Get Mystery Box with random crypto!

ከቆቃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መገኘት ከነበረበት 42 MW ኃይል አሁን የሚገኘው ከ10 MW ያልበለጠ | TIKVAH-MAGAZINE

ከቆቃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መገኘት ከነበረበት 42 MW ኃይል አሁን የሚገኘው ከ10 MW ያልበለጠ ነው ተባለ።

የቆቃ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከሐይቁ ደለል የማስወገድ ሥራ፤ ላለፉት 20 ዓመታት ያህል የተቋረጠ በመሆኑ፣ ሐይቁ ለከፍተኛ የደለል ክምችት ተጋልጧል ተብሏል። የሐይቁ ጥልቀትም ከ10 ሜትር ወደ አንድ ሜትር አካባቢ የቀነሰ ሲሆን የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በእጅጉ መቀነሱ ነው የተነገረው።

ይህ የተገለጸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በቆቃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የመስክ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

በሐይቁ የውኃ ይዘት መቀነስ ምክኒያት፤ ከሦስቱ ተርባይኖች አንዱ ሥራ እንዳቆመ ያረጋገጠው ቋሚ ኮሚቴው፤ ባለፉት ዘመናት 42 ሜጋ ዋት ያመነጭ የነበረው ይህ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከ10 ሜጋ ዋት ያልበለጠ ኃይል እንደሚያመነጭም ተገንዝቧል፡፡

የቆቃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ወልደማርያም ጥላዬ፤ ከሞጆ ቆዳ ፋብሪካዎች የሚወጣው ኬሚካል ፍሳሽ ሐይቁን እንደበከለ፤ የበፈር ዞን ሕግ ባለመኖሩ ሐይቁ ከሰው እና እንሰሳ ንክኪ ነጻ አለመሆኑ እና በደለል መሞላቱ፤ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውን ለኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን አስተባባሪ አቶ መስፍን ዳኜ፤ ኃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚጠበቀውን ያህል ኃይል እያመነጨ ባለመሆኑ፣ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ የክልሉ መንግስት እና በተለያዩ ርከኖች የሚገኙት አመራሮች የተቀናጀ እና የጋራ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ (HPR)

@tikvahethmagazine