Get Mystery Box with random crypto!

ርጢን ሚዲያ ( Ritin Media )

የቴሌግራም ቻናል አርማ theothokos — ርጢን ሚዲያ ( Ritin Media )
የቴሌግራም ቻናል አርማ theothokos — ርጢን ሚዲያ ( Ritin Media )
የሰርጥ አድራሻ: @theothokos
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 1.78K
የሰርጥ መግለጫ

ርጢን ከሙጫ ተቀምሞ የሚዘጋጅ ልዩ ፈዋሽ እጣን ነው።
#ተጨማሪ_አድራሻዎቻችን
#YouTube
https://youtube.com/channel/UC2rpoJAhNOxMgAiqgW5yqOw
#Facebook
https://www.facebook.com/ritintube/
#Tiktok
https://vm.tiktok.com/ZMRc7Sg1N/
#For_Question_and_comments
@Ritin_Media_bot

Ratings & Reviews

2.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

2

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2022-08-31 16:50:31
112 views13:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-31 16:50:31 <<< በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን :: >>>

<+> ነሐሴ 26  <+>

+*" አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ "*+

=>እግዚአብሔር በ13ኛው መቶ ክ/ዘ እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ባያስነሳ ኑሮ ምናልባትም ዛሬ የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያንን በምናያት መንገድ ላናገኛት እንችል ነበር:: እውነተኛ አባቶቻችን ፈጽሞ ከሚቆረቁራቸው ነገር አንዱ የጻድቅና ሐዋርያዊ አባት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መዘንጋት ነው::

+እርሳቸው ፍሬ ሃይማኖት ሆነው ከጽድቅ ፍሬአቸው አዕላፍ ቅዱሳንን ወልደው ሃገራችን በወንጌል ትምሕርትና በገዳማዊ ሕይወት እንድታሸበርቅ አድርገዋል:: እስኪ በዕለተ ዕረፍታቸው ስለ ጻድቁ ጥቂት ነገሮችን እናንሳ::

+አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ የተወለዱት ጐንደር : የድሮው ስማዳ (ዳኅና) አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ዘክርስቶስና እግዚእ ክብራ ይባላሉ:: የተወለዱት በ1210 ዓ/ም ነው:: ነገር ግን አንዳንድ ምንጮች በ1196 ዓ/ም ያደርጉታል::

+ጻድቁ ከክርስቲያን ወላጆቻቸው ጋር እንደሚገባ አድገዋል:: በልጅነታቸው በብዛት ወላጆቻቸውን ያግዙ ነበር:: በትርፍ ጊዜአቸው ደግሞ ትምሕርተ ሃይማኖትንና ሥርዓቱን ያጠኑ ነበር:: በ1240 ዓ/ም ግን (ማለትም 30 ዓመት ሲሞላቸው) ይሕቺን ዓለም ይተዋት ዘንድ አሰቡ::

+አስበውም አልቀሩ ፈጣሪን እየለመኑ ደብረ ዳሕሞ ገቡ:: በወቅቱ ዳሞ የትምሕርት : የምናኔ ማዕከል ከመሆኑ ባሻገር የአቡነ አረጋዊ 5ኛ የቆብ ልጅ ካልዕ ዮሐኒ ነበሩና የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ሆኑ::

+አቡነ ኢየሱስ ሞዐ በደብረ ዳሞ በነበራቸው ቆይታ ቀን ቀን ሲታዘዙ : ሲፈጩ : ውሃ ሲቀዱ ውለው ሌሊት እኩሉን በጸሎት በስግደትና የቀረውን ሰዓት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ አሳለፉ::

+በመጨረሻም ልብሰ ምንኩስናን ለበሱ:: ይህን ጊዜ 37 ዓመታቸው ሲሆን ዘመኑም 1247 ዓ/ም ነው:: ወዲያውም በዳሞ ሳሉ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ "ወደ ወሎ ሐይቅ ሒድ : ብዙ የምትሠራው አለና" አላቸው::

+በአንዴም ከዳሞ (ትግራይ) ነጥቆ ሐይቅ እስጢፋኖስ (ወሎ) አደረሳቸው:: በዚያም ለ7 ዓመታት በዼጥሮስ ወዻውሎስ ቤተ መቅደስ በተጋድሎ : በስብከተ ወንጌል : በማዕጠንትና ሐይቁ ውስጥ ሰጥሞ በመጸለይ ኖሩ::

+ቅድስናቸውን የተመለከቱ አበውም በግድ አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው:: ይህ ነው እንግዲህ በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቁ መሠረት የተጣለበት አጋጣሚ:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

+ስም አጠራሯ የከፋ ዮዲት ጉዲት ለ40 ዓመታት ሃገሪቱን እንዳልነበረች ብታደርጋት ክርስትና ተዳከመ:: ባዕድ አምልኮም ነገሠ:: አቡነ ኢየሱስ ሞዐ (ትርጉሙ ኢየሱስ ክርስቶስ አሸነፈ ማለት ነው) ደግሞ ሃይማኖታቸው የቀና ከ800 በላይ ክርስቲያኖችን ሰበሰቡ::

+በሃገሪቱ ትልቅና የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ቤተ መጻሕፍት አደራጁ:: እነዚያን አርድእት በቅድስናና በትምሕርት አብስለው አመነኮሱና "ሒዱ! ሃገሪቱን ታበሩ ዘንድ ተጋደሉ" ብለው አሰናበቷቸው::

+ክእነዚህ መካከልም ታላላቁን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን: አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እና የሁዋላውን ፍሬ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን መጥቀስ እንችላለን:: በዚህም ምክንያት ጻድቁ "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን - አእላፍ ቅዱሳንን የወለደ" ሲባሉ ይኖራሉ::

+ጻድቁ ከዚህ በተጨማሪ የወቅቱን ንጉሥ አፄ ይኩኖ አምላክን በማስተማር ለሃገርና ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ሰው አድርገዋል:: በግላቸው ሐይቅ ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ የብርሃን ምሰሶ ይወርድላቸው ነበር:: ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም ከጠፋ ከ300 ዓመታት በሁዋላ አቅንተዋል::

+እንዲህ ለቤተ ክርስቲያን ሲተጉ : በተለይ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ለዓይናቸው እንቅልፍን አላስመኙትም:: ጐድናቸውም ከምኝታ ጋር ተገናኝቶ አያውቅም::
"እንዘ የኀሊ ዘበሰማያት ዐስቦ::
መጠነ ዓመታት ሃምሳ ኢሰከበ በገቦ::" እንዲል::

+ከዚህ በሁዋላ የሚያርፉበት ዕለት ቢደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል:: በተወለዱ በ82 ዓመታቸው (በ86 ዓመታቸው የሚልም አለ) በ1282 ዓ/ም በዕለተ ሰንበት ዐርፈው ተቀብረዋል::

<< ጻድቁ ስም አጠራራቸው እጅግ የከበረ ነው !! >>

=>+"+ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማሕበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ:: የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ:: እንዲሁም ጐበዞች ሆይ! ለሽማግሌዎች ተገዙ:: ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ:: እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና:: ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል:: +"+ (1ዼጥ. 5:3)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
118 views13:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-30 23:18:12 ††† እንኳን ለቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት እና ለታላቁ አባ ቢጻርዮን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት †††

††† ቅዱሱ በ3ኛው መቶ ክ/ዘ የነበረ አረማዊ ሰው ሲሆን ከከሃዲው መክስምያኖስ ወታደሮችም አንዱ ነበር:: "ሊቀ መሓዛት" ይሉታል: የጐበዛዝቱ አለቃም ነበር:: ይህ ሰው ምንም ክርስቲያን አይሁን እንጂ በልቡ ቅንነት ተገኝቶበታል:: እንደ አሕዛብ ልበ ድንጋይ አልነበረም::

በወጣትነቱም አንዲት ደመ ግቡ ሴት አግብቷል:: ይህች ሴት ' #ኤልያና' ስትባል የተባረከች ክርስቲያን ናት:: እርሱ ግን አያውቅም:: ከተጋቡ ከዓመታት በሁዋላ ጌታ እግዚአብሔር ስለ ሚስቱ ጸሎት በጐ ጐዳና ሊመራው ፈለገ::

እንድርያኖስ ሁሌም በየቀኑ ክርስቲያኖች ደማቸውን ሲያፈሱ ይመለከታል:: የትእግስታቸው መጠንም ይገርመው ነበር:: በተለይ አብዛኞቹ በመከራው ደስተኞች ነበሩ:: ነገሩ ግራ ቢያጋባው 24 ባለንጀሮች ሊገደሉ ወደ ታሠሩበት ቦታ ሒዶ ጠየቃቸው::

"ምን ልታገኙ ነው ግን ይሕንን ሁሉ ስቃይ በአኮቴት (በምስጋና) የምትቀበሉት?" ቢላቸው "በሰማይ በክርስቶስ ዘንድ የሚጠብቀንን የክብር ሕይወት ሥጋዊ አንደበት አከናውኖ መናገር አይቻለውም:: ዝም ብሎ 'ዕጹብ: ዕጹብ' እያሉ የሚያደንቁት ነው እንጂ" አሉት::

እርሱም ተደላድሎ ተቀምጦ "እስኪ በደንብ አስረዱኝ" አላቸው:: ከዓለም መፈጠር እስከ ጌታችን የማዳን ሥራ: አልፎም ስለ ፍርድ ቀን በጥዑም አንደበታቸው አስተማሩት:: ቅዱስ እንድርያኖስ በቅጽበት ልቡ ወደ ክርስቶስ ፍቅር ሸፈተ::

በፍጥነት ተነስቶ የራሱን ስም ከሰማዕታቱ 25ኛ አድርጐ አጻፈ:: ንጉሡ ይሕንን ሲሰማ "አብደሃል" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የለም! ዛሬ ገና ከእብደቴ ተመለስኩ" በማለቱ ከ25ቱ ቅዱሳን ጋር ታሠረ:: ቅድስት ኤልያና (ሚስቱ) ነገሩን ስትሰማ ፈጽሞ ደስ አላት::

ወደ እስር ቤት ሒዳ "አይዞህ በርታ! ስለ ክርስቶስ የሞትክ ቀን ብቻ እኮራብሃለሁ" ብላ: እግራቸውን አጥባቸው ተመለሰች:: በሚገደሉበት ቀንም ልሰናበታት ብሎ ቅዱስ እንድርያኖስ ቢመጣ ቅድስት ኤልያና ቤቷን ዘግታ ገሠጸችው:: እርሷ ክዶ የመጣ መስሏት ነበር::

እርሱ ግን የሚስቱን የእምነት ጥንካሬ ተረዳ:: ቅዱሱና 24ቱ ቅዱሳን ለቀናት ብዙ መከራን እየተቀበሉ ሰነበቱ:: አካላቸውን እየቆራረጡ: ደማቸውን እያፈሰሱ ሆዳቸውንም እየቀደዱ መከራን አጸኑባቸው:: በመጨረሻው በዚህች ቀን ሲገደሉ ቅድስት ኤልያና "የእኔን ባል አስቀድሙት" አለች:: (የሌሎቹን አይቶ እንዳይደነግጥ ነው)

እንዳለችውም የእርሱንና የባልንጀሮቹን ጭን ጭናቸውን እየሰበሩ ገድለዋቸዋል:: ቅድስት ኤልያናንም መሣፍንቱ "ካላገባንሽ" እያሉ ሲያስቸግሯት ተሰዳ ሒዳ ከሰማዕታቱ መቃብር ላይ አለቀሰች:: ጌታም ጠርቷት እዚያው ዐረፈች::

††† ታላቁ አባ ቢጻርዮን †††

ታላቁ ገዳማዊ ሰው የመጀመሪያ መነኮሳት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ሲሆን ዓለምን ንቆ ከመነነ በሁዋላ ከአባ #እንጦንስ ዘንድ መንኩሷል:: ከእርሳቸው ዘንድ በረድእነት ለብዙ ዓመታት አገልግሏል:: አገልግሎቱን በፈጸመ ጊዜም አስኬማን ተቀብሎ ወደ በርሃ ወጥቷል::

ምንም የራሱን ገዳም ባይመሠርትም በ4ኛው መቶ ክ/ዘ የምናኔ ሕይወት እንዲስፋፋ ካደረጉ አበው እርሱ ዋነኛው ነው:: በተጋድሎ ዘመኑም የሚታወቅባቸው ነገሮች አሉ:: ከእነሱም ጥቂት እንጠቅሳለን:: አባ ቢጻርዮን:-
1.ጾሙም ሆነ ጸሎቱ በ40 ቀናት የተወሰነ ነበር:: ጾምን ከጀመረ ያለ 40 ቀን እህል አይቀምስም:: ለጸሎት ከቆመም የሚቀመጠው ከ40 ቀናት በሁዋላ ነው::
2.ሁሌም በየበርሃው እየዞረ ያለቅሳል:: "ምነው" ሲሉት "ወገኖቼ አለቁብኝ: ደሃም ሆንኩ" ይላቸው ነበር:: እንዲህ የሚለው አጋንንት ብዙ ነፍሳትን እየነጠቁ ሲወስዱ ስለሚመለከት ነው::
3.በየገዳማቱ እየለመነ ለነዳያን ያከፋፍል ነበር::
4.ሐፍረቱን ከሚሸፍን ጨርቅ በቀር ምንም ልብስ አይለብስም ነበር::
5.ውዳሴ ከንቱን አምርሮ ይጠላ ነበር::
6.በባሕር ላይ ተራምዶ ሲሔድና እግሮቹ ሳይርሱ ሲቀሩ አበው ተመልክተዋል::
7.መርዝነት ያለውን ውሃም ጣፋጭ አድርጐታል::

††† ቅዱሱ ድውያንን ፈውሶ: አጋንንትን ከአካባቢው አሳዶ: ብዙ ፍሬ አፍርቶ: ገዳም ውስጥ በገባ በ57 ዓመቱ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

††† ቸር አምላክ በክብረ ቅዱሳን ይከልለን:: ከበረከታቸውም ያብዛልን::

††† ነሐሴ 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት
2."24ቱ" ሰማዕታት (ማሕበሩ)
3.ቅድስት ኤልያና (ሚስቱ)
4.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ
5.ቅዱስ ኤልያኖስና እህቱ አውዶክስያ (ሰማዕታት)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

††† "ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን: የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው:: #እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከእርሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና: በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር:: በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ:: እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን:: ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን::" †††
(2ቆሮ. 5:18)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
35 views20:18
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 21:19:04
340 views18:19
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-28 21:19:04 ††† እንኳን ለሰላሳ ሺ ግብጻውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሠለስቱ እልፍ ሰማዕታት †††

††† ዘመነ ሰማዕታት አርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን በአርባ ዓመታት ከበላ በኋላ በ305 (312) ዓ/ም ቢጠናቀቅም ስለ ሃይማኖት መሞት ግን እስከ ምጽዓት ድረስ ይቀጥላል:: ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ከሚቀርቡ ፈተናዎች ሁሉ እጅግ ከባዱ ይሔው ሰማዕትነት ነውና ሊቀበለው ያለው (ያደለው) ይቀበለዋል::

ቤተ ክርስቲያን በባሕር ላይ ያለች መርከብ ናትና ዘወትር በፈተና ውስጥ መኖሯ የሚጠበቅ ነው:: ዘመነ ሰማዕታትን ተከትሎ የመጣው የመናፍቃን ዘመን ሲሆን ለመቶ ሃምሳ ዓመታት ያህል መናፍቃን እንደ አሸን ፈልተዋል:: በዚያው ልክ ከዋክብት ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና በየጊዜው ጉባኤያትን እየሠሩ: መናፍቃንን አሳፍረዋል:: ምዕመናንንም አጽንተዋል::

በ451 ዓ/ም የተፈጸመው ድርጊት ግን ዛሬም ድረስ ጠባሳው የሚለቅ አልሃነም:: ንጉሡ መርቅያንና ጳጳሱ ልዮን የንስጥሮስን ትምሕርት አለባብሰው ሊያስተምሩ ሲሞክሩ ግጭት በመፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለት ተከፈለች::

በጉባኤው የነበሩ ስድስት መቶ ሰላሳ ስድስት ጳጳሳት ስቃይና ሞትን ፈርተው በኑፋቄ መጽሐፍ ላይ በመፈረማቸው "መለካውያን" (ከእግዚአብሔር ይልቅ ለንጉሥ የሚታዘዙ) ተባሉ:: ጉባኤውም "ጉባኤ ከለባት" (የውሾች ስብሰባ): "ጉባኤ አብዳን" (የሰነፎች ጉባኤ) ተብሏል::

የወቅቱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን "በኑፋቄው ላይ አልፈርምም::" ከማለቱ አልፎ መናፍቃኑን አወገዛቸው:: በዚህ ምክንያት ጽሕሙን ነጭተው: ጥርሱንም አርግፈው: ወደ ጋግራ ደሴት ከሰባት ደቀ መዛሙርቱ ጋር አሳደዱት::
በዚያም ለሦስት ዓመታት ቆይቶ በ454 ዓ/ም ዐረፈ::

እግዚአብሔር ፈርዶባቸው ንጉሡ መርቅያን እና ንግሥቲቱ ብርክልያ (ክፉ ሴት ናት) ድንገት ሞቱ:: ፈተናው ግን በዚህ አላበቃም:: በዙፋኑ የተተካው ሌላኛው ጨካኝ ልዮን ነበር:: መንፈሳዊውን አርበኛ አባ ዲዮስቆሮስን በሞት ያጡት የግብጽ ክርስቲያኖች ደቀ መዝሙሩን "አባ ጢሞቴዎስን እንሾማለን::" ቢሉ ንጉሡ ከለከለ::

የሚሾመው መለካዊ ነው ብሎ አብሩታርዮስ የሚባል መናፍቅ ጳጳስ በላያቸው ላይ ሾመባቸው:: ይህንን መታገስ ለሕዝቡና ለካህናቱ ከባድ ነበር:: ተኩላ እንኳን በበጐች ላይ በይፋ ተሹሞ: ተደብቆም ቢሆን እየነጠቀ መብላት ልማዱ ነው:: መናፍቁ ጳጳስ በተለያየ መንገድ ሕዝቡን ለመሳብ ሞክሮ ነበር::

ለምሳሌ አውጣኪን (የክርስቶስን ሰው መሆን ምትሐት የሚል 'የቱሳሔ' አስተማሪ መናፍቅ ነው::) አወገዘው:: እነሱ ግን ተረድተውታልና ቦታ አልሰጡትም:: ምክንያቱም አውጣኪ ከቀድሞም የተወገዘ መናፍቅ ነውና:: የሚገርመው ከሕዝቡ አንድስ እንኳ ከመናፍቁ ጳጳስ የሚባረክ አልነበረም:: ሥጋውን ደሙንም ከእውነተኛ ካህናት በድብቅ ይቀበሉ ነበር::

አንድ ቀን ግን መናፍቁ ጳጳስ አብሩታርዮስ ተገድሎ ተገኘ:: (መልአክ ቀሥፎት ነው የሚሉ አሉ:: እስካሁን ድረስ የገዳዩ ማንነት አልታወቀም::) ግብጻውያን ክርስቲያኖች ግን የእርሱን ሞት ሲሰሙ ደጉን እረኛ አባ ጢሞቴዎስን ሾሙ:: ችግሩ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው::

የመናፍቁ ተከታዮች ለንጉሡ ልዮን "አንተን ንቀው: የሾምከውን ገደሉ:: ሌላ ጳጳስም ሾሙ::" ብለው መልዕክት ላኩለት:: በዚህ የተበሳጨው ልዮን ኦርቶዶክሳውያንን ባገኛችሁበት ሁሉ ግደሉ የሚል አዋጅ አወጣ:: ይህን አዋጅ ተከትሎ ሰላሳ ሺ ሰዎች በእስክንድርያ ከተማ ተጨፈጨፉ::

ገዳዮቹ ወንድ: ሴት: ሕፃን: ሽማግሌ ሳይመርጡ የክርስቲያኖችን ደም አፈሰሱ:: ለሦስት ቀናትም ግድያው ቀጥሎ እንደ ነበር ይነገራል::
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "ወኀጥኡ ዘይቀብሮሙ" እንዳለ ቀባሪም አጡ::

ገዳዮቹ ቀጥለውም አባ ጢሞቴዎስን አስረው አጋዙት:: ለአሥር ዓመታትም አሰቃዩት:: ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ግን ንጉሡ ተጸጽቶ አባ ጢሞቴዎስን ወደ መንበሩ መልሶታል:: ወገኖቻችን የግብጽ ክርስቲያኖች እንኳን ያኔ ዛሬም በጽናታቸው አብነት ልናርጋቸው የሚገቡ ናቸው::

††† አምላከ ሰማዕታት በቸርነቱ ይጠብቀን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

††† ነሐሴ 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ሰላሳ ሺ የእስክንድርያ (ግብጽ) ሰማዕታት
2.ቅዱስ ድምያኖስ ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
6.አባ ሳሙኤል
7.አባ ስምዖን
8.አባ ገብርኤል

††† "በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ:: ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን::" †††
(፩ጴጥ. ፫፥፲፫-፲፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
346 views18:19
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-27 23:03:42 ሰላም #የቤተ_ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ ቻናል ቤተሰቦች የእግዚአብሔር ሰላም በያለንበት ይጎብኘን እያልኩ ሰሞኑን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንደገና በተቀሰቀሰው ግጭት (ጦርነት) ምክንያት በአካባቢያችን ኔትወርክ በየትኛውም አጋጣሚ ሊቋረጥ (ሊጠፋ) ስለሚችል በዚህ ቻናል የሚተላለፈው ቃለ እግዚአብሔር ላልተወሰኑ ቀናት ላይተላለፍ ይችላል።

እናም የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችንን ብሎም አካባቢያችን ወደቀደመው ሰላማችን መልሶን በዚህችው ቻናል እስክንገናኝ እርስ በእርስ በጸሎት እየተሳሰብን እንጠብቅ።

እኔንም #ወልደ_ኪዳን እንዲሁም ልጄን #ፍቅርተ_ማርያም በማለት በጸሎታችሁ አስቡን።
354 views20:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-27 23:03:31
412 views20:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-27 23:03:31 ††† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሚክያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ †††

††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ::" እንዳለ ጌታ በወንጌል::
(ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10)
ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

††† ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት
¤አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት:
¤አራቱ ዐበይት ነቢያት:
¤አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና
¤ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ::

††† አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

††† አራቱ ዐበይት ነቢያት
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

††† አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

††† ካልአን ነቢያት ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::

††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::

††† ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው::
አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::

ሚክያስ አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል:: ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው::

ቅዱሱ ነቢይ ገና ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር:: በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በሦስቱ ነገሥታት (በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል::

አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና: ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት::
"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ: ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ: ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እሥራኤል::"

"አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ (መስፍን) ካንቺ ዘንድ ይወጣልና::" አለ::

ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በኋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነግሥት ኢየሱስክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል::

ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: ሰባት ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና: በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹ ቀብረውታል:: ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል::

††† ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ: በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን::

††† ነሐሴ 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
5.አባ ጳውሊ የዋህ

††† "ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?" †††
(ሚክ. ፮፥፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
409 views20:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ