Get Mystery Box with random crypto!

የሰላም ምሽጋችሁን ለብልፅግና አትልቀቁ! የድርድር ጉዳይ ወጥመድ እየሆነ ነው። ሰሞኑን ደግሞ ለብ | Skyline media

የሰላም ምሽጋችሁን ለብልፅግና አትልቀቁ!

የድርድር ጉዳይ ወጥመድ እየሆነ ነው። ሰሞኑን ደግሞ ለብልፅግና በሚመች መልኩ ወደ ወጥመዱ ዘው ተብሎ እየተገባ ነው። ጥቃት ፈፃሚው ብልፅግና ሆኖ ተጠቂዎቹ "አንደራደርም" የሚል የማይገባ ሽሽት እያደረጉለት ነው። ከዚህ የተሻለ ማድረግ ይቻል ነበር።

1) ብልፅግና እውነተኛ ድርድር አይፈልግም። ከምንም በላይ የሚፈራቸው የአማራ ጥያቄዎች አጀንዳ ሆነው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ባለበት ወይንም በሚሰማው እንዲቀርቡ አይፈልጉም።

2) የከረመውም ሆነ የሰሞኑ ዘመቻ ብልፅግና ሰላም እንደማይፈልግ ማሳያ ነው። አዳክሜያቸው ከፈለኩት ጋር እደራደራለሁ እያለ ነው። የአማራን ጉዳይ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀርብበት አይፈልግም። ድርድር አንፈልግም ከማለት ይህን የአገዛዙን አካሄድ በተደጋጋሚ ማውሳት፣ ጦረኝነቱን ማሳየት፣ እየፈፀመ ያለውን ሰብአዊ ውድመትን በየአጋጣሚው አጀንዳ ማድረግና የአገዛዙ መልክ ሰላም ሳይሆን ይህኛው መሆኑን ማስመር።

3) እደራደራለሁ አልደራደርም ሳይባልም የሚሰሩ የህዝብ ግንኙነቶች አሉ። አገዛዙን የቋጥኝ ያህል የሚከብዱት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። በዛውም ደጋግመህ የተቆጠሩ የአማራ ጥያቄና በደሎችን ነው የምታስተዋውቀው።

4) አልደራደርም ካልክ ግን ብልፅግና ደስታው ነው። እንደ ሰላም ኃይል ሆኖ የሰላም ምሽግህን ይረከብሃል። "ድርድር ውይይት" ብሎ የለቀቀው የሰላም ምሽግ ገብቶ ፕሮፖጋንዳ ያዘንብብሃል። ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ አድርጎ ጭምር ሰላማዊ ለመምሰል ይጥራል። ህዝብ ጥሪ አቀረበ ወዘተ እያለ ይቀጥላል። በእልህ ከሰላም ምሽግህ ትርቃለህ። ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ያስጠቁርሃል። በዛውም የአማራውን የህልውና ጥያቄ የግብዝነት፣ የእብሪት እያስመሰለ ይቀጥላል።

5) አሁን ባለው ሁኔታ ብልፅግና ለማወናበድ ተጨማሪ እድል እያገኘ ነው። ድርድርና ወዘተ ብሎ ቢመጣ "አንደራደርም" ያሉት ካፈርኩ አይመልሰኝ " ብለው ይሸሹለታል። እየሸሹለትም ነው። የማይገባውን እድል እያገኘ ነው።

6) ብልፅግና እንኳን ወደ አዲስ አበባ ሸሽቶም ቢሆን በድርድር ቁማር ሞክሯልኮ። አልፈልግም አላለም። ወደ ክልል አወረደው። "መሳሪያ አስረክበው ይምጡ" ብሎ መቀረጃ አደረገበት። እጅ ስጡ የሚል ሆኖ "የሰላም ጥሪ" አድርጎ ቀባባው። ብልፅግና እንኳን ድርድር አልፈልግም ከማለት በዚህ ቁማር ተጫወተ። ይህን ያደረገው ጭንቅ ውስጥ ሆኖ፣ እየተሸነፈ ጭምር ነው። የፋኖ አመራሮች ይችን እንኳ እየተጫወቱባት አይደለም። የሰላም ምሽጋቸውን ለብልፅግና እየለቀቁለት ይመስላል።

7) ይህ ሁሉ ሆኖ፣ የሰላም ምሽግህን ለቅቀህ ነገ እደራደራለሁ ብትል በዲፕሎማሲው ገፅህ ይገረጣል። ደጋፊዎችህ እምነት ያጡብሃል። ብልፅግና ከለቀቅክለት ቦታ እየተንጎማለለ አንተ ወዳለበት እየሄድክህ እንደሆነ አድርጎ ያቀርብሃል።

8/ ያለ አለም አቀፍ ማህበረሰቡ አራት ኪሎ የሚታሰብ አይደለም። ባለፈው የአሜሪካ አምባሳደር ወቀሳ አቅርቧል። ብዙ ተቆርቋሪዎች ያን መግለጫ እንዲያርም በሚጥሩበት ወቅት ድካማቸው ላይ ውሃ የሚቸልስ፣ ዲፕሎማቶቹ ለወቀሳ የሚሆን ተጨማሪ ምክንያት እንዲያገኙ፣ ፋኖ ባንክ ዘረፈ ሲባል ባንክ እየጠበቀ ያገኛትን የዓለም አቀፍ እውቅና የሚያበላሽ የውድቀት መንገድ ነው። አራት ኪሎን የሚያስብ አካልም ድርድርን በዚህ መልክ አይገልፀውም። እውነተኛ ጥያቄ ተይዞ የድርድርን ምሽግ በድሮን ንፁሃንን ለሚጨፈጭፍ ኃይል መልቀቅ ሽንፈት ነው።

9) ሰው የጦር ሜዳ ጀግንነትን ብቻ ሳይሆን ብልጠትንም ከፋኖ መሪዎች ይጠብቃል። የወረዳና ቀበሌ ከተማ ተያዘ ተለቀቀ ብሎ ዜና የሚያጮህ ዩቱዩበኛ አልደራደርም ስትል ሊያሞካሽህ ይችላል። ግን አይጠቅምህም። ወደ ወጥመድ ነው የሚያስገባህ። ለአራት ኪሎ የሚበቃ ሀሳብ ሊሰጡ የሚችሉ ትልልቅ ወታደራዊም ፖለቲካ ልምድ ባለቤቶች "የልጆች ጨዋታ ሆነ" ብለው ይሸሹሃል። ቀሪው ህዝብ ሰላም እፈልጋለሁ ስላልክ በበጎ ያይሃል። አገዛዙ ነው በጥባጩ የሚለውን ትቶ አንተን አይወቅስም። አራት ኪሎ ለመግባት የሌሎች ትብብር ወሳኝ ነው። ዛሬ አልደራደርም ያልከው፣ ነገ ከእሱም ጋር አልደራደርም እንዳትል ይሰጋል።

10) አገዛዙ በአሁኑ ወቅት በጨፍጫፊነት እየተወገዘ ነው። "አልደራደርም" ስትል ከአሁን አጀንዳውን ከሰብአዊ ግፍ ሰላም ፈላጊ መስሎ ብቻ አይመጣም። የፈፀመውን ለማስረሳት፣ ከአሁን በኋላ የሚፈፀመውን በአንተ ምክንያት የመጣ ጭምር አድርጎ ያቀርባል። ቅሬታ ብታቀርብ "ለምን አትደራደርም" የሚባል ወቀሳ ይቀርብብሃል። የሰላም ምሽግህን ከለቀቅክ የተፈፀመብህን መከራ እንኳን እንዳትናገር የተጠመደብህ ወጥመድ ጭምር ነው።