Get Mystery Box with random crypto!

#ሼር_ፖስት ይድረስ ለፅጌረዳ አብርሃ ====================== ፅጌ ደህናነሽ ብዬ እንዳ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

#ሼር_ፖስት ይድረስ ለፅጌረዳ አብርሃ
======================
ፅጌ ደህናነሽ ብዬ እንዳልጀምር ደህና አይደለሽም። ደብረ ዳሞን ተራራ የወጡ እግሮችሽ ተቆርጠው ክራንች ላይ ተቀምጠሽ በመቀሌ ጎዳና "ተረስተናል" ከሚሉት የጦር ጓደተኞች መካከል አየሁሽ። አወ...ደህናማ አይደለሽም፣ ሁላችንም ደህና አይደለንም ፅጌ።

ታስታውሺ እንደሆነ..የዛሬ 5 ዓመት ደብረ ዳሞ ገዳም ነበር የተገናኘነው፣ እንዲያውም ዐፄ ልብነ ድንግል የተቀበረው እዚሁ ገዳም እንደሆነ ነግሬሽ ነበረ።አምባገነኖች በፈጠሩት ጦርነት ውስጥ ተሳትፈሽ እግሮችሽን በማጣትሽ አዝኛለሁ።ፅጌ እንዲህ አለያይተው የሚያቋስሉን ፖለቲከኞች ናቸው።"ጦርነት ባህላዊ ጨዋታ ነው" የሚሉ እብሪተኞች ናቸው።

ዐማራና ትግራይ የሴም ልጆች እንደሆኑ ይታወቃል። ቅድመ አያታችን ሴም ነው። አቺናኔ የሴም የልጅ ልጆች ነን። በአማርኛ "ለሁሉም ጊዜ አለው" ብዬ ብጠይቅሽ በትግርኛ፣ "ንኹሉ ጊዜ አለዎ" ብለሽ እንደምትመልሽልኝ እርግጠኛ ነኝ። በዚህ መካከል ምንም ልዩነት የለም። ቋንቋችን ሴማዊ ፤ የዘር ግንዳችን ከሴም።

አየሽ ፅጌ... ዐማራና ትግሬ እንዲህ ብዙ ሺህ ዓመታት ጒንጒን ማንነት ያላቸው፣ በማይፈታ መልኩ የተጋመዱ ናቸው። በባህል የተሰበጣጠሩ፣ በቋንቋ የተወራረሱ፣ በደም ጥልቀትና በሥጋ ልደት የተሳሰሩ፣ በአንድ እናትና በአንድ አባት ጉያ፤ በአንድ ቤት ውስጥ አብረው ያደጉ ሕዝቦች ናቸው። ነገርግን ሕወሓት ዐማራን ብቻ ነጥሎ "የትግራይ ሕዝብ ደመኛ ጠላት" በማለት ፈረጀው። መለስ ዜናዊ ስለትግራይ ወርቅነቱ ሲመሰክር ዐማራን ግን አከርካሪውን ሰብረው እንደጣሉት በአደባባይ ተናገረ። እንዲህ እያሉ በመካከላችን የሚያለያይ የባቢሎን ግንብ ገነቡ።

የዐፄ ይኩኖ አምላክ አባት ተስፋ ኢየሱስ፤ አያቱ እድም አሰገድ የአክሱም ልዑላን ልጆች መሆናቸው ተዘነጋ። እነ ዐፄ ዘርዓያዕቆብ፣ እነ ዐፄ ዓምደ ፅዮን ንግሥናቸውን የፈፀሙት አክሱም ፅዮን ነበር። ዐፄ ልብነ ድንግል እና ባለቤታቸው እቴጌ ሰብለ ወንጌል የተቀበሩት ደብረ ዳሞ ገዳም ነበር።
ዐማራና ትግሬ ለመጀመሪያ ግዜ በጃንደረባው "ባኮስ" የክርስትና ሃይማኖት የተሰበከላቸው፣ ለመጀመሪያ ግዜ በካህኑ "ሕዝበ ቀድስ" አንድ ላይ የተጠመቁ ሕዝቦች ነበሩ። ገድለ ተክለ ሃይማኖት እንዲህ ይላል፣ "የትግሬና የአምሐራ ሰዎች በሕዝበ ቀድስ ቃል አምነው ፍጹማን ክርስቲያኖች ሆኑ። ደጋጎቹ ነገሥታት አብርሃና አጽብሃ በነገሡበት ዘመን።"

ምን ይሄ ብቻ በአንድ ቤተ መቅደስ አብረው ቀድሰዋል፤ በአንድ ቤተክርስቲያን አብረው አስቀድሰዋል። ዐማሮች አክሱም ፅዮን፣ ትግሬዎች ላሊበላ እየመጡ ተሳልመዋል። በ1708 ዓ.ም ደምቢያ ውስጥ ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን ተሰርታ ስትመረቅ የዐማራና የትግሬ ሰዎች በአንድ ላይ ዘምረዋል። የዐፄ ዮስጦስ ዜና መዋዕል እንዲህ ይላል፣ "....የጥምቀት እለት ታቦተ ልደታን አገቡ ነጋሪት እየተመታ መድፍ እየተተኰሰ በይባቤ በማኅሌት። የትግሬ መኳንንት ወይዛዝርት በአገራቸው ዘፈን እየዘፈኑ። ተከዜ ወዲህ ያለ ዐማሮች በዐማራ ዘፈን እየዘፈኑ"

የቤተ አምሐራዋን ተድባበ ማርያም፣ ጣና ቂርቆስን፣ የቤጌምድሩን ጃን ሚካኤልን፣ የጎጃሞችን መርጡለ ማርያምንና ደብረ ወርቅን የተከሉት አብርሃ ወአጽብሐ ናቸው። በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዋግና በላስታ አካባቢዎች ብልባላ ቂርቆስን፣ ብልባላ ጊዮርጊስን፣ አርባዕቱ እንስሳን እና ሳርዛና ሚካኤልን ያሳነጻቸው ዐፄ ካሌብ ነው። በ862 ዓ.ም. ሐይቅ እስጢፋኖስ የተመሠረተው በአክሱም ንጉሥ ዐፄ ድልነዐድ ነው። ወደ ጣና ሐይቅ በመምጣት የማንዳባን ገዳም የመሠረቱት አቡነ ያሳይ የትግራይ እንደርታ ተወላጅ ናቸው። በጣና አካባቢ መጀመሪያ ካስተማሩት ሰባቱ ከዋከብቶች መካከል አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ትውልዳቸው ትግራይ አዲ ሀገራይ ነው። በግራኝ የፈራረሰችውን አክሱም ፅዮን መልሶ ያሳነጻት ዐፄ ፋሲል ከጎንደር አክሱም ተጉዞ ነው። በ505 ዓ.ም. የተወለደው ቅዱስ ያሬድ ምልክት የሌለው ድጓ የጻፈው ጣና ቂርቆስ ውስጥ ነው።

.... ግን ምን ያደርጋል በመካከላችን የተዘራብን የሚያካክድ የታሪክ ሐተታ እንጂ እንዲህ ያለው የሚያፋቅር ታሪክ አይደለም። ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ሞቢላይዝ ለማድረግ የሐሰት ታሪክ በመጻፍ (the falsification) እና ታሪክን በማዛባት (manipulation of history) ዐማራውን ነጥሎ ነው የከሰሰው። አንድነትን፣ አብሮነትን ከመስበክ ይልቅ ዘረኝነትን (Racism)፣ እና አውራጃዊነትን (Provincialism) ሲዘራ ነው የኖረው። በግራኝ የተከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ የትግራዩ አዛዥ ሮቤል እና የጎጃሙ ዐማራ ራስ ወሰን ሰገድ በአንድ ላይ ተዋግተው በአንድ ጉድጓድ ተቀብረው ነበር። ሕወሓት ግን ነጣጥሎ አታኮሰን።

እናም ፅጌ ከተከዜ ወዲህና ወዲያ ማዶ አድርገው የሚያላቅሱን ገዥዎች እንጂ ዐማራና ትግሬ የአንድ ቤተሰብ የሴም ልጆች ናቸው። በጦርነቱ የተጎዳነው ሁለታችንም ነው።
ዛሬም ሳይሆን በፊትም። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና ደርግ በትግራይ ላይ አደረሱት ከሚባለው በደል በላይ በዐማራው ላይ አድርሰዋል። ዐፄ ኃይለሥላሴ ለጎጃም ዐማራ ችግር ዳቦ ከሰማይ በአውሮፕላን አልጣሉለትም። የወረደው ቦንብ ነው። ደርግ ለጎጃም የብቸና ሕዝብ ተቃውሞ ምላሹ የብቸናን ሕዝብ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ነው። በናፓልም እሳት ነው ያቃጠላቸው። ከሃውዜን የበለጠ ሕዝብ በብቸና ተጨፍጭፏል።

በ1966 ድርቅ በትግራይ ላይ ከደረሠው አደጋ በወሎ ያለቀው ህዝብ ይበልጣል.. ፅጌ። የ1965/67'ቱን አሠቃቂ ድርቅ፣ ረሃብና እልቂት በተመለከተ ጆናታን ዲምቢልቢ የተባለው ጋዜጠኛ የተደበቀውን ረሃብ "The hidden Hunger" በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን ፊልም በቴምስ ቴሌቪዥን ላይ በማቅረብ አሰቃቂውን የወሎ ዐማራ ያጽም ምስልና ምጽዋት ሲለምኑ የሚያሳየውን አሳዛኝ ትርኢት ለዓለም ከማሳየቱም በላይ ፊልሙን ሲጀምር "በምዕራብ አፍሪቃ ከብቶች ሲያልቁ በኢትዮጵያ ግን ሰዎች እያለቁ ነው።" በማለት የዓለምን ሕዝብ በየቤቱ ገብቶ ልቡን ሰብሮታል። ይህን ፊልም ብታይው ደም ዕንባ ታለቅሻለሽ። ግን ዐማራ ልዩ ተጠቃሚ ይመስል በጨቋኝነት ተፈረጀ። በተምቤን ቆላ የምትኖር አንዲት የትግራይ እናት እና በመንዝ ተራራ የምትኖር አንዲት የዐማራ እናት ሕይወት ተመሳሳይ ነው። ነገርግን ዐማራ በጨቋኝነት ተፈርጆ ላለፉት 50 ዓመታት ተዘመተበት። የመከራ ዶፍ ወረደበት። ጫካ መንጥሮ፣ ገደል ቆፍሮ በልፋት ድካሙ በሚኖረው ሚስኪን ህዝብ ላይ ከግራ ቀኝ እሳት ተወረወረበት።

....አሁንም በጦርነቱ የተጎዳነው ሁለታችንም ሆኖ ሳለ ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ብቻ እንደተጎዳ ለማስመሰል የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። ነገርግን ከትግራዊቷ ፅጌረዳ ላይ የደረሰው ቁስል ከዐማራዊቷ ኢክራም ላይ ደርሷል። የአጣዬ ከተማ ነዋሪ የሆነች የ14 ዓመት ታዳጊ ኢክራም በቡድን እየተፈራረቁ ደፍረዋታል። ፅጌረዳ? አንቺ ላይ ያለው የጭን ቁስል ኢክራም ላይ አለ። በዋግኽምራ ዞን በሰቆጣ ወረዳ "ጭላ" ቀበሌ ልትወልድ ሳምንት የቀራትን ነፍሰጡር ሴት ተደፍራ ልጇ ከሆድዋ ላይ እንደሞተ ስነግርሽ በተሰበረ ልብ ነው። ሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ የአስር ቀን አራስ እናትን መሬት ላይ ጥለው ለአራት ከደፈሯት በኋላ አራሱን ጨቅላ "የዐማራ ልጅ አድጎ በኋላ ስለሚወጋን" በማለት ሽንት ቤት እንደጣሉት ስነግርሽ በሃዘኔታ ነው።