Get Mystery Box with random crypto!

#Update ወጣት ሶፎኒያስ አስራትን ገድለው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ ማንነታቸው ያልታወቁ | TIKVAH-ETHIOPIA

#Update

ወጣት ሶፎኒያስ አስራትን ገድለው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ ማንነታቸው ያልታወቁ ወንጀል ፈፃሚዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ከዘረፉት ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ሟች ወጣት ሶፎኒያስ መጋቢት 24/2016 ዓ/ም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ናሆም ሆቴል አካባቢ ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ ማንነታቸው የማይታወቁ ሦስት ግለሰቦችን አሳፍሮ ወደ ቦሌ ሚካኤል ለማድርስ መሄዱን ጉዳዩን ለመከታተል የተቋቋመው የፖሊስ የምርመራና የክትትል ቡድን አባላት ባደረጉት ክትትል አረጋግጠዋል።

ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወንጀል ለመፈፀም አቅደው እና ተደራጅተው የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ መስለው ሹፌሩን በመቅረብ ከተሳፈሩ በኋላ አንገቱን በገመድ አንቀው በመግደል አስክሬኑን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ወደ አቦ ቤተክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ በመጣል አይነቷ ቪትዝ የሴሌዳ ቁጥር ኮድ 2A 93488 ተሽከርካሪ ጨምሮ 2 ሞባይል ስልኮችን ዘርፈው ይሰወራሉ፡፡

ፖሊስ ሌት ተቀን ባደረገው ብርቱ ክትትል ወንጀል ፈፃሚዎቹ የሰረቁትን ተሽከርካሪ ለመሸጥ እየተስማሙ መሆኑን በበቂ ማስረጃ ካረጋገጠ በሗላ ክትትሉን በመቀጠል ሦስቱን ዋና ወንጀል ፈፃሚዎች የሰረቁትን መኪና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ለመሸጥ እየተደራደሩ እንዳለ በቁጥጥር ስር በማዋል የተሰረቀችውን መኪና ፣ 2 ሞባይል ስልኮችን ልዩ ልዩ ኤግዚቢቶችን ይዞ ምርመራውን መቀጠሉን ገልጿል።

ፖሊስ ባደረገው ክትትልና ምርመራ ማንነታቸው የማይታወቁ ወንጀል ፈፃሚዎችን በ48 ሰዓት ጊዜ ውስጥ በመለየት 3 ዋና ወንጀል ፈፃሚዎችንና 3 ግብራበሮቻቸውን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ታውቋል፡፡

የምርመራ ሥራው እንዳበቃ የፍርድ ሂደት ውጤቱን በቀጣይ ለህዝብ እንደሚገለፅ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

@tikvahethiopia