' ኢትዮጵያዊ ነኝ' ኑሮ ቢገፋኝ ፥ የማልወድቅለት እንዳክሱም ድንጋይ ፥ እንደ ሮሐ አለት የግዜ | ቅዱስ ድልድይ/kidus bridge
" ኢትዮጵያዊ ነኝ"
ኑሮ ቢገፋኝ ፥ የማልወድቅለት
እንዳክሱም ድንጋይ ፥ እንደ ሮሐ አለት
የግዜ ሞገድ ፥ ያላደቀቀኝ
የመከራ ዶፍ ፥ ያልነቀነቀኝ
ለሙሾ ሲያጩኝ ፥ ቅኔ የምቀኝ
በግራ ሲሉኝ ፥ የምገኝ በቀኝ
ኢትዮጵያዊ ነኝ፤
ከዋርካ ባጥር ፥ ከምቧይ ተልቄ
ከፀሐይ ባንስም ፥ ከኩራዝ ልቄ
ተምድረ በዳ ፥ ጅረት አፍልቄ
ጥሜን የምቆርጥ ፥ በፍኝ ጠልቄ
ኢትዮጵያዊ ነኝ፤
ግትር ጠላቴን ፥ ባጭር አንካሴ
ራስ ምታቴን ፥ በዳማከሴ
ነቅየ ምጥል
ነገር በነገር ፥ የማብጠለጥል
ለወዳጆቼ ፥ ዓደይ ምነቅል
በጠላቴ ፊት ፥ ቀንድ የማበቅል
ልክ እንደዋልያ ፥ ተራራ መራጭ
ልክ እንዳሞራ ፥ ብርንዶ ቆራጭ
ኢትዮጵያዊ ነኝ
እንደመሀረብ ፥ ቤቴን በኪሴ
እንደንቅሳት ፥ ተስፋን በጥርሴ
ይዤ የምዞር ከቦታ ቦታ
በዘብ በኬላ የማልገታ
ኢትዮጵያዊ ነኝ።
ገጣሚ:-በውቀቱ ስዩም