Get Mystery Box with random crypto!

This too shall pass | ይህም ያልፋል የማያልፍ ነገር የለም። ባለበት የሚቆም ነገር የ | Tesfaab Teshome

This too shall pass | ይህም ያልፋል

የማያልፍ ነገር የለም። ባለበት የሚቆም ነገር የለም። እንዳለ የሚቆይ ነገር የለም። ነገሮች ይቀየራሉ። ቋሚው ነገር ለውጥ ብቻ ነው።

ለአረንጓዴው ዘመቻ ለአረንጓዴው
በርቱ ጭቁኖች ድሉ የኛ ነው

ብለን ችግኝ ተከልን። የመስኖ ቦዮች ተሠሩ። መሬት ታረሰ። ይህ ሁሉ የህዝብ ሥራ ባለቤት አልነበረውም። ያኔ ዛፍ ለመቁረጥ ቀበሌ ማስፈቀድ ያስፈልግ ነበር። ሆኖም ድርቅና ረሃብ አልቀረልንም። ኋላ ላይ ዛፎቹ ተቆረጡ።

ድርቅን ለመሸሽ ሰዎችን ከቦታ ቦታ አዛውረን አሰፈርን፣ በቆሎ አመረትን፣ ለመሪው እሸት ላክን። ከችግሩ ግን አልወጣንም። ዓመታት ቆይተን እንደገና ተራብን።

አይኖሩም አይኖሩም የማያነቡ ዓይኖች
አይኖሩም የማይጽፉ ጣቶች

ብሉን መሃይምነትን ለማጥፋት መሠረተ-ትምህርት ለማስተማር ዘመትን፣ በየዓመቱ ጀማሪ፣ ማጠናከሪያ፣ ድህረ እያልን አስተማርን፣ መሃይምነት ግን አልጠፋም።

ታጋይ ጀግና ፈፋ ለፈፋ
በጦር ሜዳ ጠላት ሲደፋ
ኢትዮጵያ ኑሪ ሀገሬ
አትደፍርም ዳር ድንበሬ

ብለን ሀገር ለመጠበቅ ብሔራዊ ውትድርና ዘመትን፣ በቅጥርም ብዙ ሆነን ዘመትን፣ ግን ድንበርና ግዛት አልተከበረም፣ እንዲያውም ግዛት ተወሰደ፣ ድንበር ተቀየረ።

ከችግር መውጣት ውስብስብ አይደለም። It is simple. But, it is not simple. ነገሩ ውስብስብ አይደለም ግን ቀላል አይደለም፤ ሥራና ተከታታይነት ያለው ዲሲፕሊን ይጠይቃል።

ችግር በዘመቻ አይጠፋም። ይህንን እንድንል የመጣንበት መንገድና ልምድ ያስገድደናል።

"ነጋ ጠባ ዘመቻ ትላለች" ሮማን ኅለተወርቅ ምርር ብሏት በኦሮማይ ላይ በበዓሉ ግርማ አንደበት። እንደዘመቻችን ብዛት የት በደረስን ነበር።

እኛ እድገት በህብረት ብለን በዘመቻ ስንናጥ እነ ቢል ጌትስ እና ስቲቭ ጆብስ ኩባንያ እየመሠረቱ ነበር፤ እነ ኤሎን መስክ ደግሞ የኮምፕዩተር ፕሮግራም ይጽፉ ነበር።

እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸው የመሠረቱት ኩባንያ እና የሚያስተዳድሩት ሀብት ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ተጽዕኗቸውም እንደዚያው እጅግ ከፍ ያለ ነው።

ትውልዱ እንዲማር የሚያስፈልገው ተመሳሳይ ነገርን በመድገም ያንኑ ውጤት መድገም እንጂ የተለየ ነገር መፍጠር እንደማይቻል ነው።

ንቃ! ከዲስኩር ማዳመጥ ውጣ።

በየቀኑ ባይቻል ቢያንስ በሳምንት አንድ ነገር አሻሽል።

ሁሉም ያልፋል፣ ጊዜም ጭምር። የሚያልፈው ጊዜ ላይ የማያልፍ ነገር ጫንበት።

ዘለቄታዊ ለውጥ ላይ አተኩር።

Duce luce peaca

@Tfanos