 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ቅጣትም ይጣልባቸዋል።

በካሊፎርኒያ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲህ ያለ ምሥጢራዊ ዋሻ የተገኘው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። ያ ዋሻ 1ሺህ 313 ሜትር ርዝመት የነበረው ሲሆን በርዝመቱም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ነው። እንደ አውሮጳዊያኑ ከ1993 ጀምሮ 90 የሚሆኑ አደገኛ ዕፅ ማስተላለፊያ የምድር ውስጥ ድብቅ ዋሻዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል። (BBC)

@tikvahethmagazine