Get Mystery Box with random crypto!

በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ ማስነሳት እርምጃ ጋር በተያያዘ የአን | Skyline media

በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ ማስነሳት እርምጃ ጋር በተያያዘ የአንድ ሰው ህይወት ህልፈት ሪፓርት እንደደረሰው ኢሰመኮ አስታወቀ።

በቤት ማፍረስና በግዳጅ ማንሳት እርምጃ ለተጎዱ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት የሚያገኙበትና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ ማስነሳት እርምጃ የመኖሪያ ቤት አልባነትን አባብሷል ብሏል።

ኢሰመኮ በጉዳዩ ዙሪያ በለገጣፎ ለገዳዲ፣ በሰበታ  አካባቢ ፉሪ እና ለቡ ተክለሃይማኖት እንዲሁም በቡራዩ ገፈርሳ ኖኖ አካባቢዎች በመዘዋወር ቀደም ሲል የፈረሱ እና የማፍረስ ተግባሩ እየተከናወነ የነበረባቸውን አካባቢዎች ተመልክቻለሁ ነው ያልው፡፡

ኮሚሽኑ በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ በመገኘት
እየፈረሱ የነበሩ ቤቶችንም ለመመልከት ችሏል።
በምልከታው የቤት ማፍረሱ እና በግዳጅ ማስነሳቱ በግብረ ኃይል እየተከናወነ እንደነበረ እና በቦታው ከፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ዱላ የያዙ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩም መመልከቱን ነው ያሳወቀው።

በዘመቻ ቤት የማፍረሱ ሂደት ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት ስለመሆኑ  ፣ አድሏዊ አሰራሮች መኖራቸውና ይህም ከብሔር ማንነት ጋር የተገናኘ መሆኑን፣ እና በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ቤቶች እንደሚፈርሱ መረዳቱን ገልጿል።

እስር፣ የአካል እና የስነልቦና ጉዳት መድረሱንም በሪፓርቱ ኢሰመኮ አትቷል። ፊሊዶሮ በተባለ ቦታ ላይ በተደረገው የቤት ፈረሳ የሰው ሕይወት ማለፉን ኢሰመኮ መረጃ የደረሰው ሲሆን ይህን በተመለከተ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቋል። 

ኢሰመኮ ከአቤቱታ አቅራቢዎች እና ተገቢነት ካላቸው የመንግሥት አካላት ባሰባሰበው መረጃ እና ማስረጃ መሠረት የማፍረስና በግዳጅ የማንሳት እርምጃው በርካታ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ቀውስ ዳርጓል፤ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ለማቋረጥ ተገደዋል፤ በርካታ ቤተሰቦች የእለት ተእለት ተግባራቸውን ማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በርካታ ቤተሰቦች ተፈናቅለው ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመሄድ ተገደዋል፤ ከፊሎቹም መንገድ ላይ ወድቀዋል ወይም በተለያዩ የሀገር ውስጥ መጠለያ ጣቢያ በመሰብሰብ የመንግሥት እርዳታ ለመጠባበቅ ተገደዋል" ነው ያለው፡፡ 

የክልሉ መንግሥትና የከተማ አስተዳደሩ የማፍረስና በግዳጅ የማንሳት እርምጃውን ተግባራዊ ከማድረግ በፊት ቤቶቹ እንደተገነቡበት የይዞታ ዓይነትና ሁኔታ፣ ለብዙ ዓመታት የመብራት እና የውሃ እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ እና ነዋሪዎቹ የማኅበራዊ ሕይወት እንዲመሠርቱ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት አማራጭ መፍትሔዎችን በማመቻቸት የሰብአዊ መብቶች መከበራቸውንና መጠበቃቸውን ሊያረጋግጥ ይገባ እንደነበር አስገንዝቧል፡፡ 

በቤት ማፍረስና በግዳጅ ማንሳት እርምጃ ለተጎዱ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ 

የኢሰመኮ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል “ኢመደበኛ ይዞታዎቸን መከላከል የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም የማፍረስና በግዳጅ የማንሳት እርምጃዎች ሰዎች ሕይወታቸው እንዲናጋ እና ቤተሰብ እንዲበተን የሚያደርግ መሆን የለበትም፤ ይልቁንም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች የተከበሩበት አሠራር መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል፡፡