Get Mystery Box with random crypto!

10ኛው እና የዓመቱ የመጨረሻው የጃንደረባው መጻሕፍት ጉባኤ በድሬዳዋ በድምቀት ተካሄደ:: ነሐሴ | ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የአንባብያን ኅብረት

10ኛው እና የዓመቱ የመጨረሻው የጃንደረባው መጻሕፍት ጉባኤ በድሬዳዋ በድምቀት ተካሄደ::

ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም
ድሬደዋ፣ ኢትዮጵያ

10ኛው እና ለዓመቱ የመጨረሻው የሆነው የጃንደረባው መጻሕፍት ጉባኤ የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባና የቅዱስ ፊልጶስን የንባብ ፈለግ የተከተሉ ወጣቶችን አሣትፎ በድሬዳዋ ደብረ ታቦር እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ጽርሐ ጽዮን ሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ብዙ አንባብያን በተገኙበት በድምቀት  ተካሄዶአል።

በዕለቱ ጉባኤው በደብሩ አገልጋይ ካህናት እና ዲያቆናት በውዳሴ ማርያም ጸሎት የተጀመረ ሲሆን መርሐግብሩ የተመራው በሰ/ት/ቤቱ ም/ሰብሳቢ ወጣት ኤልያስ ነበር። ጉባኤው መክፈቻውን ያደረገው የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8ን በማንበብ ሲሆን በሰ/ት/ቤቱ ዘማርያን ዕለቱን እና በዓሉን የሚያመለክት ጥዑም ዝማሬ ቀርቧል።

በመቀጠል ዝግጅቱ "የበረሃ ምንጮች - ማላንካራውያን" በተሰኘው የመኮንን ኃብተ ሚካኤል መጽሐፍ ላይ ዳሰሳን በማቅረብ ቀጥሎአል።

በዲ/ን ብንያም አድማሱ የቀረበው የመጽሐፉ ዳሰሳ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉትን አሳቦች በሚያስደንቅ ሁኔታ ከመተንተን በተጨማሪ ቀጣይ የቤት ሥራዎቻችንን እንዲሁም እስከ ዛሬ ያልሠራናቸውን ሥራዎች በማንሣት ለሰ/ት/ቤት፣ ለምዕመናን፣ ለካህናት፣ ለወጣቶች፣ ለወላጆች እንዲሁም ለሕፃናት በየዕድሜ ደረጃቸው የሚጠበቅባቸውን ነገር አቅጣጫ በመስጠት ጭምር የቀረበ በመሆኑ በታዳሚዎች ሕሊና ውስጥ የማይጠፋ ምስልን የቀረፀ፣ ቁጭትን የፈጠረና "እኛስ ለእኛ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን ምን ልናደርግ ይገባናል?" የሚለውን ጥያቄ የጫረ ነበር።

በመቀጠል መድረኩን የተረከበው በመጽሐፉ ዳሰሳ ዙሪያ በተሣታፊዎች የሚደረግ ውይይት እና ጥያቄ የመጠየቅ መርሐግብር ነበር። በተነሡት ጥያቄዎች ላይ የዳሰሳው አቅራቢ በቂ ማብራሪያ በመስጠት አጥጋቢ በሆነ መልኩ ጥያቄዎቹን መልሰዋል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ከድሬ አስተባባሪዎች መካከል ወጣት ዳዊት ዘገየ ባለፉት 10 ዙሮች ጉባኤውን የተሣተፉትን ሁሉ አመስግነው የዚህን ዓመት የመጽሐፍ ዳሰሳ ፍጻሜ መሆኑን አስታውቀዋል። በተጨማሪም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በ2015 ዓ.ም የመጻሕፍት ጉባኤው ሌሎቹን የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ትውልድ ሁነቶች በመጨመር ከፍ ባለ ደረጃ ዝግጅቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።

የሚቀጥለው ጉባኤ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሠረገላ ማረፊያው በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም መሆኑ ታውቋል። የሚዳሰሰውም መጽሐፍ በዲ/ን ሚክያስ አስረስ የተጻፈው "ማስያስ" የተሰኘው መጽሐፍ ይሆናል።

ለመሆኑ በዚህ የጃንደረባ ሠረገላ ላይ ተሳፍረን ከማንበብ፣ ከመጠየቅና ከመመራመር የሚከለክለን ምንድር ነው?

ቸር ያገናኘን!