Get Mystery Box with random crypto!

'ትግራይ ዮሐንስ ቢሰዋ ይነሳል በአክሱም በሳባ' ደርቡሾች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው እስከ ጎን | Teddy Afro

"ትግራይ ዮሐንስ ቢሰዋ
ይነሳል በአክሱም በሳባ"

ደርቡሾች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው እስከ ጎንደር ገብተው በርካታ አብያተክርስቲያናትን አቃጠሉ፤ ቀሳውስት እና ምእመናንን ገደሉ፤ የተረፈውንም ማርከው ወሰዱ። ይሄንንም ነገር አስመራ ሆነው የሰሙት አጼ ዮሐንስ ንጉሥ ተክለሃይማኖትን ጦራቸውን ይዘው ወደ መተማ እንዲዘምቱ አዘዙ።

ንጉሥ ተክለሃይማኖትም ትእዛዙን ተቀበለው በደርቡሽ ላይ ዘመቱ። ድልም አደረጉ ምርኮኛም ይዘው ተመለሱ። ወዲያውኑ ግን የደርቡሽን መሸነፍ የሰማው የሱዳኑ ገዢ ከሊፍ ዐብዱላሂ አቡ አንጋ ሌላ በቁጥሩ የበዛ ሰራዊት በድጋሚ ላከ። በዚኛው ጊዜ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦር የጠላትን ጦር መቋቋም ስላልቻለ መሸሽን አማራጭ አደረገ።

ከወራት በኋላም አጼ ዮሐንስ የፈሰሰውን የኢትዮጵያውያንን ደም ሊበቀሉ ጦራቸውን አስከትለው ወደ መተማ ዘመቱ። በመተማም የነበረው የደርቡሽ ጦር የአጼ ዮሐንስን ጀግንነት ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ከሰራዊቱ በተጨማሪ ገብሬና ነጋዴዎችን ሳይቀር መሳሪያ አሲይዞ ይጠብቅ ነበር።

ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም ጦርነቱ ተጀመረ። የኢትዮጵያ ሰራዊት እየፎከረና እየሸለለ ደርቡሾቹ እስከመሸጉበት ድረስ በመግባት ቀኑን ሙሉ ሲዋጋ ዋለ። ሆኖም የኢትዮጵያ ሰራዊት ኃይል ከፍ ብሎ የደርቡሽ ሰራዊት መሸሽ ጀምሮ ሳለ አጼ ዮሐንስ ከበቅሏቸው ወርደው ከሰራዊታቸው መሐል ሆነው ይዋጉና ያዋጉ ስለነበር ሳይታሰብ በጥይት ተመትተው ወደቁ። በዚህም ጊዜ ከድሉ አፋፍ እየደረሰ የነበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት የንጉሡን መመታት ሲሰማ ይደናገጥ ጀመር። የደርቡሽን ምሽግ ሰብሮ ገብቶ የነበረው ወታደርም መውጣትን መረጠ።

አጼ ዮሐንስም በነገሡ በ17 ዓመታቸው እሁድ መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በዚህም፦
"በጎንደር መተኮስ
በደንቢያ መታረድ አዝኖ ዮሐንስ፤
ደሙን አፈሰሰ እንደ ክርስቶስ።" ተብሎ ተገጠመ።

በአጼ ዮሐንስ ዙሪያ የነበሩ ወታደር ፣ መኳንንት እና ካህናትም የአጼ ዮሐንስን አስክሬን በሳጥን አድርገው በሰም በማሸግ ከመተማ መሸሽ ጀመሩ። የደርቡሽ ጦር መሪ የነበረው ዜኪ ግን ሰራዊቱን ይዞ ተከተላቸው። የአጼ ዮሐንስ ወታደሮች እና መኳንንትም የንጉሣችንን አስከሬን በሕይወት እያለን አናስነካም ብለው እስከመጨረሻው ተዋጉ ሆኖም ቁጥራቸው ትንሽ ነበርና ድል ሆኑ። ከዚህም በመቀጠል ደርቡሾች የአጼ ዮሐንስን አስከሬን ከሳጥኑ አውጥተው ራሳቸውን ቆርጠው በሱዳን ላለው ከሊፋ ላኩለት። ከሊፋውም የአጼ ዮሐንስን ራስ በእንጨት ሰክቶ በግመል አድርጎ ገበያ ለገብያ እያዞረ ሲያሳይ ዋለ። ይህንንም ያወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲህ ሲል ተቀኘ፦
"አጼ ዮሐንስ ይዋሻሉ
መጠጥ አልጠጣም ይላሉ፤
ሲጠጡ አይተናል በርግጥ፤
ራስ የሚያዞር መጠጥ።"

ምነጭ፥ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ በተክለጻዲቅ መኩሪያ