Get Mystery Box with random crypto!

#ቲንክአቢሲኒያ_የቡናቁርስ_መረጃዎች 1፤የመስቀል በዓል በመላ ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ዛሬ | Think Abyssinia

#ቲንክአቢሲኒያ_የቡናቁርስ_መረጃዎች

1፤የመስቀል በዓል በመላ ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡

ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ የመስቀል በዓል በተለያዩ ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ሥነ ስርአቶች በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል። በተለይም በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ጳጳሳት፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ምዕመናን እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት ነው በድምቀት የተከበረው።

2፤ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች "ባለሙያዎች" ቡድን እንዲፈርስ ጥያቄ ቀረበ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አደረጃጀት አባላት ጥምረት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይን እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች "ባለሙያዎች" ቡድን እንዲፈርስ ጥያቄያቸውን ለተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነርና ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክር ቤት አባል ሀገራት አቅርበዋል። ጥምረቱ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ቡድን በፈረንጆቹ መስከረም 22፣ 2022 ባወጣው ሪፖርት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለማቅረብ በጻፉት ደብዳቤ አማካኝነት መሆኑም ታውቋል።

3፤ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ከ100 በላይ ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀ።

ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በኡሙሩ፣ ሆሮ ቡልቅ እና ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የአማራ ኢመደበኛ ታጣቂዎች ከነሐሴ 25 ጀምሮ ባሉት ሦስት ሳምንታት ከ100 በላይ ሲቪል ሰዎች ገድለዋል ሲል ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኮሚሽኑ የፌደራል እና ክልል ባለሥልጣናት በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸም ብሄርን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንዲያስቆሙም ጠይቋል።

4፤መረጃ አሳልፎ ሰጥቷል ስትል አሜሪካ በጥብቅ ለምትፈልገው ሰው ሩሲያ ዜግነት ሰጠች።

የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ለቀድሞ የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ሰራተኛ እና መረጃ አሳልፎ ለሰጠው ኤድዋርድ ስኖውደን የሩሲያ ዜግነት እንዲሰጠው በፊርማቸው አጽድቀዋል፡፡ ስኖውደን በፈንጆቹ 2013 የአሜረካ መንግስት የጀርመኗን መሪ ጨምሮ የ35 ሀገራት መሪዎችን ስልክ እና ኢሜል ላይ ስለላ ማድረጓን አጋልጦ ነበር፡፡ስኖውደን የሩሲያ ዜግነት ከተሰጣቸው 70 የውጭ ሀገራት ዜጎች መካከል አንዱ መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

5፤የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ-ግብር ማሻሻያ ተደረገበት።

የፊታችን ዓርብ የሚጀምረው የመጀመሪያ ዙር የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ-ግብር ማሻሻያ ተደረገበት። የመርሃ ግብር ማሻሻያው በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፈው ፋሲል ከነማ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ሁለተኛ ዙር ቅድመ ማጣሪያ ላይ ስለሚሳተፍ የፋሲልን ጨዋታዎች ታሣቢ በማድረግ የሊጉ የበላይ አካል የጨዋታ ፕሮግራም ማስተካከያ ማድረጉን ይፋ አድርጓል።

መልካም በአል
• @ThinkAbyssinia •