2022-04-04 22:20:17
እ ይ ታ ና ጤ ን ነ ት
═════❁═════
በአንድ ጥናት ላይ የቀረበ ውጤት እንዲህ ይለናል። ሰዎች ከዚህ ቀደም ያሳለፏቸውን "ክፉ" እና ውስጥን የሚረብሹ የሕይወት ልምምዶች ለአምስት ደቂቃዎች ጠልቀው እንዲያስቡ ሲደረጉ የሰውነት የመከላከል አቅማቸው (immune system) በ55 በመቶ በመውረድ ለስድስት ሰዓታት በዚያ ሁኔታ ይቆያል። ጥናቱ የተደረገባቸው ሰዎች ደስ የሚያሰኙ ልምምዶቻቸውን ለአምስት ደቂቃዎች እንዲያሰላስሉ ሲደረጉ ደግሞ የሰውነት የመከላከያ አቅማቸው (immune system) በ40 በመቶ ከፍ በማለት ለተወሰነ ጊዜ ይቆያል።
አካላዊ ስጋችን የአእምሯችን ባሪያ ነው። አምነንበትም ሆነ ሳናምንበት በአእምሯችን የምናሰላስለው ሃሳብ ካለማቋረጥ ወደ አካላችን ትዕዛዝን ያስተላልፋል። ስለዚህ የምናሰላስላቸው እያንዳንዳቸው የደካማነትና የሕመም ሃሳቦች ሰውነታችንን ለዚያ ሁኔታ ሲያዘጋጁ፣ በተቃራኒው ደግሞ ውብና አዎንታዊ ሃሳቦቻችን ሰውነታችን ጥሩ ነገርን እንዲጠባበቅ፣ እንዲጓጓ ያደርጉታል። ከዚህ እውነታ ጋር አብሮ የሚሄድ ሌላ ጥናት አለ።
በአንድ አዛውንቶች በሚኖሩበት የመንግሥት መጦሪያ ቦታ የድርጅቱ አስተዳዳሪዎች የአዛውንቶቹ አሟሟት ሁኔታና ወቅት ግር ስላላቸው ማጥናት ጀመሩ። እነዚህ አዛውንት እጅግ ያረጁና በዕድሜ ጫናና ድካም ውስጥ ያሉ ናቸው። ጥናቱን ያደረጉት ሰዎች ሁለት ነገር አስተዋሉ።
አንደኛው፣ አዛውንቶቹ በፊታቸው እንደ ልደትና የመሳሰሉ ሁኔታዎች የሚከበርላቸው ሁኔታ ሲኖር ቀና በማለት ይነቃቃሉ። በዚያ ጉጉት ውስጥ ካሉ አዛውንቶች መካከል የመሞት ሁኔታ አይታይም። ሁለተኛው ግኝት፣ እንደ አዲስ ዓመትና የመሳሰሉ ቤተሰቦቻቸው መጥተው የሚያከብሩላቸው በዓል ሲኖር በመኖሪያ ቦታው የሚሞት ሰው ብዙም አይገኝም። በተቃራኒው ምንም ዓይነት ጉጉት የሚፈጥር ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በማይኖሩባቸው ወቅቶች የሚሞቱት አዛውንት ቁጥር ከፍተኛ ነው።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ጥናቶች አመለካከታችን በጤንነታችን ላይ ያለውን ቀጥተኛ ተጽእኖ አመልካቾች ናቸው። ሁኔታው ደግሞ የአእምሮንም ሆነ አካላዊ ጤንነቶችን የሚጠቀልል ነው።
የአካላችንንም ሆነ የአእምሯችንን ጤንነት ለመጠበቅ ከፈለግን የአመለካከታችንን ጤንነት መጠበቅ ተገቢ ነው
>>>
-------------------------
እ ይ ታ
በዶ/ር ኢዮብ ማሞ
ገፅ 21 - 22
944 viewsErmiyas Hayilye, 19:20