Get Mystery Box with random crypto!

#Genocide የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) እንዳይፈጸም በመከላከል እና ሲፈጸምም በማስቆም ላይ የ | TIKVAH-ETHIOPIA

#Genocide

የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) እንዳይፈጸም በመከላከል እና ሲፈጸምም በማስቆም ላይ የሚሰራው ተቋም " የጄኖሳይድ ዎች " ባደረገው ምርምር የሰው ልጆች ልባቸው ሲደድር የሚጠናወታቸው የዘር ጭፍጨፋ አባዜ 8 ደረጃዎች አሉት።

እነዚህም #በተደራጀ እና #ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚፈጸሙት ናቸው።

ደረጃዎቹ :-

1ኛ. መከፋፈል (Classification) - እኛና እነርሱ ብሎ በመከፋፈል ለየት ይላሉ ተብለው ሚታሰቡትን የኅብረተሰብ ክፍሎች #በቀልድም_ጭምር በማንቋሸሽ በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት አለማክበር።

2ኛ. የሚታይ መገለጫ መስጠት (Symbolization) - ይህ የጥላቻ ግልጽ መገለጫ ሲሆን ይሁዲዎች በናዚ ጀርመን ቢጫ ኮከብ ያለበት ልብስ እንዲለብሱ እንደተደረገው ነው፡፡

3ኛ. ከሰው ክብር ዝቅ ማድረግ (Dehumanization) - ይህ ተግባር ከራስ የተለዩትን ሰብዓዊ ክብርም ሆነ መብት በመንፈግ ይፈጸማል፡፡ በሩዋንዳ አክራሪ ሁቱዎች የቱትሲ ዘውግ ተወላጆችን " #በረሮ ፣ #እባብ " ይሏቸው እንደነበረው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሂደት ገዳዮቹ ' እየገደልን ያለነው ሰው አይደለም፤ ታዲያ ድርጊታችን ምኑ ላይ ነው ጥፋትነቱ ? ' እንዲሉ መንገዱን ይጠርግላቸዋል፡፡

4ኛ. ማደራጀት (Organization) - በጥላቻ ላይ የተመሠረቱ መንግሥታት አንድን ሕዝብ የሚያጠፋላቸውን ኃይል #ያሰለጥናሉ፡፡

5ኛ. በተቃራኒ ጎራዎች ማሰለፍ (Polarization) - ሕዝቡ በዘውጉ ከጨፍጫፊው እና ከተጨፍጫፊው ወገን ሚናውን እንዲለይ ይደረጋል፡፡ በብዛት ይህ የሚሆነው በጥላቻ ቡድኖች ውትወታ በመገናኛ ብዙሃን የጥላቻውን መርዝ በመርጨት ነው፡፡ አንዱን ዘውግ ከሌላው ለይቶ በማውጣት " ጠላት ነው " ብሎ ማወጅ ፤ ይህ የገዳዩን ዘውግ አባላት በቀላሉ ለማሳመንና ለህሊናው እንዲቀለው ለማድረግ ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

6ኛ. ዝግጅት (Preparation) - ሰለባዎቹ በልዩነቶቻቸው ተለይተው ይፈረጃሉ፡፡ የጭፍጨፋው ንድፍ አውጭዎች ሰዎችን በመኖሪያ አድራሻቸውና በሌሎችም መለያዎች ይፈርጁና ለፍጅት ያዘጋጇቸዋል፡፡

7ኛ. ፍጅት (Extermination) - በታቀደና ሆነ ተብሎ በተመቻቸ ዘመቻ የጥላቻ ቡድኖቹ ሰለባዎቻቸውን ይጨፈጭፋሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዘር ፍጅት ማንነታቸውን መለየት እስኪከብድ ድረስ ተጨፍጭፈዋል፡፡

8ኛ. ክህደት (Denial) - ግድያውን የፈጸሙትም ሆኑ ቀጣይ ትውልዶች ምንም ዓይነት ጥፋት ያልተፈጸመ በማስመሰል ክህደት ይፈጽማሉ፡፡

ከዚህ የጭፍጨፋ ሂደት እንደምንረዳው የዘር ፍጅት በአንድ ሌሊት ያለምንም ዝግጅት ስለማይፈጸም ራሳችንን ከላይ ከተጠቀሱት በሌላው ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ከስተቶች ፈጽሞ ማራቅና የዕለት ከዕለት ድርጊቶቻችንን መገምገምም ያሰፈልገናል።

እነዚህን የዘር ፍጅት አመላካች ሂደቶች በማናቸውም ደረጃ በእንጭጩ መቅጨት ከተቻለ የከፋ እልቂትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ይችላል።

ሁቱትሲ
ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛና ስቲቭ ኤርዊን
በመዘምር ግርማ

#Rwanda2024 #Kwibuka #Remembering

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
2016 ዓ/ም

@tikvahethiopia