Get Mystery Box with random crypto!

​​የብፁዕ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሥርዓተ ጸሎ | መርጌታ ባምላኩ የባህል መዳኒት

​​የብፁዕ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሥርዓተ ጸሎትና ሥርዓተ ቀብርን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ተከትሎ፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሰብሳቢነት የመከረው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥርዓተ ቀብራቸውን የሚያስፈጽም ዐቢይ ኮሚቴ አቋቁሟል።

የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ ከአምስት ያላነሡ ንዑሣን ኮሚቴዎችን በማቋቋምና ሥራዎችን በየዕለቱ እየተከታተለ፣ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ሥራዎችን በወጣው መርሐ ግብር መሠረት እያከናወነ ይገኛል። በዚህም መሠረት፦

ከሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዓርብ ድረስ ይፋዊ የኃዘን ቀናት ታውጆ፥ የእምነት ተቋማት መሪዎች፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሪዎችና ተወካዮች፣ የውጭ ሀገራት ኤምባሲ አምባሳደሮች፣ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንና ምእመናት በመንበረ ፓትርያርክ ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ በመገኘት በተዘጋጀው የኃዘን መግለጫ መዝገብ ላይ በጽሑፍ ኀዘናቸውን እየገለጹ ይገኛል።

በቀጣይ ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ የቅዱስነታቸው አስከሬን ከሃሌ ሉያ ሆስፒታል በክብር ወደ መስቀል አደባባይ ያመራል፤ በመስቀል አደባባይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት፣ መላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየድርጅትና የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ምእመናንና ምእመናት ለዕለቱ የተዘጋጀው መርሐ ግብር ተከናውኖ ከተጠናቀቀ በኋላ በክብር ታጅቦ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጉዞ በማድረግ ያርፋል።

በመንበረ ፓትርያርክ ጸሎተ ወንጌል ደርሶ፣ ልዩ ልዩ የሐዘን መግለጫና መንፈሳዊ መልእክቶች ከተላለፉ በኋላ፥ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የክብር ሽኝት ይደረጋል።

በዚያም ሌሊቱን በሙሉ ስብሐተ እግዚአብሔር፣ ከነግህ ጀምሮ ጸሎተ ቅዳሴ ከደረሰ በኋላ፤ በመርሐ ግብሩ መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ የእምነት ተቋማት መሪዎች፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትና ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንና ምእመናት በተገኙበት ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል።

ምንጭ፡-የ/ኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ