Get Mystery Box with random crypto!

ሰላም ልጆች ክብር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ የተባሉትን ሰው ታውቃላችሁ? እስኪ ለማታውቁ ላስተ | ተረት ተረት

ሰላም ልጆች
ክብር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ የተባሉትን ሰው ታውቃላችሁ?

እስኪ ለማታውቁ ላስተዋውቃችሁ።

ከአዲስ አበባ 45 ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘው ደብረ ዘይት(ቢሾፍቱ) ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ፣ ዶሎ በምትባል ቀበሌ በ1921 ዓም ተወለዱ።

ሠዓሊና ቀራፂው ለማ ጉያ የሸክላ ጥበብ ባለሞያ የነበሩትን እናታቸውን ወሮ ማሬ ጎበናን በማየት የቅርፃ ቅርፅ እና የሥዕል ዝንባሌ ይዘው በእረኝነት አደጉ።

በ15ዓመታቸው ደብረ ዘይት ላይ በተከፈተው የአፄ ልብነ ድንግል ት/ቤት ገብተው መማር ጀመሩ።

እስከ ሰባተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ በተሳቡበት ሥነ ጥበቡ ለመሠማራት ወደ ወላጆቻቸው ተመለሱ። ብዙም ሳይቆዩ በመምህርነት ለመሠልጠን ኮተቤ ማሠልጠኛ ቢገቡም፣ ከልባቸው ጋር አልገጠመምና ወዲያውኑ አቆሙት። ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው፣ የሥነጥበቡንና የቅርፃ ቅርፅ ሥራቸውን አጠበቁ።

በደብረ ዘይትና አካባቢው በሠዓሊነታቸውና በቀራፂነታቸው ታውቀው ሣቆዩ፣ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ በከተማቸው የሚገኙበትን አጋጣሚ ጠብቀው የሥዕል ትዕይንት አዘጋጅተው እንዲመለከቱላቸው ጋበዟቸው።

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለስዕል ሥራዎች ልዩ ፍላጎት የነበራቸው በመኾኑ፣ የሥዕል ትዕይንታቸውን በሚገባ ተመልክተው በማድነቅ፣ ምን እንዲያደርጉለት እንደሚፈልጉ ወጣቱን ለማ ጉያን ጠየቋቸው።

ለማ፣ “የአየር ኃይሉ ሠራዊት አባል በመኾን፣ አየር ማብረርን ፣” እንደሚፈልጉ ነገሯቸው።
ወድያውኑ በደብረ ዘይቱ የአየርኃይል መኰንኖች ማሠልጠኛ እንዲማሩ አዘዙላቸው። በዚህም አጋጣሚ የአየርኃይል ወታደር ኾኑ።

በአየር ኃይሉ ግቢም የሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን መሥራት ቀጥለው ነበርና አሥመራ ላይ በነበረው የጣሊያኖች የሥዕል ት/ቤት ገብተው የመማር ዕድል አግኝተው ለአጭር ጊዜ ሠለጠኑ።

በውትድርናው የሻምበልነት ማዕረግ ይዘው፣ እስከ ሠላሳ ሦስት ዓመታቸው፣ ለአስርት ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተው፣ አኹንም በጥበቡ ሥራ ብቻ ለመኖር በመፈለግ ከአየር ኃይል ተሰናብተው ወጡ።

ከዚያን ጊዜ ጀምረው በቀረው ዘመናቸው ኹሉ ሥነ ጥበቡን ሕይወታቸው አድርገው ኖረዋል።

ለማ ጉያ የአፍሪካ መሪዎችን ምሥል በመሥራት ለየ ራሳቸው በማበርከት ሥራዎቻቸውን በመላው የአፍሪካ አብያተ መንግሥታት አኑረዋል።
በቢሾፍቱ መኖርያቸው በስማቸው የተጠራ የግል ቤተ ሥዕል ከፍተዋል። ለብዙ ልጆች የእጅ መፍቻና መሠረታዊ የንድፍ ጥበብ መማርያ የኾነ
ያለ አስተማሪ የሥዕል መማርያ መጽሐፍ” አሳትመዋል።

ሠዓሊና ቀራፂ ሻምበል ለማ ጉያ የሦስት ሴቶችና የኹለት ወንዶች ልጆች አባት ነበሩ።
አርቲስት ለማ ጉያ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት በአገር ውስጥ እና በውጪ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
@TeretTeretChannel