Get Mystery Box with random crypto!

† ጥያቄ ለኦርቶዶክስ አገልጋዮች † ★ በየሆቴሉና በየአዳራሹ ጉባዔ ማድረግ የተወገዘ ነው ስትሉ | Tariku Abera

† ጥያቄ ለኦርቶዶክስ አገልጋዮች †

★ በየሆቴሉና በየአዳራሹ ጉባዔ ማድረግ የተወገዘ ነው ስትሉ የነበረ ለእናንተ ችርቻሮ ጊዜ የተቀደሰ ያደረገው ማነው ? ★

" የተለሰኑ፡መቃብሮችን፡ስለምትመስሉ፥ወዮላችኹ።
እንዲሁ፡እናንተ፡ደግሞ፡በውጭ፡ለሰው፡እንደ፡ጻድቃን፡ትታያላችኹ፥በውስጣችኹ፡ግን፡ግብዝነትና፡
ዐመፀኝነት፡ሞልቶባችዃል።" ማቴ 23 ፥ 27

ከጊዜ ወደ ጊዜ በኦርቶዶክስ አገልጋዮች ዘንድ የምናየው ነገር እጅግ የሚያሳፍርና በሕዝብ ዘንድ የሚያስተዛዝብ ነው።
ሁላችን እንደምናስታውሰው ከጥቂት ዓመታት በፊት በርካታ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሰባክያንና ዘማርያን ከእናት ቤተክርስቲያናቸው ተወግዘው እንዲወጡ ተደርገዋል።ከቤተክርስቲያን እንዲወጡም ከፍተኛ ጫናና ግፊት ተደርጓል ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት የነበረው በየአዳራሹና በየሆቴሉ ጉባዔ እያዘጋጁ ወጣቱን ከቤተክርስቲያን መዓዛ እየለዩት ነው የሚል ነበር።

የአዳራሽ ጉባዔ ሲቃወሙ የነበሩት የዛሬ ነጋዴ ሰባክያንና ዘማርያን በወቅቱ ምክንያታቸውን ሲያቀርቡ የዕጣኑ መዓዛ ወደ ማይሸተትበት ፣የካህናቱ ዜማ ወደ ማይሰማበት፣ኪዳን ወደ ማይደረስበት ፣ቅዳሴ ወደ ማይቀደስበት አዳራሽና ሆቴል ሕዝቡን እየወሰዱ ከቤተክርስቲያን ዓውደ ምሕረት ሊለዩት ነው ብለው ከፍተኛ ሁሁታና አድማ በማድረግ አገልጋዮቹ ከቤተክርስቲያን እንዲወጡ አስደርገዋል።

ለመሆኑ የዛኔ እንደ ርኩስ ይቆጠር የነበረው የአዳራሽ ጉባዔ ዛሬ ቅዱስ የሆነው ለእናንተ የካሴትና የመጽሐፍ ችርቻሮ ሲሆን ነው እንዴ ? በየሆቴሉ አትሂዱ ስትሉ የነበራችሁ ግብዞች ዛሬ ለእናንተ ንግድ ሲሆን ሆቴሉ ቤተመቅደስ ሆነ እንዴ? የአዳራሽ ጉባዔ የተወገዘ ነው ስትሉ የነበረ እናንተ የተለሰነ መቃብር የመሰላችሁ ግብዞች ዛሬ ለእናንተ ቢዝነስ መስሪያ ሲሆን አዳራሹ ገዳም ሆነ እንዴ ?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል ፦ "አንተ፡የምትፈርድ፡ሰው፡ዅሉ፡ሆይ፥የምታመካኘው፡የለኽም፤በሌላው፡በምትፈርድበት፡ነገር፡ ራስኽን፡ትኰንናለኽናእንደዚህም፡በሚያደርጉት፡ላይ፡የእግዚአብሔር፡ፍርድ፡እውነተኛ፡እንደ፡ኾነ፡እናውቃለን።" ሮሜ 2፥1

እውነት ለመናገር እናንተ ግብዝ አገልጋዮች በወቅቱ እንደዛ ያዙን ልቀቁን እያላችሁ ወንድሞቻችሁን ስታሳድዱ የነበረው የቤተክርስቲያን ክብርና የወንጌል ፍቅር ልባችሁን አቃጥሎት ሳይሆን ክፋ ሰይጣናዊ ቅናት አዕምሯችሁን አደንዝዞት በምቀኝነት ነው።እንደዛ ባይሆንም ኖሮ ዛሬ በየሆቴሉና በየአዳራሹ ስትልከሰከሱ አትታዩም ነበር።በሰይጣናዊ ቅናት ተበለጥን የሚል ክፋ ምቀኝነት እንቅልፍ ነስቷችሁ ስለነበር የገዛ ወንድምና እህቶቻችሁን ካደጉበት ከእናት ቤተክርስቲያናቸው አሳዳችሁ ለአውሬ ሰጣችኋቸው፣አንድም ቀን ቁጭ ብለን እንወያይ ብላችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ገልጣችሁ ያላነጋገራችኋቸውን ወንድም እህቶቻችሁን ገፍታችሁ አስወግዛችሁ ከበሮ ስትደልቁ ነበር እግዚአብሔር ግን ይፈርዳል።በእግዚአብሔር ልጆች ላይ ስለፈጸማችሁት ግፍ እግዚአብሔር በእያንዳንዳችሁ በምትወልዷቸው ልጆች ላይ ፍርዱን ያሳያችኋል በልጆቻችሁ ታገኙታላችሁ ጠብቁ።

ከቤተክርስቲያን አሳዳችሁ ስላስወጣችኋቸው አገልጋዮችና ምዕመናን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እግዚአብሔር ደሙን ከእጅህ እፈልጋለሁ ብሎ በግልጽ ይጠይቃችኋል።ፍርድን ከእግዚአብሔር ጠብቁ።

እናንተ የተለሰነ መቃብር የምትመስሉ ግብዝ አገልጋዮች የቤተክርስቲያን ልጆችን አሳዳችሁና በረሃብ ቀጥታችሁ ለሌሎች አሳልፋችሁ ከሰጣችሁ በኋላ አንዳንዶቻችሁ የቤተመንግሥት ፍርፋሪ ለመለቃቀም ከዓቢይ አህመድ መንግሥት ጋር ተጣብቃችሁ ቤተክርስቲያን ላይ የመከራ ዶፍ ሲወርድ በየሥርቻው ድምጻችሁን አጥፍታችሁ ትቀመጣላችሁ ለሲዲና ለመጽሐፍ ችርቻሮ ሲሆን ግን ተለቃቅማችሁ ትመጣላችሁ።አንዳንዶቻችሁ ወንጌል እየሰበኩና እየዘመሩ ወጣቱን ይዘው የነበሩ አገልጋዮችን በሰይጣናዊ ቅናት አሳዳችሁ አስወጥታችሁ ዛሬ በዘር ፓለቲካ ውስጥ ገብታችሁ ስትጨመላለቁ እያየን ነው።ወጣቱ ከቤተክርስቲያን እየፈለሰ ሲሄድ ጉዳያቹ ስላልሆነ እናንተ የዩቱዩብ ምጽዋታችሁን ለመለቃቀም ፓለቲካ ስታንቦጫርቁ ትውላላችሁ።የቤተክርስቲያን አምላክ ይፈርድባችሁ።በጣም ርካሾች ናችሁ።

ዛሬ እኮ ብዙ ወጣት ከቤተክርስቲያን እየኮበለለ እየወጣ ያለው እናንተ መድረኩን እንጂ የወጣቱን ልብ መያዝ ስላልቻላችሁ ነው።ሲጀመር በሥጋዊ ቅናት የእግዚአብሔርን መንፈስ እያሳዘናችሁ የምትሰብኩት ስብከት ለእናንተ ንግድ እንጂ ለወጣቱ ሕይወት አይሆንም ለዚህ ነው የቤተክርስቲያን አማኞች ቁጥር ቁልቁል እየወረደ ያለው።

ሌላው የገረመኝ ጉዳይ ኢሊሌ ሆቴል ከፓስተሮችና ሁስታዞች ጋር ስለ ሃገራዊ ጉዳይ እንወያያለን ብላችሁ የለጠፋችሁት ማስታወቂያ ነው።እውነት እናንተ በመወያየት የምታምኑ ከሆኑ ከጥቂት ዓመታት በፊት ስንቱን የወንጌል አገልጋይና ዘማሪ ነው ከቤተክርስቲያን ካልወጣ ካልተወገዘ እያላችሁ አድማ እያሳደማችሁ ስታሳድዱ የነበረው ? አታስመስሉ እግዚአብሔር ያያል፣ልብና ኩላሊትንም ይመረምራል።በመወያየት የምታምኑ ከሆነ ለመሆኑ የትኛውን አገልጋይ ነው ጠርታችሁ ያወያያችሁት ፣የት ቦታ፣በምንጊዜ፣በምን ርዕሰ ጉዳይ ? በጅምላ አይደል እንዴ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ልጆች በአድማ አሳዳችሁ ለአውሬ የሰጣችኋቸው እግዚአብሔር ግን ይፈርዳል የማንም ዕንባ ፈሶ አይቀርም።

አሁንም ከፓስተርና ከሁስታዝ ጋር የውይይት ፕሮግራም ብላችሁ ሕዝቡን በየሆቴሉ እንደ ከብት የምትነዱት ለሃገር ተጨንቃችሁ፣ለቤተክርስቲያን አስባችሁ ሳይሆን ከዓቢይ አህመድ መንግሥት ጋር ተመሳስላችሁ ለመኖር እንደ ውሻ እየተላላሳችሁ ለመኖር የነደፋችሁት ርካሽ ሥጋዊ ዕቅድ ነው።

ስለዚህ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በጣም አስተውሉ ዛሬ ቤተክርስቲያንን ከበው ያሉት አስመሳይ ነጋዴዎች ፣በሥጋዊ ቅናትና ፣ሥጋዊ አድማ ልባቸው የደነደነ ክፋዎች እንጂ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ለጨበጡት ወንጌል ታምነው ክርስቶስ ኢየሱስን በጽድቅ የሚያገለግሉ የጽድቅ አጉልጋዮች አይደሉም።የሰው ደም በየቦታው ሲፈስ ግድ የማይላቸው፣ኦርቶዶክሳውያን ብሔራቸውና ሃይማኖታቸው እየተለየ እንደ ከብት ሲታረዱ ለምን ብለው አጥብቀው የማይታገሉ አስመሳዮች ፣ለአንድ ሐሰተኛ ነቢይ የኦርቶዶክሳውያን መኖሪያ ቤት ፈርሶ ሜዳ ላይ ሲበተኑ ሄደው የማያጽናኑ ለምን ብለው የማይሟገቱ ሐሞተ ቢስ ግብዞች ናቸው።ሕዝቡን ለገንዘቡ ሲሆን እንጂ በመከራው ሰዓት ዞር ብለው አያዩትም።

በርግጥ እውነተኛ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች አሉ ትናንትም አድማና ተንኮል ውስጥ ያልነበሩ ዛሬም ክርስቶስ ኢየሱስን በሰው ልብ ውስጥ እስኪሳል ድረስ በጭንቅ የሚሰብኩ ብርቱ አገልጋዮች አሉ።አስመሳይ ነጋዴዎቹ ግን ሸቀጣቸውን ለማረገፊያ በየሆቴሉና በየአዳራሹ ኑ ሲሏችሁ ለምን ? ብላችሁ መጠየቅን ልመዱ ።

መ/ር ታሪኩ አበራ

ለሌሎችም ሼር አድርጉት