Get Mystery Box with random crypto!

#Ethiopia ማንኛውንም ሰው ከሀገር እንዳይወጣ የማገድ ስልጣንን፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አ | Skyline media

#Ethiopia

ማንኛውንም ሰው ከሀገር እንዳይወጣ የማገድ ስልጣንን፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመራ ኃላፊ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀረበ።

የአዋጅ ማሻሻያው ምን ይዟል ?

ማንኛውንም ሰው ከሀገር እንዳይወጣ የማገድ ስልጣንን፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመራ ኃላፊ ይሰጣል።

ነባሩ ህግ ምን ይላል ? “ ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በህግ መሰረት በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ብቻ ነው ” ይላል። ዛሬ ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ በነባሩ ህግ የተቀመጠውን የፍርድ ቤት “ ብቸኛ ስልጣን ” የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመራ ኃላፊ በተጨማሪነት ያጋራ ነው።

አዲሱ ማሻሻያ ፥ " የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ከሚመለከታቸው የደህንነት አገልግሎት እና ህግ አስከባሪ አካላት ከሚያገኘው መረጃ ወይም አገልግሎቱ በራሱ ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት፤ በብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ መኖሩን ሲያምን፤ ማንኛውም ሰው ከሀገር እንዳይወጣ ማገድ ይችላል " ሲል ደንግጓል። 

  የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት " ከሀገር እንዳይወጣ ያገደውን ሰው ይዞ የሚያቆይ ከሆነ ፍርድ ቤት መቅረቡን ማረጋገጥ አለበት " ሲል የአዋጅ ማሻሻያው ደንግጓል። 

ዜጎች ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ስልጣን ላይ ማሻሻያ የተደረገው፤ በነባሩ ድንጋጌ ምክንያት እየደረሰ ያለውን " ከፍተኛ ጉዳት " ለመቅረፍ ነው ይላል ማሻሻያው። አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ መሰረት " ከፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እስኪገኝ ድረስ በብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ወይም ሊያደርሱ የሚችሉ ሰዎች ከሀገር እየወጡ ከተጠያቂነት እያመለጡ በሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው " መሆኑን የረቂቅ አዋጁ ገልጿል።

በሌላ በኩል ፦

ማሻሻያ አዋጁ " አስተዳደራዊ ቅጣት " አንቀጽ ይዟል።

" ከጊዜ ወደ ጊዜ በህገ ወጥ መንገድ በሀገራችን ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እየተበራከቱ፤ በህገ ወጥ ድርጊቶች እየተሳተፉ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ በአስተዳደራዊ ቅጣት በመቅጣት ከህገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው " ሲል ያስረዳል።

በዚህም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሀገር ዜጎችን " በጥቁር መዝገብ እንዲመዘገቡ እና ከሀገር እንዲወጡ ማድረግ ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲመጡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና " እንዳለው ተብራርቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ አማካኝነት፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጥል በአዋጅ ማሻሻያው ስልጣን ተሰጥቶታል።

" ይህን አዋጅ አሊያም በዚህ አዋጅ መሰረት የወጣ ደንብ ወይም መመሪያን የጣሰ ማንኛውም ሰው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰድበታል " ይላል ማሻሻያው።