Get Mystery Box with random crypto!

#ቲንክአቢሲኒያ_የቡናቁርስ_መረጃዎች 1፤በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ያተኮረ የትራንስፖርት | Think Abyssinia

#ቲንክአቢሲኒያ_የቡናቁርስ_መረጃዎች

1፤በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ያተኮረ የትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ “ጤናማ ትራንስፖርትን ማበረታታት” በሚል መሪ ሃሳብ ምክክር እየተካሄደ ሲሆን በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስተሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ያተኮረ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

2፤ሦስተኛ ዙር ጦርነት ባለበት አካባቢ የምግብ ፍጆታ ዋጋ በ4 እጥፍ መጨመሩ ተሰማ።

በሰሜኑ ጦርነት ቀጠና ውስጥ ባሉ ቦታዎች የተለያዩ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ከነበረበት በአራት እጥፍ በላይ መጨመሩን አዲስ ማለዳ ዘግባለች። በሦስተኛው ዙር ጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር በኩል እና በራያ ቆቦ ወረዳ ግራና ቀኝ እንዲሁም በአፋር ክልል በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች ሲሆኑ በተለይም በራያ ቆቦ ከተማ ሦስተኛው ዙር ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የነበረው የምግብ ፍጆታ ዋጋ አሁን እስከ አራት እጥፍ ጨምሯል ተብሏል።

3፤አዲሱ የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር በአዲስ አበባ ተመሰረተ። 

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን ለማኅበሩ ዕውቅና መስጠቱን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የሙያ ማኅበሩ ማኅበሩ የተመሠረተው፣ የጤና ሙያን ለማሳደግ፣ በጤናው እና በሙያው ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስተካከል ረገድ እገዛ ለማድረግ፣ የጤና ሙያተኞችን መብቶችና ጥቅሞች ለማስከበር እና በረጅም ጊዜ የጤና ነክ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለመንግሥት ለማቅረብ እንደሆነ ተገልጧል።

4፤ኬንያ ከሩሲያ ነዳጅ ለመግዛት ፍላጎት እንዳላት ገለፀች።

የአሜሪካ ዲፕሎማት፤ የአፍሪካ ሃገራት ከስንዴ እና ማዳበሪያ ውጭ ከሩሲያ ምንም ነገር እንዳይገዙ ባስጠነቀቁበት በዚህ ሰአት የኬንያው ፐሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሀገራቸው ከሩሲያ ነዳጅ ለመግዛተ ፍላጎት እንዳላት እና ለዚህም ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ግን ሀገራቸው ያሉትን አማራጮች ሁሉ እያጤነች ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

5፤ጣሊያን የመጀመሪያዋን ሴት ጠ/ሚ ለመሾም ተቃርባለች ተባለ።

የቀኝ አክራሪው መሪ ጆርጂያ ሜሎኒ በጣሊያን ምርጫ ለማሸነፍ መቃረባቸው መገለፁን ተከትሎ የሀገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ሜሎኒ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኃላ የጣሊያን ቀኝ ክንፍ መንግሥት እንደሚመሰርቱ ከወዲሁ በሰፊው እየተጠበቁ ይገኛል። ጣሊያን የአውሮፓ ህብረት ሶስተኛዋ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ስትሆን የቀኝ ዘመሟ ሜሎኒ ድል ለአብዛኛው የአውሮጳ ህብረት ስጋት ፈጥሯል።

6፤ኢትዮጵያና ሱዳን የወዳጅነት ጨዋታቸውን ዛሬ ያካሂዳሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአቋም መለኪያ ከሱዳን ጋር ዛሬ ከቀኑ 10:00 ላይ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የእግር ኳስ ቤተሰቡ በስፍራው በነፃ በመታደም ብሔራዊ ቡድናችንን እንዲያበረታቱ ጥሪውን አቅርቦዋል።

• @ThinkAbyssinia •